የአልሸባብ ታጣቂዎች (ፎቶ ፋይል)
የምስሉ መግለጫ,የአልሸባብ ታጣቂዎች ከቅርብ ወራት ወዲህ ዳግም እየተሰባሰቡ እና ተከታታይ ጥቃቶችን እየፈጸሙ ነው (ፎቶ ፋይል)

ከ 4 ሰአት በፊት

የሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ቁልፍ አካባቢዎችን ለመቆጣጣር የሚያደርጉትን ጥረት ተከትሎ በተደረገ ውግያ አሜሪካ እና ሶማሊያ በታጣቂ ቡድኑ ላይ የአየር ድብደባ መፈፀማቸወን የሶማሊያ መንግሥት ገለፀ።

ከዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾ በስተሰሜን በምትገኘው አዳነን ያባል ላይ “በሚገባ የተቀናጀ” የአየር ጥቃት የተፈፀመው አልሸባብ ከተማይቱን ከወረረ ከሰዓታት በኋላ ነው።

አልሸባብ ከተማይቱን ሲቆጣጣር ለወታደራዊ ዘመቻ ቁልፍ ማስጀመሪያ ለማድረግ ማቀዱ ተነግሮ ነበር።

የሶማሊያ ማስታወቅያ ሚኒስቴር መስርያ ቤት በኤክስ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ በአየር ጥቃቱ ከተገደሉት 12 ታጣቂዎች መካከል የእስላማዊ ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ከፍተኛ ተዋጊዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

አልሸባብ ባለፈው ወር በፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ አጃቢ መኪኖች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።

የታጣቂ ቡድኑ በተደጋጋሚ የፈጸማቸውን ጥቃቶች የሚከታተሉ በሶማሊያ የእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴ ዳግም ሊያንሰራራ ይችላል የሚል ፍርሃታቸውን ገልጸዋል።

በደቡብ እና መካከለኛው ሶማሊያ ሰፊ አካባቢዎችን የሚቆጣጠረው አልሸባብ ከመንግሥት ጋር ለ20 ዓመታት ያህል ሲዋጋ ቆይቷል።

ታጣቂ ቡድኑ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥትን በኃይል በማስወገድ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት ይፈልጋል።

በአፍሪካ ኅብረት የሚመራው የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 እና 2023 ታጣቂ ቡድኑ እንዲያፈገፍግ እና ከማጥቃት ይልቅ መከላከል ላይ እንዲያተኩር አድርጎ ነበር።

ቡድኑ በርካታ ተከታታይ ወታደራዊ ጥቃቶች ቢፈጸምበትም አሁንም በሶማሊያ ትልቅ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።

የሶማሊያ መንግሥት ቡድኑ ተዳክሟል ሲል ያስተባብላል።

ረቡዕ ረፋድ ላይ የሶማሊያ መከላከያ እና የአሜሪካ አፍሪካ ኮማንድ (አፍሪኮም) የፈጸሙት የአየር ድብደባ “በታጣቂዎች የሚፈጠረውን ስጋት ለማስወገድ ያለመ” መሆኑን የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

“በጥቃቱ ታጣቂዎቹ እንደ መሰብሰቢያ እና ምሽግ ይጠቀሙበት የነበረውን ስፍራ ተመትቷል” ካሉ በኋላ “ከምንም በላይ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት አልደረሰም” ብሏል።

በመካከለኛው ሸበሌ ክልል የሚገኘው አዳን ያባል እአአ በ2016 በአልሸባብ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ፣ የፌደራል መንግሥቱ ጦር በ2022 መልሶ ይዞታል።

ረቡዕ ዕለት የአልሸባብ ተዋጊዎች ከተማይቱን ከወረሩ በኋላ በማለዳ ከባድ ውጊያ መቀስቀሱ ተነግሯል።

በኋላም ቡድኑ ከተማዋን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለፀ ሲሆን፣ ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎች ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ታጣቂዎች አዳነን ያባልን መቆጣጠራቸውን አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ከተማዋን በማን ቁጥጥር ስር እንደሆነች መንግሥት በመግለጫው ላይ ያለው ነገር የለም።

ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሀሙድ ባለፈው ወር ከተማዋን የጎበኙ ሲሆን፣ የጦር አዛዦችን አግኝተው ታጣቂዎችን ለመዋጋት አካባቢው ያለውን ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ጠቁመዋል።

በሌላ ዜና የብሔራዊ ጦር ኃይሉ ሐሙስ ዕለት በባይዶዋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ ቢያንስ 35 ተዋጊዎችን መግደሉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ፕሬዝደንት መሐሙድ አልሸባብ የሚያደርገውን ተከታታይ ጥቃት እና ግስጋሴ ያጣጣሉ ሲሆን፣ አልፎ አልፎም በጦር ሜዳ የሚገጥሙ ሽንፈቶች የሚጠበቁ ናቸው ብለዋል።

አክለውም መንግሥታቸው ታጣቂዎችን ለማሸነፍ ቆርጦ መነሳቱን ገልጸዋል።