ጳጳሱ

23 ሚያዚያ 2025, 06:56 EAT

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሚመረጡት በመንበር ላይ ያሉት ጳጳስ ሲሞቱ ወይም ከፖፕ ፍራንሲስ በፊት የነበሩት ቤኔዲክት 16ኛ እንዳደረጉት በፈቃዳቸው መንበራቸውን ሲለቁ ነው።

ተተኪው ጳጳስም በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ ያላት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ በመሆን የመሪነቱን መንበር ይረከባሉ።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጳጳሱ በታች ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ካርዲናሎች ከመካከላቸው የቤተ ክርስቲያኗ መሪ ሊሆኑ የሚችሉትን አዲሱን ጳጳስ ይመርጣሉ።

በዓለም ዙሪያ 252 የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካርዲናሎች ያሉ ሲሆን፣ ከመካከላቸው በአዲሱ የጳጳስ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ከ80 ዓመት በታች የሆኑት ብቻ ናቸው።

የእነዚህ በጳጳስ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት ካርዲናሎች ቁጥር አብዛኛውን ጊዜ በ120 የተገደበ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥራቸው 135 ይደርሳል።

ኢትዮጵያዊው ካርዲናል ማን ናቸው?

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል የሆኑት ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሟቹን ፖፕ ፍራንሲስን በመተካት በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏትን ቤተክርስቲያን የሚመሩትን አዲስ ጳጳስ በመምረጥ ከሚሳተፉት መካከል ናቸው።

የአዲስ አበባ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ካርዲናል ብርሃነየሱስ 76 ዓመታቸው ሲሆን፣ በአገር ውስጥ እና በውጪ በከፍተኛ ደረጃ መንፈሳዊ ትምህርትን ተከታትለዋል።

በአውሮፓውያኑ 1976 በኢትዮጵያ ውስጥ የቅስና ማዕረግን ተቀብለው ከሦስት ዓመት በኋላ ለአንድ ዓመት በወታደራዊው መንግሥት ታስረው ቆይተዋል።

ከእስር ከወጡ በኋላ ወደ ሮም አቅንተው በመንፈሳዊ ሥራ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፤ ተጨማሪ ትምህርትም ተከታትለዋል።

ከጣሊያን ተመልሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እና የመንፈሳዊ የሥራ ዘርፎች በማገልገል የቤተክርስቲያኗ መሪ እስከመሆን ደርሰዋል።

ከአስር ዓመት በፊት ፖፕ ፍራንሲስ ወደ ጵጵስናው መንበር ከመጡ በኋላ በርከት ያሉ ካርዲናሎችን ከአፍሪካ እና ከእስያ አገራት በሾሙበት ጊዜ ብርሃነየሱስ ሱራፌልም በአውሮፓውያኑ የካቲት 15/2015 በሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ካርዲናል ሆነው ተሾመዋል።

በዚህም ምክንያት ካርዲናል ብርሃነየሱስ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመላው ዓለም ካሏት 252 ካርዲናሎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ፖፕ ፍራንሲስን የሚተኩትን አዲሱን ጳጳስ ከሚመርጡት 135 ካርዲናሎች አንዱ ይሆናሉ።

በአውሮፓውያኑ 2005 የዳግማዊ ጆን ፖል ተተኪን ለመምረጥ ካርዲናሎች ወደ ምሥጢራዊው የምርጫ ቦታ ሲገቡ
የምስሉ መግለጫ,በአውሮፓውያኑ 2005 የዳግማዊ ጆን ፖል ተተኪን ለመምረጥ ካርዲናሎች ወደ ምሥጢራዊው የምርጫ ቦታ ሲገቡ

ካርዲናሎች አዲስ ጳጳስ እንዴት ይመርጣሉ?

