
ከ 1 ሰአት በፊት
በኢትዮጵያ “ከአስር ሚሊዮን በላይ” ሰዎች በሀገሪቱ “እየጨመረ ላለው ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት” መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
ፕሮግራሙ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያከናውነው ሥራ የሚውል ተጨማሪ ገንዘብ በአስቸኳይ የማያገኝ ከሆነ “ለ3.6 ሚሊዮን” ሰዎች የሚያቀርበው “የነፍስ አድን ምግብ” ድጋፍ “በመጪዎቹ ሳምንታት” እንደሚያቋረጥ አስጠንቅቋል።
በምግብ ዋስትና ላይ የሚሠራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋም የሆነው የዓለም የምግብ ፕሮግራም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ “እየጨመረ የመጣውን ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን” በተመለከተ ስጋቱን የገለጸው ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 14/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።
ተቋሙ ኢትዮጵያ ውስጥ የረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየጨመረ የመጣው ሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። ግጭት፣ ቀጣናዊ አለመረጋጋት እና መፈናቀል ተቋሙ ከጠቀሳቸው ምክንያቶች መካከል ናቸው።
በሀገሪቱ ውስጥ ያለው “ኢኮኖሚያዊ ቀውስ” እና ድርቅ እየጨመረ ለመጣው ረሃብ እና ተመጣጠነ ምግብ እጥረት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። እነዚህ ችግሮች “ሚሊዮኖችን ያለ በቂ የተመጣጠ ምግብ እንዳስቀሩ” የዓለም የምግብ ፕሮግራም ገልጿል።
የተቋሙ መግለጫ፤ “በመላው ኢትዮጵያ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ እና ምግብ እጥረት ተጋልጠዋል” ብሏል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል “ሦስት ሚሊዮን ያህሉ በግጭት እና በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ” እንደሆኑም ጠቅሷል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለበትን ደረጃ “አሳሳቢ” ሲል ጠርቶታል። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያጋጠማቸው “4.4 ሚሊዮን ነፍሰ ጡር እና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ህጻናት ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው” አስታውቋል።
በዓለም የጤና ድርጅት መስፈርት መሠረት በአንድ አካባቢ ከሚገኙ ህጻናት መካከል 15 በመቶው ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጋለጡ ከሆነ በአካባቢው ያለው ሁኔታ “የአደጋ ጊዜ” ተብሎ ይበየናል።
ይህንን ያስታወሰው የዓለም የምግብ ፕሮግራም መግለጫ፤ በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው እጅግ የከሱ ህጻናት ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ “የአደጋ ጊዜ” በሚል ለመበየን ከተቀመጠው የ15 በመቶ ገደብ ያለፈ እንደሆነ ገልጿል።
ይህ ችግር የታየበትን ሶማሌ ክልል በመጪው ግንቦት ይኖራል ተብሎ በሚጠበቀው “ዝቅተኛ ዝናብ” ምክንያት ሌላ የድርቅ ስጋት እንደተጋረጠበትም መግለጫው አሳስቧል።
በሶማሌ ክልል የሚገኙ ቤተሰቦች “በሀገሪቱ ታሪክ ለረጅም ጊዜ በቆየው” እና እ.አ.አ ከ2020 እስከ 2023 በነበረው ድርቅ “አሁንም እየተቸገሩ” መሆኑንም አስታውሷል።
እንደ ሱዳን ባሉ ጎረቤት ሀገራት እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች ለኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት መጨመር ምክንያት እንደሆነም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
- ስለ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ብዙዎች የማያውቋቸው አምስት እውነታዎችከ 4 ሰአት በፊት
