ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

ከ 5 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ባካሄደው አጀንዳ ማሰባሰብ ከፋኖ ውጪ ያለ ታጣቂ ቡድን ለውይይት እና ምላሽ ለማግኘት አጀንዳ ማስገባቱን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ታጣቂ ቡድኑ ወደ ትጥቅ ትግል ያስገቡትን ምክንያቶች የምክክር አጀንዳ ጥያቄዎች በማድረግ ወደ ምክክር ኮሚሽኑ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል ከመጋቢት 27 አስከ ሚያዝያ 4/2017 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የማኅበረሰብ ወኪሎች እና የተለያዩ ተቋማት እንዲሁም የማኅበራት ተወካዮች መሳተፋቸው ተገልጿል።

በዚህ ሂደት ላይ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀስ አንድ ታጣቂ ቡድን ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጥያቄዎቹን የያዘ አጀንዳ ማስገባቱን ሰብሳቢው ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ተናግረዋል።

ሰብሳቢው በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው ያሉት ይህ ቡድን ያሉት ጥያቄዎች በአጀንዳነት ለኮሚሽኑ ያቀረበው “በትክክል ውይይት ተደርጎ መግባባት የሚደረስበት ከሆነ የትጥቅ ትግሉን ማቆም ይቻላል በሚል እምነት” መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር መስፍን አክለውም ታጣቂ ቡድኑ ያቀረበው አጀንዳ “በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ ሊጠየቁ የሚገባቸውን ጥያቄ የያዘ” መሆኑን ጠቁመው በታጣቂ ቡድኑ የቀረበውን አጀንዳ አሁን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ታጣቂ ቡድኑ በርካታ ታጣቂዎች ያሉት ነው ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው “የፋኖ ቡድን አካል” አለመሆኑን ተናግርዋል።

Skip podcast promotion and continue reading

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

የቢቢሲ አማርኛ ዋትስአፕ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት

ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!

End of podcast promotion

ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀናዳ አስገባ የተባለው ታጣቂ ቡድኑ ስለ ኮሚሽኑ ለማወቅ በተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን የገለጹት ሰብሳቢው፣ “በመጨረሻ [በኮሚሽኑ ላይ] እምነት ስላደረባቸው በዚያ ምክንያት አጀንዳዎቻቸውን ልከዋል” ብለዋል።

በአማራ ክልል ውስጥ ከፋኖ ውጪ ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ቡድኖች አሉ ያሉት ሰብሳቢው፣ ለኮሚሽኑ የምክክር አጀንዳ ያስገባው ታጣቂ ቡድን “ፋኖ አለመሆኑን በእርግጠኝነት” እንደሚናገሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከቢቢሲ የታጣቂ ቡድኑን ማንነት ተጠይቀው ፈቃደኛ ያልሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ምክንያታቸውም “ማንነታቸውን መግለጽ የምንችለው ከእነርሱ ይሁንታን ስናገኝ ነው” ብለዋል።

ነገር ግን ታጣቂ ቡድኑ ማን መሆኑ እንዳይገለጽ አለመጠየቁን የጠቀሱት ሰብሳቢው፣ እነርሱ ስለማንነታቸው መግለጽ ከፈለጉ ግን ማድረግ አንደሚችሉ እንደተነገራቸው አስረድተዋል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከአማራ ክልል በርካታ አጀንዳዎችን ማሰባሰቡን የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ከክልሉ አሁንም የተለያዩ ወገኖች አጀንዳቸውን እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

አጀንዳ የማሰባሰቡብ ሂደት ከትግራይ ክልል፣ ከዲያስፖራ እና ከፌደራል አሰባስበው ካጠናቀቁ እና በቅደም ተከተል ካስቀመጡ በኋላ ይፋ እንደሚያደርጉ የተናገሩት ሰብሳቢው፣ ከዚያ በፊት ግን ማን ምን ዓይነት አጀንዳ አንዳቀረበ እንደማይገልጹ አመልክተዋል።

ምክክር ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ባካሄዳቸው የአጀንዳ ማሰባሰብ ማንነትን፣ አስተዳደር እና ወሰንን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ፍትህን፣ ሕገ መንግሥትን፣ ሰንደቅ ዓላማን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን ማሰባሰቡን ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለቢቢሲ ተናግርዋል።

የአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበ ሲሆን፣ እስካሁን በይፋ የሚታወቅ በሁለቱ ወገኖች በኩል ግጭቱን በንግግር ለማስቆም የሚያስችል እንቅስቃሴ የለም።