
ከ 8 ሰአት በፊት
በጋዛ የእስራኤል ጥቃት ሞተዋል ተብለው ከተገለፁ ከ51 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መካከል የ3000 ሰዎች ስም ዝርዝር መሰረዙን ተከትሎ በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስትሩ የሟቾችን ቁጥር አሳስቶ አቅርቧል መባሉን አስተባበለ።
በሃማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር 18 ወራትን በዘለቀው ጦርነት ቢያንስ 51 ሺህ 266 ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻል።
ከሟቾች መካከል አንድ ሦስተኛው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት መሆናቸውንም አስታውቋል።
ይሁን እንጂ እስራኤል በፍልስጤም ተቋማት የሚወጣው የሟቾችን ዝርዝር በተደጋጋሚ እንደማትቀበለው የምትገልፅ ሲሆን በዋናነት ቁጥሩ እና የሕዝቡ ልየታው ለሃማስ ፕሮፓጋንዳ እየዋለ ነው ስትል ትከሳለች።
በሀማስ የሚወጣው የሟቾች ቁጥር በመንግሥታቱ ድርጅት ኤጄንሲዎች እና በመገናኛ ብዙኃን በዋቢነትም ይጠቀሳል።
የሟቾች ዝርዝር በግጭቱ የሚገደሉ ንፁኃን እና መሳሪያ የታጠቁ የሃማስ ተዋጊዎችን የማይለይ ሲሆን፤ እስራኤል የሴት እና ሕጻናትን ሞት ያጋንናል የሚል ክስ ታቀርብበታለች።
በቅርብ ጊዜያት በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ሪፖርቶች የቁጥሩን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከተውታል።
ሪፖርቶቹ በግጭቱ ተገደሉ ተብለው ስም ዝርዝራቸው የወጡ ሦስት ሺህ ሰዎች ከተሻሻለው ስም ዝርዝር እንዲወጡ መደረጉን አመልክተዋል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣን አህር አል ዋህዲ ግልፀኝነት መጓደሉን ለቢቢሲ የካዱ ሲሆን፤ “የጤና ሚኒስቴሩ ትክክለኛ መረጃ ከተዓማኒነት ጋር ለማቅረብ የሚሰራ ነው” ሲሉ ደጋግመው ተናግረዋል።
“የጤና ሚኒስቴሩ ትክክለኛ መረጃ ለማቅረብ የሚሰራ ነው” ሲሉ የመረጃውን እውነተኛነት ገልጸዋል።
“እያንዳንዱ የምናጋራው ዝርዝር መረጃ የተጣራ ነው። የጤና ሚኒስቴሩ ስም ዝርዝር ይሰርዛል ብለን መናገር አንችልም። የመሰረዝ ሂደት ሳይሆን የማጣራት እና የማሻሻል ሂደት ነው” ብለዋል።
- በኢትዮጵያ “ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ” መጋለጣቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ22 ሚያዚያ 2025
- ኢትዮጵያዊው ካርዲናል የሚሳተፉበት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ምርጫ እንዴት ይካሄዳል?ከ 9 ሰአት በፊት
- ኤለን መስክ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የሚያሳለፈውን ጊዜ ሊቀንስ ነውከ 8 ሰአት በፊት
በጦርነቱ የመጀመሪያ ወራት የሟቾች ቁጥር የሚታወቀው ወደ ሆስፒታል በመጣ አስከሬን ነበር።
የጤና ባለሞያዎች በተማከለ የኮምፒውተር ስርዓት የሟቾችን ቁጥር ይመዘግባሉ።
ይሁን እንጂ ቀውሱ ሲባባስ እና የጤና ተቋማት ተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስባቸው የምዝገባ ስርዓቱ አስተማማኝነቱ ቀንሷል።
እ.አ.አ ከ2024 ወዲህ የጋዛ ጤና ባለሥልጣናት የሞቱ አሊያም የጠፉ ቤተሰቦችን ማሳወቂያ የኦንላይን ቅፅ አስተዋውቋል።
የጤና ሚኒስቴር የስታትስቲክ ኃላፊ የሆኑት አል ዋህዲ ከሰሞኑን ከይፋዊ የሟቾች ዝርዝር የተሰረዙት ስሞች በኦንላይን ቅፅ ማመልከቻ ከገባ በኋላ ማጣራት በመካሄዱ ነው ብለዋል።
“መዝገቦችን የሚያጣራ የዳኞች ኮሚቴ ተቋቁሟል። ይህም ተአማኒነትን ለማሳካት የመረጃውን እውነተኝነት ለማረጋገጥ ነው” በማለት አስረድተዋል።
በምርመራው መሰረት አንዳንድ ሰዎች በቀጥታ ከጦርነቱ ውጭ በተፈጥሯዊ ሁኔታ ሞተው መገኘታቸውንም ገልፀዋል።
ሌሎች ሰዎች ደግሞ ሞተዋል ተብለው ሪፖርት ከተደረጉ በኋላ በእስራኤል ከታሰሩ በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መሀል ሆነው ተገኝተዋል።
በዚህም መሰረት ከነሀሴ እስከ ሕዳር ባለው ጊዜ ሦስት ሺህ ስሞች ሙሉ በሙሉ ማጣራት እስኪካሄድ ድረስ ከይፋዊ የሟቾች ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ ተደርጓል ብለዋል።
ለእስራኤል ወገንተኛ ለሆኑ ቡድኖች ግን እርምጃው ሆን ተብሎ የተፈፀመ የማጭበርበር ተግባር እንጂ ስህተት ተደርጎ አይታይም።