- የእርግዝና መከላከያ ክኒን በእርግጥ ሴቶችን የበለጠ እንዲጨነቁ ሊያደርግ ይችላል?ከ 9 ሰአት በፊት
- ሴቶችን ይጨቁናል የሚባለው ታሊባን ሚሊዮኖችን ለመከታተል የዘረጋው የስለላ መረብከ 9 ሰአት በፊት

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በ2025 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እርዳታ ማቅረቡን የገለጸው የዓለም የምግብ ፕሮግራም፤ ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶው ድጋፍ የቀረበው “ለተፈናቀሉ እና የከፋ የምግብ ዋስትና” ችግር ላጋጠማቸው ኢትዮጵያውያን መሆኑን አስታውቋል።
ይሁን እንጂ ተቋሙ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያከናውናቸው የእርዳታ ሥራዎች ላይ ሁለት ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙት ገልጿል። መግለጫው በቀዳሚነት የጠቀሰው ተግዳሮት ከተደራሽነት ጋር የተያያዘ ነው።
በአማራ ክልል ያለው “ግጭት እና የደኅንነት ስጋት” ተቋሙ በክልሉ የሚያከናውናቸውን የሰብአዊ እርዳታ ሥራዎችን ማስተጓጉሉን አስረድቷል። በአማራ ያለው ሁኔታ ተቋሙ “በክልሉ ግማሽ ሚሊዮን ተጎጂ ሰዎችን ለመድረስ ያለውን አቅም ስጋት ውስጥ እንደከተተው” ገልጿል።
“እንደ የመኪና እገታ፣ ስጋቶች እና ዘረፋ ያሉ የወንጀል ድርጊቶች እየጨመሩ እንዲሁም በሠራተኞች ደኅንነት እና የነፍስ አድን ድጋፍ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እየጋረጡ ነው” ሲል ስጋቱን አስታውቋል።
ተቋሙን እንዳጋጠመው የተጠቀሰው ሁለተኛው ተግዳሮት የገንዘብ እጥረት እንደሆነ መግለጫው ያስረዳል። የዓለም የምግብ ድርጅት በኢትዮጵያ ከሚያዝያ እስከ ቀጣዩ ዓመት መስከረም ባሉት ጊዜያት ለሚያከናውናቸው ተግባራት ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ የ222 ሚሊዮን ዶላር እጥረት እንዳጋጠመው ገልጿል።
መግለጫው፤ “እያጋጠመ ባለው አሳሳቢ የገንዘብ እጥረት ምክንያት የድርጅቱ የነፍስ አድን እርዳታ እጅጉን ተስተጓጉሏል” ብሏል።
ተቋሙ “አስቸኳይ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ከሌለ 3.6 ሚሊዮን የኢትዮጵያ እጅጉን ተጋላጭ ሰዎች ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ያገኙ የነበረውን የነፍስ አድን እና የተመጣጠነ ምግብ ድጋፍ በመጪዎቹ ሳምንታት ያጣሉ” ሲልም አስጠንቅቋል።
የዓለም የምግብ ድርጅት ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት “በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለተጎዱ 650 ሺህ ሴቶች እና ህጻናት ያደርግ የነበረውን ህክምና በግንቦት ወር” ለማቋረጥ መገደዱን አስታውቋል። ተቋሙ በዚህ ዓመት ለሁለት ሚሊዮን እናቶች እና ህጻናት የነፍስ አድን ምግብ የማቅረብ ዕቅድ እንደነበረው ገልጿል።
የተቋሙ የእርዳታ አቅርቦት በሀገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችም ላይ ተጽዕኖውን እንደሚያሳርፍ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ተቋሙ ተጨማሪ ገንዘብ የማያገኝ እንዲሁም ስደተኞች ከደቡብ ሱዳን መሸሻቸውን ከቀጠሉ “ለአንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች የሚያቀርበውን የገንዘብ እና የምግብ አቅርቦት ሰኔ ላይ እንደሚያቆም” አስጠንቅቋል።
የዓለም የምግብ ድርጅት በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ለሚገኙ አንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች 60 በመቶ የምግብ ድጋፍ እንዳቀረበ አስታውሷል።
ተቋሙ በኢትዮጵያ እርዳታ ከሚያደርግላቸው 800 ሺህ ስደተኞች መካከል 100 ሺህ ያሉ ሱዳናውያን ናቸው ተብሏል። በደቡብ ሱዳን ሰሜን ምሥራቅ አካባቢ እየጨመረ ያለው የደኅንነት ስጋት ተጨማሪ 10 ሺህ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንዲፈልሱ ምክንያት እንደሆነ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።