በአፍጋኒስታን የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ካሜራዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።
የምስሉ መግለጫ,በአፍጋኒስታን የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ካሜራዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ከ 9 ሰአት በፊት

ሰዎች ባጨናነቁት የቁጥጥር ማዕከል ዙሪያው በቴሌቭዥን መስኮቶች ተከቧል።

የታሊባን ፖሊስ የሚሊዮኖችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚከታተልበት 90 ሺህ የመከታተያ ካሜራዎች (ሲሲቲቪ) ተክሎ በኩራት ያሳያል።

የታሊባን ፖሊስ አዛዥ ቃል አቀባይ ካሊድ ዛድራን ወደ አንደኛው የቴሌቭዥን መስኮት እየጠቆሙ “መላው የካቡል ከተማን ከዚህ ሆነን እንከታተላለን” ይላሉ።

የታሊባን ባለሥልጣናት በካሜራ የሚያደርጉት ክትትል ወንጀልን እንደሚከላከል ቢናገሩም ተቺዎች ደግሞ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ለማደን እና እስላማዊው የታሊባን መንግሥት ለሚያስፈፅመው የሥነ ምግባር ደንብ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው።

አዲሱ የታሊባን የቁጥጥር ሥርዓት እንዴት እንደሚሠራ ለማየት ቢቢሲ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ነው።

በቁጥጥር ማዕከሉ ውስጥ የፖሊስ መኮንኖች ተደርድረው ተቀምጠው በሺዎች ከሚቆጠሩ ካሜራዎች በቀጥታ የሚተላለፈውን ተንቀሳቃሽ ምሥል ይመለከታሉ፤ የስድስት ሚሊዮን የካቡል ነዋሪዎችን ሕይወት ይከታተላሉ።

ከመኪኖች የሰሌዳ ቁጥር ጀምሮ የሰዎችን የፊት ገፅታ ሁሉንም እንቅስቃሴ በአንክሮ ይቆጣጠራሉ።

“በአንዳንድ የመኖሪያ ሰፈሮች ሰዎችን በቡድን ተሰባስበው አደንዛዥ እፅ ሲጠቀሙ፣ በወንጀል ሲሳተፉ ወይም አጠራጣሪ ነገሮች ወይም ተጠርጣሪዎችን ስናይ ለአካባቢው ፖሊስ በፍጥነት እናሳውቃለን” ይላሉ ቃል አቀባዩ።

“በአፋጣኝ ስፍራው ላይ ደርሰው ሰዎቹ ለምን እንደተሰበሰቡ ይመረምራሉ” ብለዋል።

በቀድሞው የአገሪቱ መንግሥት ካቡል በየቀኑ በታሊባን እና በእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) በሚባሉ ታጣቂዎች ጥቃቶች ይሰነዘራሉ። ከዚህ ባሻገርም የታዋቂ ሰዎች እገታዎች እና የመኪና ነጠቃ ወንጀሎች ይፈፀማሉ።

እ.አ.አ በ2021 ታሊባን ዳግም ሥልጣን ሲቆጣጠር ወንጀሎችን ለማጥፋት ቃል ገብቷል።

በአፍጋኒስታን መዲና በአስደናቂ ሁኔታ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ካሜራዎች የታሊባን መንግሥት ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር የሚያደርገው እርምጃ ምልክት ነው።

ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት ታሊባን ተመልሶ የሥልጣን መንበሩን ከመቆጣጠሩ በፊት በካቡል 850 ካሜራዎች ብቻ ነበሩ።

የታሊባን መንግሥት ከሦስት ዓመት ወዲህ በተለይም የሴቶችን መብት እና ነፃነት የሚገድቡ ጠንካራ እና ሰፊ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።

የታሊባን መንግሥት እስካሁን ከየትኛውም አገር እውቅና አልተሰጠውም።

ቢቢሲ የተመለከተው በካቡል የሚገኘው የቁጥጥር ማዕከል ሰዎችን በመልካቸው ብቻ በመለየት መከታተል የሚያስችልም ነው።

ጥግ ላይ ያለ አንደኛው የቴሌቭዥን መስኮት በዕድሜ፣ በፆታ እና ፂም ያላቸው አሊያም ጭምብል ማጥለቃቸውን በመለየት ምሥሎችን ይደረድራል።

ቃል አቀባዩ ወደ ተጨናነቀው መንገድ ካሜራውን እያስተካከሉ “በምቹ ቀን በኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሰዎችን ምሥል በማቅረብ ማየት እንችላለን” ይላሉ።

