
ከ 5 ሰአት በፊት
ከአውሮፓ ውጪ በመመረጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን በመምራት የመጀመሪያው የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በ88 ዓመታቸው አርፈዋል።
ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ያላትን ቤተክርስቲያን ለ12 ዓመታት የመሩት ፖፕ ፍራንሲስ አርጀንቲናውያን ቤተሰቦቻቸው ያወጡላቸው ስም ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ የሚል ነበር። ስለ ጳጳሱ ብዙም የማይታወቁ አንዳንድ እውነታዎችን እነሆ . . .
የምሽት ክለብ ጋርድ ነበሩ
ቤርጎሊዮ በአርጀንቲና ዋና ከተማ በቦነስ አይረስ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኬሚስትሪ ዲፕሎማ በማጠናቀቅ በነገረ መለኮት ዲግሪ አግኝተው ሥነ-ጽሁፍ እና ሥነ ልቦና አስተምረዋል።
በአውሮፓውያኑ 2010 በሰጡት ቃለ ምልልስ 13 ዓመት ሲሆናቸው ሥራ እንዲጀምሩ ያበረታቷቸው ስለነበረ በአንድ የሹራብ ፋብሪካ ውስጥ በጽዳት ሠራተኝነት እንዲቀጠሩ አደረጓቸው።
ከዚያም በኋላ ከጽዳት ሥራው በተጨማሪ በምሽት ክበብ ውስጥ ጋርድ (የጥበቃ ሠራተኛ) ሆነው መሥራታቸውን ሮም ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲናገሩ ብዙዎችን አስደንቀዋል።
በተጨማሪም በአንድ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ ሠርተው ነበር።

የእግር ኳስ አፍቃሪ ነበሩ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በልጅነቱ የሚደግፉት የአካባቢያቸው የቦነስ አይረስ ቡድን የሆነው የሳን ሎሬንዞ ደ አልማግሮ የዕድሜ ልክ ደጋፊ ነበሩ።
በአውሮፓውያን 2014 ሳን ሎሬንዞ የኮፓ ሊበርታዶሬስን የተባለውን የደቡብ አሜሪካ የክለቦች እግር ኳስ ውድድር ላይ እጅግ የተከበረውን ዋንጫ ሲያሸንፍ በክለቡ የ106 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛው ውጤት ነበረ።
ጳጳሱ ለክለቡ ያላቸው ድጋፍ ለድል አድራጊነቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ወይ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ “በጣም ደስተኛ ነኝ፣ ግን አይደለም፣ ይህ ተአምር አይደለም” ብለዋል።
ቡድኑ በዚያው ዓመት የአርጀንቲናን ከፍተኛ ዲቪዚዮን አሸናፊ በመሆን የቡድኑ አባላት ከጀርባው “ፍራንሲስኮ ካምፔዮን” ወይም ሻምፒዮኑ ፍራንሲስ የሚል ጽሁፍ የሰፈረበት የቡድኑን ማሊያን ለጳጳሱ አበርክተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በተጨማሪም ሊዮኔል ሜሲ እና ሟቹ ዲዬጎ ማራዶናን ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን እንዲሁም ስዊድናዊው ኮከብ ተቻዋች ዝላታን ኢብራሂሞቪች እና ጣሊያናዊው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጂ ቡፎን ጋር ተገናኝተዋል።
የጳጳሱ ህልፈት ይፋ ከሆነ በኋላ ለሰኞ ዕለት የታቀደው የነበሩ አራት የጣሊያን ከፍተኛ የእግር ኳስ ሊግ ሴሪኤ ጨዋታዎች ተሰርዘው ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።
- ከምሽት ክበብ ‘ጋርድነት’ እስከ ጵጵስና – የሮማው ሊቃነ-ጳጳስ ፍራንሲስ አስገራሚ የሕይወት መስመር21 ሚያዚያ 2025
- የእርግዝና መከላከያ ክኒን በእርግጥ ሴቶችን የበለጠ እንዲጨነቁ ሊያደርግ ይችላል?ከ 9 ሰአት በፊት
- ከግብፅ ለባለቤታቸው ጉቦ ተቀብለዋል የተባሉት የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ሚስት ጥፋተኛ ተባሉከ 8 ሰአት በፊት

