ኤለን መስክ እና ዶናልድ ትራምፕ

ከ 9 ሰአት በፊት

ኤለን መስክ የቴስላ ትርፍ መቀነሱን ተከትሎ በአሜሪካ ፌደራል መንግሥት ውስጥ የሚያሳልፈውን ጊዜ ለመቀነስ መወሰኑን ገለፀ።

ኤለን መስክ ከሥልጣን የመልቀቅ ዕቅድ እንደሌለው ግን ተናግሯል።

የቴስላ ኃላፊ የሆነው ኤለን መስክ የኩባንያው ትርፍ እና ገቢ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የሚያሳልፈውን ጊዜ በሳምንት ወደ ሁለት ቀናት ለመቀነስ መወሰኑን ገለጿል።

የቴስላ ገቢ በዓመቱ መጀመርያ ሦስት ወራት ላይ ከፍተኛ መቀነስ ማሳየቱ ተገልጿል።

ኤለን መስክ በዋይት ሐውስ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ከጨመረ ወዲህ የኤሌትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።

የኩባንያው ገቢ በ2025 የመጀመሪያ ሦስት ወራት በ20 በመቶ መቀነሱ ተገልጿል።

ይህ የገቢ መቀነስ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በ70 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።

ኩባንያው የድርጅቱ ባለድርሻዎች “የፖለቲካው ስሜት መቀየሩን ተከትሎ” ያለው ፍላጎት ላይ ተጨባጭ የሆነ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ እና የገቢ መቀነሱ ሊቀጥል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ኩባንያው የገጠመው የገቢ መቀነስ የተሰማው በርካታ አሜሪካዊያን ኤለን መስክ በዶናልድ ትራምፕ ውስጥ ያለው ኃላፊነትን በተመለከተ ከፍተኛ ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ ነው።

ኤለን መስክ ዶናልድ ትራምፕ ዳግም እንዲመረጡ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር ኤለን መስክ የትራምፕ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱን ወጪ ለመቀነስ በሚል የመንግሥት ተቀጣሪዎችን በከፍተኛ ቁጥር የሚቀነሰውን የመንግሥት ውጤታማነት መሥርያ ቤት ይመራል።

ኤለን መስክ የሚመራው መሥሪያ ቤት በእንግሊዝኛው ‘ዶጅ’ በሚል ምሕጻር የሚታወቅ ሲሆን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ወጪ መቀነስ እና ሥራቸውን የሚያሳልጡበትን መንገድ የማፈላለግ ሚና ተሰጥቶታል።

መስክ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ “በዶጅ ውስጥ የማሳልፈው ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሰል” ሲል ተናግሯል።

ኤለን መስክ በመንግሥት ጉዳዮች ላይ “ፕሬዝዳንቱ እንድሰራ እስከፈለጉ እና ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ” በሳምንት አንድ ወይንም ሁለት ቀናት ሊያሳልፍ እንደሚችል ተናግሯል።

የመስክ የፖለቲካ ተሳትፎ በመላው ዓለም ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን፣ የኩባንያውን ምርት ላለመጠቀም እስከመወሰን ተደርሷል።

ስለገጠመው ተቃውሞ ሲናገርም ሰዎች “እኔን እንዲሁም ዶጅን ለማጥቃት ስለሚፈልጉ ሊሆን ይችላል” ብሏል።

ነገር ግን በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ያለውን ኃላፊነት “ወሳኝ” ሲል የጠራው መስክ “የመንግሥትን ቢሮዎች መልክ የማስያዙ ሥራ በአብዛኛው ተጠናቅቋል” ብሏል።

በዚህ ሩብ ዓመት ውስጥ ቴስላ 19.3 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ አግኝቷል።

ተንታኞች 21.1 ቢሊዮን ገቢ ያገኛል ብለው ገምተው የነበረ ቢሆንም፣ ያ ባለመሆኑ ገዢዎችን ለማማለል ኩባንያው የዋጋ ቅናሽ አድርጓል።

ኩባንያው ዶናልድ ትራምፕ ቻይና ላይ የጣሉት ታሪፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጎዳውም አስታውቋል።

ምንም እንኳ ቴስላ መኪናዎቹን አሜሪካ ውስጥ ገጣጥሞ የሚሸጥ ቢሆንም በርካታ የመኪናው ክፍሎች የሚመረቱት ቻይና ውስጥ ነው።

ኩባንያው “በፍጥነት የሚቀያየረው የንግድ ፖሊሲ” የአቅርቦት ሰንሰለቱን እንደሚጎዳ እና የዋጋ ጭማሪ እንዲኖርም እንደሚያደርግ ተናግሯል።

“ይህ ለውጥ ካለው ፖለቲካዊ ስሜት ጋር ተያይዞ ምርቶቻችን ላይ የሚኖር ፍላጎት ላይ በሚቀጥለው ሩብ ዓመት ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል” ሲል አስታውቋል።

መስክ ንግድን በሚመለከት ከትራምፕ አስተዳደር ኃላፊዎች እንዲሁም ከአማካሪያቸው ፒተር ናቫሮ ጋር አለመግባበት ውስጥ ገብቶ ነበር።