ለቤተ ክርስቲያኗ አዲስ ጳጳስ መምረጥ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉም ካርዲናሎች ሮም ውስጥ ወደምትገኘው ቫቲካን ተጠርተው ፓፓል ኮንክሌቭ በሚባለው ስፍራ ተነጥለው ስብሰባ ያካሂዳሉ።

ይህ ጳጳስ የመምረጥ ሂደት ከሞላ ጎደል ለውጥ ሳይደረግበት ለ800 ዓመታት ያህል ሲተገበር የቆየ ነው።

ካርዲናሎቹ በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ (ክርስቲያናዊ የአምልኮ ሥርዓት) ያደርጋሉ። ከዚያም በቫቲካን ሲስቲን ቤተ መቅደስ ውስጥ ይሰበሰባሉ።

በመቀጠልም አዲስ ጳጳስ የሚመረጥበት ሂደት መጀመሩ ከተገለጸ በኋላ፣ ሁሉም ካርዲናሎች አዲስ ጳጳስ እስኪመረጥ ድረስ ከቫቲካን ሳይወጡ በአንድ ስፍራ ይቆያሉ።

በምርጫው የሚሳተፉት ካርዲናሎች በዝግ በሚካሄደው ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ቀዳሚ ድምጽ የማግኘት አማራጭ አላቸው።

ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ ለሊቃነ ጳጳሳነት የሚወዳደሩት ዕጩዎች ብዛት ወደ አንድ እስኪደርስ ድረስ በየጠዋቱ ሁለት ምርጫዎችን፣ ከሰዓት በኋላም ሁለት ድምጽ የመስጠት ሂደቶችን በቤተ መቅደስ ውስጥ ያካሂዳሉ።

በድምጽ መስጠት ሂደቱ እያንዳንዱ ካርዲናል መራጭ የሚመርጠውን ዕጩ ስም ስር “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አድርጌ መርጫለሁ” በማለት በድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ይጻፋሉ።

ሂደቱን ምሥጢራዊ ለማድረግም ካርዲናሎቹ በተለመደ የእጅ ጽሑፍ ስልታቸው እንዳይጠቀሙ ይደረጋል።

በሁለተኛው ቀን መጨረሻ ላይ ግልጽ በሆነ ልዩነት የተመረጠ ካርዲናል ከሌለ በሦስተኛው ቀን ምንም ድምጽ ሳይሰጥ ለጸሎት እና ለማሰላሰል ይውላል።

ከዚያ በኋላም ድምጽ መስጠት እንደተለመደው ይቀጥላል።

አንድ ዕጩ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ለመመረጥ ከመራጮቹ ካርዲናሎች የሁለት ሦስተኛውን ድምጽ ማግኘት ያስፈልገዋል።

በዚህ ሂደት ከዕጩዎቹ መካከል አንዱ ከፍተኛውን ድምጽ ማግኘት ካልቻለ ድምጽ መስጠቱ ለበርካታ ቀናት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሳምንታት ሊቀጥል ይችላል።

ካርታ

ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ምን ይከናወናል?

ካርዲናሎቹ የሚሰበሰቡበት ስፍራ ከሁሉም የተነጠለ እና ከቀሪው ዓለም ጋር የማይገናኙበት ነው።

በዚህም ወቅት ቫቲካንን ለቅቀው አይወጡም፣ሬዲዮን አይሰሙም፤ቴሌቪዥን አይመለከቱም፤ ጋዜጦችን አያነቡም ወይም በውጭው ዓለም ከሚገኝ ከማንኛውንም ሰው ጋር በስልክ አይገናኙም።

በስፍራው የቤት ውስጥ ሥራን ከሚያከናውኑ ሠራተኞች፣ ከዶክተሮች እና ንሰሐ ከሚቀበሉ ቀሳውስት በስተቀር ማንም ሰው ካርዲናሎቹ ወዳሉበት እንዲገባ አይፈቀድም።

እነሱም የሂደቱን ምሥጢራዊነት ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል።

በድምጽ መስጠቱ ሂደት መካከል፣ ካርዲናሎቹ (ድምጽ በመስጠት የሚሳተፉት እና በእርጅና ምክንያት የማይመርጡት) በቀረቡት ዕጩዎች ዙሪያ ውይይት በማድረግ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።