ታሊባን የራሱን ሰዎችንም ይከታተላል።

የአፍጋኒስታን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ካሜራዎቹ “ደኅንነትን ለመጠበቅ፣ የወንጀል መጠንን ለመቀነስ እና ወንጀለኞችን በፍጥነት ለመያዝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል” ይላል።

እ.አ.አ በ2023 እና 2024 ባሉት ጊዜያት የክትትል ካሜራዎች እና ሞተር ሳይክል ቁጥጥር የወንጀል ምጣኔን በ30 በመቶ መቀነሱንም አክሎ ገልጿል።

ይሁን እንጂ ይህን አሃዝ በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አይቻልም።

የታሊባን ፖሊስ አዛዥ ቃል አቀባይ ካሊድ ዛድራን የክትትል ካሜራዎች ወንጀልን ለመቀነስ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ብለዋል።
የምስሉ መግለጫ,የታሊባን ፖሊስ አዛዥ ቃል አቀባይ ካሊድ ዛድራን የክትትል ካሜራዎች ወንጀልን ለመቀነስ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ብለዋል።

የመብት ተሟጋቾች እነማን ክትትል እንደሚደረግባቸው እና ለምን ያህል ጊዜ የሚለው እንደሚያሳስባቸው እየገለፁ ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል “በብሔራዊ ደኅንነት ሽፋን ታሊባን በአፍጋኒስታን ውስጥ ያሉ ሰዎችን በተለይም በአደባባይ የሴቶችን መሠረታዊ መብቶች የሚጥሱ ጨቋኝ ፖሊሲዎችን ለማስፈፀም” ካሜራዎችን ስለመትከሉ ተናግሯል።

ታዳጊ ሴቶች ሁለተኛ ደረጃ እና ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ የማይፈቀድላቸው ሲሆን፤ ሴቶች በበርካታ ሥራዎች ተቀጥረው እንዳይሠሩም እግድ ተጥሎባቸዋል።

ካቡልን በመሰሉ ከተሞች በመንገዶች ሴቶች ሲንቀሳቀሱ ቢታዩም ፊታቸውን የመሸፈን ግዴታ አለባቸው።

የአፍጋኒስታን ሴቶች ካሜራዎቹ ሂጃብ መልበሳቸውን ለመቆጣጠር ይከታተላሉ የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታሊባን ግን ካሜራዎቹን መጠቀም የሚችሉት የከተማዋ ፖሊስ እና አንድ ሚኒስቴር ተቋም እንጂ ሴቶች ሂጃብ መልበሳቸውን የሚቆጣጠረው የታሊባን የሞራል ፖሊስ አይደለም ብሏል።

አዲስ የኮሌጅ ተመራቂ የሆነችው የካቡል ነዋሪ “ብዙ ግለሰቦች፣ የቀድሞ ወታደሮች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ተቃዋሚ ሴቶች በነፃነት ለመንቀሳቀስ ይቸገራሉ፤ በአብዛኛው በፍርሃት ይኖራሉ” ትላለች።

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይት ዋች አፍጋኒስታን በካሜራዎች የሚቀረፁ ምሥሎች እንዴት እንደሚቀመጡ እና ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የሚደነግግ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ሕግ የላትም ብሏል።

በአንፃሩ ፖሊስ መረጃዎች ለሦስት ወራት ብቻ እንደሚቀመጡ የሚናገር ሲሆን፤ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ ካሜራዎቹ የግላዊ መብትን ስጋት ውስጥ የሚጥሉ አይደሉም ይላል።

ካሜራዎቹ ቻይና ሰራሽ ናቸው።

የቁጥጥር ማዕከሉ መሳሪያዎች ከቻይና መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ኩባንያ ስም ተለጥፎባቸዋል።

የካሜራዎቹ ዋጋ ተራ ተረታ አፍጋናውያን ትከሻ ላይ የወደቀ ሲሆን፤ ነዋሪዎች በየመንገዱ ለተገጠሙ ካሜራዎች መዋጮ እንድንከፍል እየተጠየቅን ነው ብለዋል።

በመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ መሠረት 30 ሚሊዮን አፍጋናዊያን እርዳታ የሚሹ ናቸው።

“ሰዎች እየተራቡ ነው። እነዚህ ካሜራዎች ለእነርሱ ምን ይፈይዳሉ?” በማለት ዜጎች ይጠይቃሉ።