ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ አካባቢው በእሳት ተያይዞ ይታያል
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን የፈፀመው ለሁቲ ታጣቂ ቡድን የሚደርሱ ቁሳቁሶችን እና ገንዘቦችን ለመገደብ መሆኑን ተናግሯል

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ጦር በየመን በሁቲዎች ላይ በፈፀመው የአየር ጥቃት የነዳጅ ማከማቻ ማውደሙን አስታወቀ።

በራስ ኢሳ የቀይ ባህር ወደብ ላይ የተፈጸመው የዚህ ጥቃት አላማ በኢራን ለሚደገፈው የሁቲ ታጣቂ ቡድን የሚደርሱ ቁሳቁሶችን እና ገንዘቦችን ለመገደብ መሆኑ ተገልጿል።

ሁቲዎች በጥቃቱ ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን የገለፁ ሲሆን ከሟቾቹ መካከልም በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል ብለዋል።

የሐሙሱ የአየር ጥቃት የተፈጸመው ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ጦር በሁቲዎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ካጠናከረ በኋላ ነው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት በጥቃቱ ምን ያህል ሰው እንደሞተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አለመስጠታቸውን ዘግቧል።

በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጽያን በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦችን ማጥቃት የጀመሩት የእስራኤል እና የጋዛ ጦርነት በጥቅምት 2023 ከጀመረ በኋላ ነው።

የሁቲ አማፂያን በፈጸሟቸው ጥቃቶቹ የንግድ መርከቦች የሰጠሙ ሲሆን በዚህም የተነሳ ብዙ የመርከብ ኩባንያዎች ቀይ ባህርን መጠቀም እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል።

ቀይ ባሕር የዓለማችን 15 በመቶ የንግድ መርከቦች የሚመላለሱበት መስመር ነው።

አሜሪካ ከባለፈው ወር ጀምሮ በየመን የሁቲ ዒላማዎች ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ጨምራለች።

አማጺው ሁቲ ራሱን በኢራን የሚመራው የእስራኤል፣ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት ተቃዋሚ ንቅናቄ አካል አድርጎ የሚቆጥር ሲሆን፣ በጋዛ ሰርጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ያለውን ድጋፍ በይፋ ገልጿል።

የሁቲ አማጺያን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸው መርከቦች ላይ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ጥቃት እያደረሱ ቆይተዋል።

ይህንንም የሚያደርጉት ለፍልስጤም ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

በምላሹ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሁቲ ኃይሎችን ዒላማ በማድረግ የመን ውስጥ ተከታታይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል።

በአጸፋው የሁቲ አማጽያን ከእነዚህ አገራት ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሌሎች አገራት መርከቦችን ዒላማ እያደረጉ ይገኛሉ።

ይህ የአማጺያኑ ጥቃት በርካታ የመርከብ ድርጅቶች በዓለም የባሕር ንግድ ውስጥ 15 በመቶ ድርሻ ያለውን የቀይ ባሕር መስመርን እንዳይጠቀሙ እያስገደዳቸው ነው።

የሁቲ አማፂያ ከኢራን የገንዘብ ድጋፍ የሚደርግላቸው ሲሆን በሊባኖስ ውስጥ የሚገኘው የሺአው ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።

ሄዝቦላህም ለሁቲ አማጽያን ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮም ሰፊ ወታደራዊ ስልጠናዎችን መስጠቱን ሽብርተኝነትን የሚዋጋው ‘ዘ ኮምባቲንግ ቴሬሬዚም ሴንተር’ የተሰኘው የአሜሪካው የምርምር ተቋም አስታውቋል።

ሁቲዎች ኢራንን በአጋርነት የሚያይዋት ሲሆን ሳዑዲ አረቢያም የጋራ ጠላታቸው ናት።

ኢራን ለሁቲ አማጺያን የጦር መሳሪያ ታቀርባለችም የሚሉ ጥርጣሬዎችም ጎልተው ይሰማሉ።