ማንም ለመመረጥም ሆነ ሌላውን ለማስመረጥ ቅስቀሳ ማድረግ አይፈቀድለትም።

ቫቲካን ካርዲናሎቹ በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ ናቸው ትላለች። ይህ ቢሆንም ግን ለአንድ ወይም ለሌላ ዕጩ ድጋፍ የማሰባሰብ ሂደት በጣም ፖለቲካዊ ነው ተብሎ ይታሰባል።

በየቀኑ ሁለት ጊዜ ካርዲናሎቹ ለምርጫ ድምጽ በመስጠት የተጠቀሙባቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲቃጠሉ ይደረጋል።

ካርዲናሎቹ ድምጽ ከሚሰጡበት ስፍራ ካለው የጭስ ማውጫ በኩል የተቃጠሉት ወረቀቶች ጭስ ሲወጣ በቫቲካን ተሰብስበው ውጤቱን የሚጠባበቁ ምዕመናን ይመለከታሉ።

ወረቀቶቹ ሲቃጠሉ ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም ስለሚደረግባቸው በጥቁር የተነከሩት የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ጥቁር ጭስ እንዲወጣ ሲያደርጉ በነጭ የተነከሩት ደግሞ ነጭ ጭስ ያወጣሉ።

ይህም ጭሱን ለሚመለከቱ ሰዎች መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው።

ጭሱ ጥቁር ከሆነ በተካሄደው ድምጽ አሰጣጥ ከዕጩዎቹ መካከል ማንም የበላይነት ድምጽ ያገኘ አለመኖሩን ሲያመለክት፣ ነጭ ከሆነ ግን ካርዲናሎቹ አዲስ ጳጳስ መምረጣቸውን ያበስራል።

ካርዲናሎቹ ምሥጢራዊ ምርጫውን ከመጀመራቸው በፊት በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ጸሎት ያደርጋሉ
የምስሉ መግለጫ,ካርዲናሎቹ ምሥጢራዊ ምርጫውን ከመጀመራቸው በፊት በቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ጸሎት ያደርጋሉ

ጳጳሱ ሲመረጡ ምን ይሆናል?

በዕጩነት ከቀረቡት ካርዲናሎች መካከል አንደኛው አስፈላጊውን ድምጽ አግኝተው ከተመረጡ “ይህንን ቀኖናዊ ምርጫ ተቀብለው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሊቀ ጳጳስነት ይቀበላሉ?” ይጠየቃሉ።

ተመራጩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ተብለው ሊጠሩበት የሚፈልጉትን ስም በመምረጥ የጵጵስና ካባ እንዲለብሱ ይደረጋል።

የቀሩት ካርዲናሎችም ለአዲሱ ጳጳስ እጅ ይነሳሉ፤ ሊታዘዟቸውም ቃል ይገባሉ።

ይህንንም ተከትሎ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን በረንዳ ላይ በላቲን ቋንቋ “ጳጳስ አለን” ተብሎ ይታወጃል።

የአዲሱ ሊቃነ ጳጳሳት ስም ይፋ ይሆናል፣ ጳጳሱ ራሳቸውም በአካል ወጥተው ለሕዝቡ ይታያሉ። አዲሱ ጳጳስም አጭር ንግግር አድርገው ለከተማዋ እና ለዓለም የቡራኬ ቃል ያስተላልፋሉ።

በመጨረሻም በምሥጢራዊ ምርጫ ሂደት የእያንዳንዱ የምርጫ ዙር ውጤትን ጳጳሱ እንዲመለከቱ ይደረጋል።

ሰነዶቹ ታሽገው በቫቲካን ቤተ መዛግብት ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርገው ከዚያ በኋላ ሊከፈቱ የሚችሉት በሊቀ ጳጳሱ ትዕዛዝ ብቻ ነው።

ካርዲናሎቹ ከተሰበሰቡበት ስፍራ ካለ ጭስ ማውጫ ነጭ ጭስ ከወጣ አዲስ ጳጳስ የመመረጡ ምልክት ነው
የምስሉ መግለጫ,ካርዲናሎቹ ከተሰበሰቡበት ስፍራ ካለ ጭስ ማውጫ ነጭ ጭስ ከወጣ አዲስ ጳጳስ የመመረጡ ምልክት ነው