
ከ 5 ሰአት በፊት
በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሐሙስ ሚያዝያ 9/2017 ዓ.ም. በትምህርት ቤት ዙሪያ በደረሰ የድሮን ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በዞኑ እናርጅ እናውጋ ወረዳ ገደብ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ የትምህርት ቤት አጥር ለማጠር እና ቤት ለመሥራት ‘ለልማት ሥራ’ የወጡ “ሰላማዊ ሰዎች” በጥቃቱ መገደላቸውን ገልፀዋል።
የአካባቢው አስተዳደር ግን ጥቃቱ በአካባቢው ተሰብስበው በነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች ላይ እንጂ በንፁሃን ነዋሪዎች ላይ አለመፈጸሙን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።
ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ተሰብስበው” በከተማዋ ያለው ገደብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አጥርን እያጠሩ በነበሩ የሰዎች ላይ ነው ጥቃቱ የተፈፀመው።
ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ እንደነበሩ የተናገሩ ሌላ የዓይን እማኝ ወዲያው ጩኸት፣ ግርግር እና ድንጋጤ መፈጠሩን ጠቁመው “የሆነውን አናውቀውም” ሲሉ በቅፅበቱ የነበረውን ሁኔታ ገልፀዋል።
እሳቸውን ጨምሮ ሥራ ላይ የነበሩ ሰዎች ጥቃቱ ወደተፈፀመበት አካባቢ ሲጠጉ “ሰው የሚባል አይለይም” ሲሉ ስለ ጉዳቱ ተናግረዋል።
“እንዳለ በሙሉ ጥቁር ነገር ነው የሆነው። አካባቢው በሙሉ ሰው የሚባል ነገር የለም። ከወደቀው ውስጥ የሚጮህ አለ፤ የሚንከባለል አለ። የተፈጠረው ነገር ይዘገንናል። ሰው ለሆነ እጅግ የሚዘገንን ድርጊት ነው” ብለዋል።
የፈረሰውን የትምህርት ቤቱን አጥር እያጠሩ እያለ ቀኝ እጃቸውን ተመትተው መቁሰላቸውን የተናገሩ ሌላ ነዋሪ “ከባድ ፍንዳታ” መከሰቱን ጠቅሰው “ብዙ ሰው ነው የተጎዳው” ብለዋል።
“ባሕር ዛር የሚቆርጥ፤ ሚስማር የሚመታ አለ፤ ማገር የሚቆርጥ አለ፤ የሚይዝ አለ” ሲሉ ማኅበረሰቡ መሰባሰቡን የገለፁ ሌላ የዓይን እማኝ የሟቾቹን ቁጥር “ብዛት ይኖረዋል” በማለት ገልፀዋል።
አስከሬን ስለማንሳታቸው የተናገሩ ሌላ እማኝ ደግሞ አብዛኛው የጥቃቱ ተጎጂዎች ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀው፤ ሟቾቹ በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው ብለዋል።
- ኢትዮጵያዊው ካርዲናል የሚሳተፉበት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ምርጫ እንዴት ይካሄዳል?23 ሚያዚያ 2025
- የአሜሪካ ድምጽ ወደ ሥራ እንዲመለስ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠከ 7 ሰአት በፊት
- ኤለን መስክ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የሚያሳለፈውን ጊዜ ሊቀንስ ነው23 ሚያዚያ 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ከ24 በላይ ቁስለኞችንም ወደ ሕክምና መወሰዳቸውን የገለፁት እማኞች፤ አብዛኞቹ በከተማዋ ወደሚገኘው ገደብ ጤና ጣቢያ ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
ከ70 በላይ አስከሬን አንስተው በባጃጅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ማመላለሳቸውን የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ፤ ታዳጊዎችን እና ሽማግሌዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 120 እንደሚደርስ ገልፀዋል።
“ከ115 እስከ 120 የሚሆን አስከሬን ነው የተቀበረው። ያልታወቀም ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ድንጋጤ ውስጥ ስለነበርን” ብለዋል።
ሌላ የዓይን እማኝ በበኩላቸው 57 አስከሬን እስከሚነሳ ድረስ እንደነበሩ ጠቁመው የሟቾቹ ቁጥር ከ100 በላይ እንደሚሆን ገምተዋል።
አስከሬኖቹ ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ ሟቾችን መለየት ከባድ እንደነበር የተናገሩት እማኞች በዚህ ምክንያት እና በስጋት እስከ ቀትር 08፡00 ድረስ ገደብ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በጅምላ እንደተቀበሩ ገልፀዋል።
