April 23, 2025

አዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ ያቋቋመው ካቢኔ “ለአንድ ቡድን ያደላ ነው” በማለት እንደማይቀበሉት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሶስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አስታወቁ። በትግራይ ክልል በሶስት የተከፈሉ የታጠቁ ኃይሎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሳቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊነሳ የሚችልበት እድል እንዳለም ፓርቲዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል። 

ይህን አቋማቸውን እና ስጋታቸውን ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 15፤ 2017 በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የገለጹት፤ ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና)፣  ወድብ ናፅነት ትግራይ (ውናት) እና የብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) የተባሉት ፓርቲዎች ናቸው። ሶስቱ ፓርቲዎች “የተጋሩ ብሔራዊ ደህንነት ቃልኪዳን” የተሰኘ ጥምረት አቋቋመው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ናቸው። 

የፓርቲዎቹ የዛሬ መግለጫ በዋናነት ያተኮረው፤ በሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው አዲሱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባዋቀረው ካቢኔ ላይ ነው። ሌተናል ጄነራል ታደሰ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን የመምራት ስልጣን ከአቶ ጌታቸው ረዳ የተረከቡት፤ ከሁለት ሳምንት በፊት መጋቢት 30 በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ ስነ ስርዓት ነበር።

ዓረና፣ ውናት እና ባይቶና በዛሬው መግለጫቸው፤ ሌተናል ጄነራል ታደሰን ጨምሮ በክልሉ የነበረውን ጊዜያዊ አስተዳደር “በኃይል እንዲገለል ላደረጉ አካላት” ሹመት መሰጠቱ “ተቀባይነት የለውም” ብለዋል። በስልጣን ርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “አቃፊ እና አሳታፊ ይሆናል” ቢባልም፤ አዲሱ ካቢኔ ሲዋቀር ግን ቃል ከተገባው የታቃረነ እንደሆነ ፓርቲዎቹ ገልጸዋል።     

የዓረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ “[ሌተናል] ጄነራል ታደሰ ወደዚህ [ስልጣን] ከመጡ በኋላ ከህወሓት ጽህፈት ቤት አንጃ ጋር በመመካከር፣ ካቢኔው ከህወሓት እና የህወሓት ደጋፊ ከሚባሉ ብቻ በማወቀር፣ ‘አቃፊ እና አሳታፊ ይሆናል’ የተባለው ጊዜያዊ አስተዳደር የአንድ ቡድን ብቻ እንዲሆን አድርገዋል” ሲሉ ተችተዋል። አዲሱ ፕሬዝዳንት የሰጧቸውን የካቢኔ አባልነት ሹመቶች፤ የተለያዩ ፓርቲዎች ተወክለውበት ለተመሰረተው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክር ቤት በተቋቋመበት ደንብ መሰረት አቅርበው አለማጸደቃቸውንም ነቅፈዋል። 

ይህ አካሄድ የትግራይን ችግር ከመፍታት ይልቅ፤ ክልሉን “ወደ በለጠ ችግር የሚወስድ” “አደገኛ አካሄድ” እንደሆነ አቶ ዓምዶም አጽንኦት ሰጥተዋል። ሶስቱ ፓርቲዎች በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ውስጥ ብቸኛ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት የትግራይ ክልል ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታደለ መንግስቱ መታሰራቸውን በመግለጽም እርምጃውን ኮንነዋል። 

አቶ ታደለ የባይቶና ፓርቲን በመወከል የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን ካቢኔ የተቀላቀሉት በአቶ ጌታቸው ረዳ የስልጣን ዘመን ነበር። ሌተናል ጄነራል ታደሰ ካቤኒያቸውን ሲያወቅሩ እንደ እርሳቸው ሁሉ ባይቶናን በመወከል የውሃ እና ኢነርጂ ቢሮን ሲመሩ የቆዩትን አቶ ሞገስ ገብረእግዚያብሔርን ከኃላፊነት አንስተዋል። 

የዛሬውን ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡት የፓርቲ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት የባይቶና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በርሀ “[አቶ] ታደለን ማሰር በካቢኔው የቀረን ብቸኛ የተለየ ድምጽ የሚያሰማ አካል ማፈን ነው” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል። አቶ ታደለ የታሰሩት በመቐለ ከተማ በሚገኘው ሃውልቲ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንደሆነም ገልጸዋል። 

የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊው የታሰሩት፤ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ) “በጦርነቱ ጊዜ የወሰዱትን የመንግስት መኪና ማስመለስ አልቻሉም” በሚል ምክንያት እንደሆነ የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከተወሰደ በኋላ በዛሬው ዕለት በነበረ የችሎት ውሎ፤ አቶ ታደለ ላይ የስድስት ወራት እስራት እንደተፈረደባቸው መረዳቱን ባይቶና ፓርቲ ከጋዜጣዊ መግለጫው መጠናቀቅ በኋላ አስታውቋል። 

ለአቶ ታደለ እስር ምክንያት የሆነው በወ/ሮ ፈትለወርቅ እጅ ይገኛል የተባለው ተሽከርካሪ ዛሬ ማምሻውን በመመለሱ፤ የቢሮ ኃላፊው ከእስር መለቀቃቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ከሰዓት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የአቶ ታደለ እስር ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ እንዲፈቱ ጠይቀው ነበር። 

በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ በትግራይ ክልል በተለያዩ ጎራ ሆነው እየተንቀሳቀሱ ስላሉ ታጣቂ ኃይሎች ጉዳይም ተነስቷል። በትግራይ ክልል ሶስት የተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች እንዳሉ የገለጹት የዓረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም፤ የመጀመሪያዎቹ ራሳቸውን “ከኮር በላይ” ብለው የሚጠሩ እና አንዱን የህወሓት ጎራ የሚደግፉ የጦር አዛዦች እንደሆነ አስረድተዋል።  

ሁለተኛዎቹ የታጠቁ ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ እና “የተከዜ ዘብ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው እንደሆነ አቶ ዓምዶም ገልጸዋል። ሶስተኞቹ የታጠቁ ኃይሎች፤ የክልሉ ወታደራዊ አመራሮች አንዱን የህወሓት ጎራ መወገናቸውን በመቃወም “ነጻ መሬት” ባሉት ስፍራ የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን አክለዋል።

በሶስት የተከፈለው የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ “ትግራይን ክፉኛ የሚጎዳ ነው” ያሉት የዓረና ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር፤ “የታጠቁ ኃይሎች በዚህ እና በዚያ ስላሉ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያጋጥም ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። የታጣቂዎቹን እንቅስቃሴ “አደገኛ አካሄድ” ሲሉ የጠሩት አቶ ዓምዶም፤ የትግራይ ህዝብ እና የዓለም ማህበረሰብ “ተጽዕኖ በመፍጠር” እንዲቆም እንዲያደርግ” አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)