
23 ሚያዚያ 2025, 06:58 EAT
ቫቲካን እንደምትለው በመላው ዓለም 1.4 ቢሊዮን ካቶሊኮች ያሉ ሲሆን፣ ይህም ከአጠቃላይ የዓለም ሕዝብ 17 በመቶውን ይይዛል።
የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በአውሮፓውያኑ 2024 እስያን ሲጎበኙ በምሥራቅ ቲሞር የሚኖሩ ሰዎች በአጠቃላይ አደባባይ ወጥተው ነበር የተቀበሏቸው።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኪንሻሳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
እነዚህ የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመላው ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎች ናቸው።
ሊቀ ጳጳሱ ከቤተ ክርስቲያኑ ባሻገር ቫቲካንንም ያስተዳድራሉ። ሆሊ ሲ (መንበረ ጵጵስና) የሚባለው ይህ ሥፍራ በዓለም አቀፍ ሕግ እንደ ሉዓላዊ ግዛት ነው የሚቆጠረው።
ከ184 አገራት እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያደርጋሉ። በተባበሩት መንግሥታት ድምጽ መስጠት ባይችሉም የቋሚ ታዛቢነት ሚናም አላቸው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውይይቶች ላይ በመሳተፍ አቅጣጫ ማስያዝ የሚችሉበት አቅም ይሰጣቸዋል።
በ2015 የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ሲፈረም ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ በቂ ትኩረት አልሰጡም ብለው ተችተዋል።
አገራት ምድርን ለማትረፍ ጥረት እያደረጉ እንዳልሆነ እና “በትዕቢት የተሞላ ችላ ባይነት” እንዳሳዩ ተናግረው ነበር።
- ከምሽት ክበብ ‘ጋርድነት’ እስከ ጵጵስና – የሮማው ሊቃነ-ጳጳስ ፍራንሲስ አስገራሚ የሕይወት መስመር21 ሚያዚያ 2025
- ስለ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ብዙዎች የማያውቋቸው አምስት እውነታዎች22 ሚያዚያ 2025
- የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ አረፉ21 ሚያዚያ 2025
የሚያደርጉት ንግግርም በተለይም በደቡባዊ የዓለም ክፍል ላሉ አገራት ጠቃሚ እንደሆነ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል።
በ2024 የአየር ንብረት ለውጥ ውይይት በመንግሥታቱ ድርጅት ሲካሄድ የሴቶች መብት ጉዳይ እንዳይነሳ ሆሊ ሲ ማገዱ ይታወሳል።
ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች እና ከተሻጋሪ ፆታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አለመግባባት ስለተፈጠረ ነበር የሴቶች መብት ርዕሰ ጉዳይ እንዳይነሳ ያገዱት።
የተባበሩት መንግሥታት ሊወያይ አቅዶ የነበረው በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ ሴቶችን በገንዘብ መደገፍ የሚቻልበትን መንገድ ነበር።
ቫቲካን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሩሲያ፣ ኢራን እና ግብፅ ከተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች እና ከተሻጋሪ ፆታ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ውይይት እንዳይደረግ ጫና አሳድረዋል።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባሳደረችው ጫና ተተችታለች። በዚህም ምን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሆነች ግን ልብ ይሏል።

በአውሮፓውያኑ 2014 በኩባ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲታደስ ለማድረግ ጳጳሱ የተጫወቱት ሚና አይዘነጋም።
የቀድሞው ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማ እና ራውል ካስትሮ በአደባባይ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን አመስግነዋል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ለሁለቱም አገራት ደብዳቤ በመጻፍና በቫቲካን ምሥጢራዊ ውይይት በማዘጋጀት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንዲታደስ አስችለዋል።
አሜሪካ ይሄንን ስምምነት በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ዘመን ውድቅ አድርጋዋለች።
በበርክሌይ ዩኒቨርስቲ የሃይማኖት ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዴቪድ ሆለንባክ እንደሚሉት፣ ባለፉት 25 ዓመታት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሚና ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ ማድረግ ነው።
በ1960ዎቹ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ሲካሄድ ቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮቷን ከልሳለች። ለሰብአዊ መብት እና ለሃይማኖት ነጻነት የምትሰጠው ዋጋ ከፍ ያለ እንደሆነ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
ይህም በከፍተኛ ሁኔታ አቅጣጫ የለወጠ ውሳኔ እንደነበር ፕሮፌሰር ዴቪድ ይናገራሉ።

የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ሳሙኤል ሀንቲንገን እንደሚሉት፣ ዳግማዊ ጆን ፖል ሊቀ ጳጳስ ሳሉ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ ከተሻገሩ አገራት መካከል ሦስት አራተኛው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው የተለወጡት።
“ስፔን እና ፖርቹጋል ከፍራንኮ እና ሳልዛር አስተዳደር ከወጡ በኋላ ወደ ላቲን አሜሪካም ለውጡ ተስፋፍቷል። ካቶሊኮች በብዛት በሚኖሩባቸው ፊሊፒንስ እና ደቡብ ኮሪያም ተጽዕኖው ታይቷል” ይላሉ ፕሮፌሰር ዴቪድ።
ሊቀ ጳጳስ ጆን ፖል ዳግማዊ በትውልድ አገራቸው ፖላንድም ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ጫና በማሳደር ይታወሳሉ።
የሶቪየት ኅብረት እንዲወድቅ እና ዴሞክራሲ እንዲስፋፋ በማስቻልም ስማቸው ይነሳል።
ቫቲካን በሁሉም አገራት መሪዎች ላይ ጫና ታሳድራለች ማለት ግን አይደለም። የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ካቶሊክ ቢሆኑም ስደተኞችን ከአገር እያባረሩ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስም ሳይቀር ስደተኛ ነው በሚል ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለደረሰባቸው ትችት የአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ ሹም የሆኑት ካቶሊኩ ቶም ሆማን “ጳጳሱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ያስተካክሉ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የአማዞን ደን ጥበቃ እንዲደረግለት ማሳሰባቸውን ተከትሎ፣ በ2020 የብራዚል የቀድሞ ፕሬዝደንት ቦልሶናሮ “ጳጳሱ አርጀንቲናዊ ቢሆኑም ፈጣሪ ብራዚላዊ አይደለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች፣ ጽንስ በማቋረጥ እና በሴቶች የሥነ ተዋልዶ መብት ላይ ወግ አጥባቂ አቋም ነው የያዘችው በሚል በአውሮፓ ያላት ድጋፍ ቀንሷል።
ይህ ወግ አጥባቂነት ከ21ኛው ክፍለ ዘመን አይጠበቅም ሲሉም ቫቲካንን ይተቻሉ።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሴቶች ዲያቆን፣ ቄስ እና ሌላም የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው ባለመፍቀድም ይተቻሉ።
በላቲን አሜሪካ አሁንም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጫና ብታሳድርም ከጊዜ ወደ ጊዜ ተጽእኖዋ እየቀነሰ መጥቷል።
ጽንስ ማቋረጥን በላቲን አሜሪካ በመገደብ ቫቲካን ስሟ ይነሳል። ባለፉት 20 ዓመታት ግን ኡራጓይ፣ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲና እና ኮሎምቢያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮትን ችላ በማለት የጽንስ ማቋረጥ ተደራሽነት እንዲስፋፋ አድርገዋል።

በርካታ ካቶሊኮች በሚኖሩባት ብራዚል በቀጣይ አምስት ዓመታት በርካታ ተከታዮች ያሉት ሃይማኖት ሆኖ እንደማይቀጥል ተንታኞች ይገምታሉ።
በቤተ ክርስቲያኗ ቀሳውስት የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች አደባባይ መውጣታቸው ሲቀጥል የቤተ ክርስቲያኗ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትም እየተሸረሸረ ነው።
ሆኖም ግን የትኛውም ሊቀ ጳጳስ በመሪዎች ላይ የሚያሳድሩት ጫና እንዳለ ይቀጥላል። የክርስትና ሰፊው ቅርንጫፍ የሆነውን ሃይማኖት ከመምራት ባሻገር እንደ ሉዓላዊ አስተዳደርም መቀጠላቸው አይቀርም።
በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ተዋጊዎች እግር ላይ መውደቅ፣ በግሪክ ስደተኞች መጠለያ ያሉ ስደተኞችን በማጽናናት እና በሌሎችም ክንውኖች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ሚና ማሳያ ናቸው።