“አሞራ እንዳይበላቸው ቅበሩ ሲባል ማኅበረሰቡ በፍጥነት አምስት የሚሆን መቃብር ውስጥ ነው የቀበራቸው” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
የመንግሥት ኃይሎች ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተከትሎ ስጋት ያደረባቸው አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መሸሸታቸውን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ተጨማሪ ጥቃቶች መፈፀማቸውንም ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡ ከተረጋጋ በኋላ ለሟቾቹ ድንኳን እንደተጣለ እና ከቀናት በኋላ በአካባቢው “ፍራጅ” የሚባለው ማስተዛዘኛ መርሃ ግብር እንደተደረገም ነዋሪዎች ተናግረዋል።
“ሰሞኑን ሲሸበር ነበር። ሕዝቡ በሙሉ ሽብር ላይ ነው ያለው” ሲሉ ዳግም የድሮን ጥቃት ይደርሳል በሚል የፋሲካ በዓልን በስጋት ማሳለፋቸውን “በዓል የሚባል ነገር የለም” ብለዋል።
“ከባድ ሐዘን ውስጥ ነው ያለው። በዓል ምንም አይመስልም ነበር። ለበዓል ከከተማ የሚመጡ ልጆች አልመጡም” ሲሉ አካባቢው በሐዘን ድባብ ውስጥ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግጭት በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከተማዋ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሆነች ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ጥቃቱ ሲፈፀም ግን የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋ ውስጥ እንዳልነበሩ እና በአካባቢው ግጭት እንዳልነበረ ጠቁመዋል።
ታጣቂዎቹ “አንዳንድ ሥራ ለመሥራት ካልመጡ በቀር ከተማው ውስጥ አይታዩም” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
ነጋዴ እንደሆኑ የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ ሟቾቹ ንፁሃን ስለመሆናቸው ሲናገሩ “በርካቶቹን በንግድ ሥራቸው” የሚያውቋቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
“የፋኖ አባላት ቢሆኑ [አስከሬን ሲነሳ] ታጣቂ እናገኝ ነበር። ፋኖዎችን እና ማኅበረሰቡን [ለይተን] እናውቃቸዋለን። [ፋኖዎች] በአንድ ላይ ነው የሚንቀሳቀሱት” ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።
ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው “የተሰበሰው አጥር የሚያጥረው እና ቤት የሚሠራው ሰው በቀረፃው [የድሮን ቅኝት] የፋኖ ስብስብ ነው ተብሎ ታስቦ ይሁን ያወቅነው ነገር የለም። . . .ምንአልባት ሲሰበሰብ ፋኖ ነው ተብሎ ታስቦ [ይሆናል] እንደዚያ ነው እኛ የተረዳነው” ሲሉ ጥቃት ሊፈጸም የቻለበትን ምክንያት ግምታቸውን ገልፀዋል።
የእናርጅ እናውጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ጌቴ ንፁሃን ሰዎች ተገደሉ መባሉን “የጠላት ወሬ” ያሉ ሲሆን፤ እርምጃው “ፅንፈኛ” ያሏቸው የፋኖ ታጣቂዎች ላይ መወሰዱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እዚህ አካባቢ ቁጥሩ በርከት ያለ የኃይል ስብስብ አለ። ሰብስበው ሥልጠና ጭምር [እንደሚሰጡ] መረጃው አለኝ። የትምህርት ቤት አጥር፤ ቤት ሥራ የሚባለው ነገር ማሳመሪያ ነው . . .” በማለት ንፁሃን በፍንጣሪም ቢሆን አልተገደሉም ሲሉ አስተባብለዋል።
የፋኖ ታጣቂዎች በበኩላቸው በወረዳው በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው ገደብ ከተማ አካባቢ ላይ ግን በወቅቱ “ምንም ዓይነት የታጠቀ ኃይል” አልነበረም በማለት በጥቃቱ የተገደለ አባል እንደሌላቸው ተናግረዋል።
አካባቢውን ለሥልጠና እንደማይጠቀሙት የተናገሩት የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢ አቶ አስረስ ማረ ዳምጤ “ሁሉም ግድያው የተፈፀመባቸው ሲቪሊያን ናቸው። አንድም የታጠቀ ኃይል በቦታው ላይ አልነበረም” በማለት ግድያውን ማኅበረሰቡን ከማሸበር ጋር አያይዘውታል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የድሮን ጥቃቱ ላይ ክትትል እያደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።