የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን

ከ 43 ደቂቃዎች በፊት

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬኑ መሪ ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር የሁለትዮሽ ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ፍንጭ ሰጡ።

ፑቲን ይህን ያሉት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ፕሬዚደንቱ ለሩሲያ መንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰኞ ዕለት ሲናገሩ ሩሲያ ” ሁልጊዜም ማንኛውንም ሰላም ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን በበጎ ነው የምትመለከተው። የኪዬቭ መንግሥት ተወካዮችም ተመሳሳይ ስሜት እንደሚኖራቸው ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

የፑቲን አስተያየት ሲቪል ኢላማዎች ላይ ጥቃት አለመፈፀምን በተመለከተ ከዩክሬን ጋር ቀጥተኛ የሆነ ንግግር ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት መኖሩን እንደሚያመለክትም የክሬሚሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል።

ዘሌንስኪ ለፑቲን አስተያየት በቀጥታ ምላሽ አልሰጡም።ሆኖም ዩክሬን የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት ለሚያረጋግጥ ማንኛውም ንግግር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ 2022 በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከከፈተች በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል ቀጥተኛ ድርድር ተካሂዶ አያውቅም።

ፕሬዚደንት ፑቲን፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ጨምሮ ሲቪል ኢላማዎች ላይ ጥቃት ስላለመፈፀም ውይይት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሲገልጹ፣ በዩክሬን በኩልም ድርድር እና ውይይት ለማካሄድ ፍላጎት እንዳለ በማሰብ እንደሆነ ፔስኮቭ ለኢንተርፋክስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ዘሌንስኪ ምሽት ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ሞስኮ በሰላማዊ መሠረተ ልማቶች ላይ የምትፈፅመውን ጥቃት ለማቆም ትስማማ አሊያም አትስማማ እንደሆነ ዩክሬን ግልጽ የሆነ መልስ ትፈልጋለች ብለዋል።

የዩክሬኑ መሪ፣ ፑቲን ለፋሲካ አጭር እና ውስን የሆነ የተኩስ አቁም ማድረጋቸውን ተከትሎም በረዥም ርቀት ተወንጫፊ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች በሲቪል መሠረተ ልማት ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለማባራት ቢያንስ ለ30 ቀን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሃሳብ አቅርበው ነበር።

ሆኖም ፑቲን ክሬሚሊን ሃሳቡን እንደምታጤነው ገልጸው፣ ‘ሲቪል መሠረተ ልማት ላይ ጥቃት እንዳይፈፀም’ የሚለው ሃሳብ መስተካከል አለበት ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሆኖም በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሰሜን ምሥራቅ ከተማ ሱሚይ ከተማ ቸ 35 ሰዎች የተገደሉበትና ከ100 በላይ ሰዎች የተጎዱበትን የሲቪል ሕንጻ ጦራቸው ኢላማ ማድረጉን ፑቲን አምነዋል።

” በሰሚይ ቀጠና በኮንግረንስ ሴንተር በጦራችን ስለተፈፀመው ጥቃት ሁሉም ሰው ያውቃል። የሲቪል መሰረተ ልማት ነው ወይስ አይደለም? ሲቪል መሠረተ ልማት ነው። ሆኖም በኩርስክ ክልል ወንጀል ለፈፀሙት የሽልማት ሥነ ሥርዓት እየተካሄደበት ነበር ” ብለዋል ፕሬዚደንት ፑቲን።

በዚያን ወቅት የሰሚይ ማዕከል ፋሲካን በሚያከብሩ ሰዎች ጎዳናዋ ተጨናንቆ ነበር።

ሆኖም በኮንግረንሱ ህንጻ የሜዳሊያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ እንደነበር ከተዘገበ በኋላም የክልሉ ምክትል መሪ ከሥራቸው ተባረዋል።

ዘሌንስኪ ሰኞ ዕለት በሰጡት አስተያየት ” ዩክሬን ቢያንስ ቢያንስ የሲቪል መሠረተ ልማትን ላለመምታት ያላትን አቋም አቅርባለች፤ ከሞስኮም ግልጽ መልስ እንጠብቃለን። ይህንን እንዴት እንደምናረጋግጥ ለማንኛውም ንግግር ዝግጁ ነን።” ብለዋል።

ዘሌንስኪ ጨምረውም ” ግልጽ የሆነ ፣ ቀላል እና ተጨማጭ የሆነ መንገድ አለ። ይህም በሚሳኤሎች እና ረጅም ርቀት ድሮኖችን የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ማቆም ነው።ይህ የሁሉንም የሲቪል መሠረተ ልማቶች ደኅንነት ያረጋግጣል። እውነተኛ እና ዘላቂ ተኩስ አቁም ማድረግም ሰላም እና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን አለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰኞ ምሽቱት ላይ ሩሲያ በዩክሬን የወደብ ከተማ ኦዴሳ ላይ የድሮን ጥቃት መፈፀሟ ተዘግቧል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንዳሉት በጥቃቱ የመኖሪያ ህንጻ በእሳት በመያያዙ እና በመፈራረሱ ሦስት ሰዎች ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

በሌላ በኩልም ዩክሬን ረቡዕ በለንደን በሚካሄደው ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አገራት ጋር በሚደረግ ውይይት ትሳተፋለች።

የውይይቱ ቀዳሚው አጀንዳ ” ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ ማቆም እንዲደረግ መግፋት” እንደሆነም ዘሌንስኪ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለቱ አገራት ውይይቱን ‘ከባድ’ የሚያደርጉት ከሆነ አሜሪካ በአሸማጋይነት አትሳተፍም ካሉ በኋላ፣በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሩሲያ እና ዩክሬን ተኩስ አቁም ላይ ይደርሳሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።