
ከ 2 ሰአት በፊት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቢሾፍቱ አቅራቢያ ለሚያስገነባው አዲስ አየር ማረፊያ 2,500 አባወራዎች እንደሚነሱ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሥራ አስፈጻሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚያስነሳቸው 2,500 አባወራዎች መኖሪያ ቤቶች እንደሚገነባ እና በሚቀጥለው ዓመት ሕዳር ወር እንደሚያስረክባቸው እንዲሁም በተመሳሳይ ወር የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በቢሾፍቱ አቅራቢያ አቡሴራ አካባቢ አዲስ የሚገነባው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሚቀጥለው ዓመት ሕዳር ወር እንደሚጀመር አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።
በቢሾፍቱ አቅራብያ ይገነባል የተባለው ግዙፍ አውሮፕላን ማረፍያ 3,500 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ መሆኑን የገለፁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ከመሬታቸው ለሚነሱ 2,500 አባወራዎች “በሕዳር ወር ወደ አዲሱ መኖርያቸው እንደሚዘዋወሩ” አስታውቀዋል።
አቶ መስፍን በአካባቢው የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ እና የንግድ ተቋማትን ጨምሮ አዳዲስ አገልግሎት መስጫዎች እንደሚገነቡ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስገነባው አየር ማረፊያ ግንባታ ከአራት ዓመታት በኋላ የሚጠናቀቅ መሆኑን እና በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የአውሮፕላን ማረፊያ እንደሚሆን ተገልጿል።
ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባው ይህ አዲሱ አየር መንገድ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን እደሚያስተናግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
“በሁለት ምዕራፍ ግንባታው የሚከናወን ይሆናል። በመጀመሪያው ምዕራፍ 60 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ የሚችለው ይገነባል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 50 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግደው ሁለተኛው ምዕራፍ ይገነባል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ እአአ በ2029 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።
ለዓመታት በአዲስ አበባ የሚገኘው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።
የአየር መንገዱ ዕድገት በጨመረ ቁጥር ለአውሮፕላን ማረፊያው የተለያዩ የማስፋፊያ ስራዎች ሲከናወኑ ቢቆይም፣ በዓመት 25 ሚሊዮን ተጓዦችን ማስተናገድ በሚችልበት የመጨረሻ አቅሙ ላይ መድረሱን አቶ መስፍን አስታውቀዋል።
ይህ ግዙፍ የአየር መንገድ 1.1 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ የሚያርፍ የመንገደኞች ተርሚናል እንዲሁም 126,190 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ የሚያርፍ ለአየር መንገዱ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት፣100,000 ስኩዌር ኪሎሜትር ላይ የሚያርፍ የጭነት አገልግሎት መስጫ እንደሚይዝ ተገልጿል።
አዲሱ በቢሾፍቱ አቅራቢያ የሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረርያ ጋር በፈጣን መንገድ እንዲሁም በፈጣን ባቡር እንደሚገናኝ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ለአዲሱ አየር መንገድ ግንባታ የሚውል የ7.8 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል።
- የኢየሱስ ስቅለት እና ሞት በሕክምና ባለሙያዎች ዓይን እንዴት ይተነተናል?ከ 5 ሰአት በፊት
- በአማራ ክልል ለምክክር ኮሚሽን አጀንዳቸውን ያቀረቡት ታጣቂዎች የፋኖ ኃይሎች እንዳልሆኑ ተገለፀከ 5 ሰአት በፊት
- አልሸባብ የሶማሊያን ቁልፍ ከተማን መቆጣጣሩን ተከትሎ የአሜሪካ እና ሶማሊያ ጦር የአየር ድብደባ ፈፀሙከ 3 ሰአት በፊት
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
የአየር መንገዱ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከቢቢሰ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አፍሪካ አገራት ለሚያደርጋቸው በረራዎች ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቀው በአስተናጋጅ አገራት ከፍተኛ ክፍያ እና በነዳጅ ወጪ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማላዊ፣ቶጎ እና ዛምቢያን ከመሳሰሉ አየር መንገዶች ጋር በሽርክና እየሠራ ይገኛል።
ቢቢሲ አየር መንገዱ ከተለያዩ አፍሪካ አገራት ጋር በሽርክና እየሰራ እንዲሁም የበረራ መስመሮቹ ከፍተኛ ሆነው በእነዚህ መስመሮች ላይ የበረራ ዋጋው ከፍተኛ የሆነው ለምንድን ነው ሲል ለአቶ መስፍን ጥያቄ አቅርቧል።
አቶ መስፍን አስተናጋጅ አገራት ከፍተኛ ክፍያ መጠየቃቸውን በመግለጽ “አማካኙ የአፍሪካ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ” ነው ብለዋል።
አክለውም በዚህ የተነሳ ከመካለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እና እስያ ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ መሆኑን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በሌሎች አካባቢዎች የማይደረገው እና በአፍሪካ አየር መንገዶች ላይ የሚጣለው ታክስም የቲኬት ዋጋን ማናሩን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በባለፈው የበጀት ዓመት 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
ከአስር ዓመት በፊት ባወጣው ዕቅድ መሠረት በዘንድሮው በጀት ዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢያቅድም፣ገቢው 8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተገምቷል።
በአውሮፕላኖች እና በመዳረሻ አገራት ቁጥር ደግሞ በ2025 ግቡን ማሳካቱን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ከቦይንግ 67 አውሮፕላኖችን ለመግዛት አዝዟል።
አየር መንገዱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ የነበረው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኑ ተከስክሶ ሁሉም ተጓዦች እና የበረራ ሠራተኞች ሕይወታቸው ቢያልፍም ከቦይንግ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ቀጥሏል።
ግንኙነቱ አውሮፕላኖችን ከመግዛት ያለፈ ነው የሚሉት አቶ መስፍን፣ ከእነዚህም መካከል አንዳንድ የአውሮፕላን አካላት “በኢትዮጵያ ተመርተው ቦይንግ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ሲያመርት የሚጠቀምባቸው ጭምር በመሆናቸው ግንኙነታችን በጣም ጠንካራ ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ከ78 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ150 በላይ የዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት ሲሆን 100 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ማዘዙንም ድረገጹ ላይ ያስቀመጠው መረጃ ያመለክታል።
ወደ 142 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች የሚበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከእነዚህ ውስጥ 70ዎቹ የአፍሪካ አገራት ከተሞች ናቸው።
የኢትየጵያ አየር መንገድ ለተከታታይ ስድስት ዓመታት አፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ ከመባል ባለፈ በርካታ ሽልማቶችን ለማግኘት በቅቷል።