
ከ 8 ሰአት በፊት
አንድ የአሜሪካ ፌደራል ዳኛ የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ ድምጽ እና የሌሎች በአሜሪካ ድጋፍ የሚሰጣቸው የዜና ማሠራጫዎች ሠራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ እና የሚሰጡ የገንዘብ ድጋፎች በሙሉ እንዲቀጥሉ ትዕዛዝ አስተላለፉ።
ዳኛው የአሜሪካ ድምጽን (ቪኦኤ) እና ሌሎችንም የመገናኛ ብዙኃን ለማፍረስ የተደረገው ጥረት ሕግን እና የአሜሪካን ሕገ መንግሥትን የጣሰ ነው በማለት ወስነዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ትዕዛዝ ተከትሎ ወደ 1,000 የሚጠጉ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከ1,300 በላይ የቪኦኤ ሠራተኞች የግዳጅ እረፍት ተሰጥቷቸው የመገናኛ ብዙኃኑ ሥራ ተቋርጧል።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት፣ ዋይት ሐውስ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቱን “ፀረ-ትራምፕ” እና “አክራሪ” ሲል ይከሰዋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የናዚን ፕሮፓጋንዳ ለመመከት የተቋቋመው ቪኦኤ በዋነኛነት የራዲዮ ሥርጭት አገልግሎት ሲሆን፣ ከዋነኛ የዓለማችን የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መካከል አንዱ ነው።
ቪኦኤ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በትግርኛ ዜና እና ትንታኔዎችን ለኢትዮጵያ አድማጮች ሲያቀርብ ከአርባ ዓመታት በላይ እንደቆየ ይታወቃል።
ጣቢያው እንዲዘጋ ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ በሦስቱ ቋንቋዎች ለኢትዮጵያውያን አድማጮች የሚደርሰው ሥርጭት ከተቋረጠ ከአንድ ወር በላይ ሆኖታል።
በዳኛው ውሳኔ ላይ በሠራተኞቹ እና በበጀት ቅነሳው ምክንያት “ቪኦኤ በ80 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜና እየዘገበ አይደለም” ተብሏል።
ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ሮይስ ላምበርት የትራምፕ አስተዳደር እርምጃ የወሰደው “በሠራተኞች፣ በኮንትራክተሮች፣ በጋዜጠኞች እና በዓለም ዙሪያ የመገናኛ ብዙኃኑን በሚከታተሉ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከግምት ሳያስገባ ነው” ብለዋል።
- ኢትዮጵያዊው ካርዲናል የሚሳተፉበት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ምርጫ እንዴት ይካሄዳል?23 ሚያዚያ 2025
- በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ ፊልሞች ኦስካር ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ተገለፀከ 9 ሰአት በፊት
- ኤለን መስክ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የሚያሳለፈውን ጊዜ ሊቀንስ ነው23 ሚያዚያ 2025
አክለውም የአሜሪካ መንግሥት የአሜሪካ ድምጽ ቋሚ እና ኮንትራት ሠራተኞች ከፕሬዝዳንታዊው ውሳኔው በፊት ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ፣ በራዲዮ ፍሪ ኤዢያ እና ሚድል ኢስት ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክስ ላይም ተመሳሳዩ እንዲደረግ አዘዋል።
ዳኛው በተጨማሪም የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ የዓለም አቀፍ ብሮድካስቲንግ ደንብን እና በጀት የሚመድበውን የአሜሪካን ምክር ቤት ሥልጣንን የሚጋፋ ድርጊት ነው ብለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በአጠቃላይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ከሚፈጽሙት ጥቃት አንጻር በቪኦኤ ላይ ለረጅም ጊዜ ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ ዋነኛ የመገናኛ ብዙኃን ወገንተኛ ናቸው በሚል ሲከሱ ቆይተዋል።
ትራምፕ ባለፈው ጥር ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ የፖለቲካ አጋራቸው የሆኑትን ካሪ ሌክ ቪኦኤን እንዲመሩ ሾመዋቸዋል።
ሌክ ትራምፕ በ2020 ምርጫ በባይደን በተሸነፉበት ጊዜ ምርጫው ተሰርቋል የሚለውን የትራምፕን ሐሰተኛ ክስ ደግፈው ነበር።
መጋቢት ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ድምጽን የሚያስተዳድረው እና በባሕር ማዶ ያሉትን ራዲዮ ፍሪ ዩሮፕ እንዲሁም ራዲዮ ፍሪ ኤዢያን በገንዘብ የሚደግፈው የአሜሪካ መንግሥት መሥሪያቤት ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያ እነዚህን የመገናኛ ብዙኃን “ሕግ በሚፈቅደው ልክ እንዲዘጋ” ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
ውሳኔውን ተከትሎ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተከራካሪ ቡድኖች እና የሙያ ማኅበራት እርምጃው ሕገ ወጥ ነው በሚል ክስ መሥርተው የኒው ዮርክ ዳኛ የፕሬዝዳንቱን ትዕዛዝ በጊዜያዊነት አግደውት ነበር።
አሁን መቀመጫቸውን ዋሽንግተን ያደረጉት የፌደራል ዳኛው ላምበርት በኮንግረስ በጀት የሚመደብለት እና በዓለም ዙሪያ ተዓማኒ ዜና እንዲያርብ በሕግ የተቋቋመውን ቪኦኤን የትራምፕ አስተዳደር ለመዝጋት ሥልጣን የለውም ብለዋል።
ዳኛው የትራምፕ አስተዳደርን ውሳኔ “ግለጽ በዘፈቀደ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም” በማለት የተፈጸመው ጥሰጥ እንዲስተካከል አዘዋል።
የዳኛውን ውሳኔ በተመለከተ ቪኦኤን የሚያስተዳድረው ተቋም እና የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አስተያየት ተጠይቀው ወዲያው ምላሽ አልሰጡም።