ጋዛ

ከ 8 ሰአት በፊት

በሐማስ እና በእስራኤል መካከል አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር ሊደረግ መሆኑን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ፍልስጤማዊ ባለሥልጣን እንዳሉት የኳታር እና የግብፅ አደራዳሪዎች አዲስ የተኩስ አቁም ድርድር እያረቀቁ ነው።

የተኩስ አቁሙ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት የሚዘልቅ እንደሚሆን ምንጩ ገልጸዋል። ሁሉም እስራኤላውያን ታጋቾች ተለቀው በምላሹ በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን ይለቀቃሉ።

ጦርነቱ በይፋ ቆሞ የእስራኤል ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ከጋዛ እንዲወጡም ይደረጋል።

በጉዳዩ ላይ ምክክር ለማድረግ የሐማስ ልዑካን ወደ ካይሮ እንደሚሄዱ ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከአንድ ወር በፊት መፍረሱ ይታወሳል። ስምምነቱ ለመፍረሱ ሁለቱ ወገኖች አንዳቸው ሌላውን ሲከሱ፣ እስራኤል ጋዛ ላይ ጥቃት መፈጸም ቀጥላለች።

ነገር ግን አዲስ ድርድር ሊደረግ ስለመሆኑ እስካሁን ከእስራኤል በኩል የተባለ ነገር የለም።

የሐማስ የፖለቲካ ክንፍ ኃላፊ ሞሐመድ ዳርዊሽ እና ዋና ተደራዳሪው ኻሊል አል-ሀያ በካይሮ ለድርድር እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

ሐማስ የታጠቀውን መሣሪያ ፈትቶ በምላሹ የስድስት ሳምንታት የተኩስ አቁም እንዲደረግ እስራኤል ከሰሞኑ ያቀረበችው ሐሳብ በሐማስ በኩል ውድቅ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐማስ ካልከሰመ እና ታጋቾች በአጠቃላይ ካልተለቀቁ ጦርነቱን እንደማያቆሙ ተናግረዋል።

ሐማስ በበኩሉ ጦርነቱን እስራኤል ስታቆም ታጋቾች እንደሚለቀቁ አስታውቋል።

ሐማስ የጋዛን አስተዳደር ለፍልስጤም ባለሥልጣናት ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“አገራዊ እና ቀጣናዊ” የጋዛ አስተዳደርን በዌስት ባንክ ላለው የፍልስጤም አመራር ሊያስረክቡ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኔታንያሁ ግን ጋዛ በፍልስጤም አስተዳደር ሥር እንደማትሆን ተናግረዋል። ጋዛ ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ በሐማስ ሥር እየተዳደች ትገኛለች።

የቢቢሲ ምንጭ እንዳሉት አዲሱ ድርድር ስኬታማ ይሆናል ለማለት ጊዜው ገና ቢሆንም በዚህ ድርድር ሐማስ “ባልተጠበቀ ሁኔታ አቋሙ መለሳለሱን” ገልጸዋል።

ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1,200 ሰዎችን ሲገድል፣ ይህንን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ባለው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከ51 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መግደሏ ተገልጿል።