ከሌሎች ጋር መጓዝን ይመርጣሉ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለረጅም ጊዜ አገልግሎታቸውን እና እንቅስቃሴያቸውን ቀላል ያለ በማድረግ ሥነ ምግባራቸው ይታወቃሉ። ለዚህም የመጓጓዣ ምርጫቸው ማሳያ ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ወዲያውኑ ለጳጳስ የተዘጋጀውን ቅንጡ ሊሞዚን ከመጠቀም ይልቅ ከካርዲናሎቻቸው ጋር በአውቶብስ ነበር የሄዱት።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከመሆናቸው በፊት በቦነስ አይረስ በአስቸጋሪ የሕይወት ዘይቤያቸው ይታወቁ የነበሩ ሲሆን ካርዲናል እና ሊቀ ጳጳስ የሆኑትም እዚያው ናቸው።
ፍራንሲስ በአውቶብሶች እና በከተማ የምድር ውስጥ ባቡሮች አዘውትረው መጓዝን የሚመርጡ ሲሆን፣ ወደ ቫቲካን በአውሮፕላን ሲጓዙ በአንደኛ ማዕረግ ሳይሆን በመደበኛው የኢኮኖሚ ክፍል ውስጥ ቦታ ይዘው ነበር የሚሄዱት።
በጵጵስና ዘመናቸውም የቅንጦት መኪናዎችን የማይጠቀሙት ፍራንሲስ ውድ ያልሆኑትን የጣሊያን ስሪት ፎርድ ፎከስ ወይም በአውሮፓውያኑ 2015 አሜሪካን ሲጎበኙ ፊያት 500 ኤል ያሉ ሞዴሎችን በመምረጥ ይታወቃሉ።
ብዙ ጊዜ በጉብኝት ወቅት ሰዎችን ሰላምታ ለመስጠት “ፖፕሞባይል” የተባለውን ግልጽ መኪና ይጠቀም ነበር።
ነገር ግን በእሳቸው እና በተሰበሰቡ ምዕመናን መካከል ጥይት መከላከያ መስታወት ያላቸውን ተሸከርካሪዎች አይወዷቸውም። እንዲህ ያለውን ሁኔታ “በሰርዲን ጣሳ” ውስጥ ያሉ ያህል እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ቀልድ አዋቂ ነበሩ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በተገናኙባቸው ስፍራዎች ሁሉ በቀልድ እና በሳቅ ይታወቃሉ።
በአውሮፓውያኑ 2024 ከ15 አገራት የተውጣጡ ጂሚ ፋሎን፣ ክሪስ ሮክ እና ሁፒ ጎልድበርግን ጨምሮ ከ100 በላይ ኮሜዲያንን በቫቲካን አስተናግደዋል።
ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በየቀኑ “አቤቱ፣ ጌታዬ ሆይ፣ ጥሩ ቀልድ ለዛሬ ስጠኝ” እያሉ ይጸልዩ እንደነበር ለኮሜዲያኑ ተናግረዋል።
ይህም በ16ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ በአገር ክህደት የተገደለው እና በኋላም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ተብሎ የተሰየመው የቶማስ ሞር ጸሎት አካል ነበር።
በወቅቱ ለኮሜዲያኑ የተነበበው ጸሎት እንዲህ ይላል፡- “ቀልድ እንዳገኝ፣ በሕይወት ውስጥ ትንሽ ደስታን እንድገነዘብ እና ከሌሎች ጋር ለመካፈል እንድችል ፀጋውን ስጠኝ” የሚል ነው።
በተጨማሪም “በእርግጥ በአምላክ ላይም መሳቅ ትችላላችሁ። ይህ ደግሞ ማዋረድ አይደለም” በማለት ይህንንም “የምዕመናንን ሃይማኖታዊ ስሜት ሳያስከፋ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል።

ከፍተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታይ አፍርተዋል
በ2018 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በይነመረብን (ኢንትርኔት) “የእግዚአብሔር ስጦታ” ነው በማለት ገልጸውት፣ ነገር ግን “ታላቅ ኃላፊነትን” እንሚጠይቅም አሳስበዋል።
ከሳቸው በፊት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ ጳጳስ ትዊተርን (አሁን ኤክስ) የሚባለውን በአውሮፓውያኑ 2012 ከፍተዋል፣ ነገር ግን የተከታዮቹ ቁጥር ፍራንሲስ ጳጳስ በነበሩበት ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
የጳጳሱ ኤክስ አካውንት በእንግሊዝኛ፣ በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛ፣ በፖርቱጋልኛ፣ በፖላንድኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በአረብኛ እና ላቲን ዘጠኝ ቋንቋዎች መልዕክት የሚያጋራ ሲሆን በአጠቃላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሉት።
የጳጳሱ ኢንስታግራም አካውንት 9.9 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ሲሆን በቅርቡ “አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን” መጠቀም “የሰውን ግንኙነት እንደማይተካ፣ የሰውን ክብር የሚያስከብር እና የዘመናችንን ቀውሶች እንድንጋፈጥ የሚረዳ” በማለት ጸሎት ተጋርቶበታል።
ፖፕ ፍራንሲስ ለመጨረሻ ጊዜ በኤክስ ገጻቸው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ከህልፈታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የፋሲካ ዕለት ነበር።
በመልዕክታቸውም “ክርስቶስ ተነሥቷል! እነዚህ ቃላት የመኖራችንን አጠቃላይ ትርጉም ይይዛሉ፣ ምክንያቱም እኛ የተፈጠርነው ለሕይወት እንጂ ለሞት አይደለም” ብለው ነበር።
