
ከ 4 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ የሰላም ስምምነቱን እየጎዱ ነው በማለት ከሰሱ። ትራምፕ ወቀሳ ያሰሙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ሀገራቸው በሩሲያ ቁጥጥር ስር ለምትገኘው ክሬምያ እውቅና እንደማትሰጥ መናገራቸው ተከትሎ ነው።
ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የሩሲያ እና ዩክሬንን ጦርነት ለማብቃት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ “እጅግ ቅርብ” እንደነበር ተናግረዋል። ነገር ግን ዜሌንስኪ የአሜሪካን የስምምነት ነጥቦች አለመቀበላቸው “ጦርነቱን ከማራዘም በቀር ምንም አያደርግም” ብለዋል።
ከዚህ አስቀድሞ አሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳምት ጄዲ ቫንስ፤ “የግዛት መስመሮችን ባሉበት [. . .] አሁን ላይ በሚገኙበት አቅራቢያ ማቆም” ሲሉ ዋሽንግተን ለስምምነቱ ያላትን ዕቅድ አመልክተው ነበር።
ዩክሬን፤ ሩሲያ እ.አ.አ በ2014 በሕገ ወጥ መንገድ ቆርጣ የወሰደቻትን እና በደቡባዊ የባሕር ሰርጥ አካባቢ የምትገኘውን ክሬምያን አሳልፋ እንደማትሰጥ ለረጅም ጊዜ ስትናገር ቆይታለች።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቫንስ፤ ስምምነቱ ዩክሬን እና ሩሲያ “አሁን ላይ የሚቆጣጠሩትን ግዛት በተወሰነ መልኩ እንዲሰጡ የሚያደርግ” እንደሆነ ገልጸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር እስካሁን ድረስ በስምምነቱ የትኞቹ መሬቶች እንደሚሰጡ በዝርዝር አላሳወቀም።
ትራምፕ አስተዳደራቸው ሩሲያ በክሬምያ ላይ ላላት ሉዐላዊነት እውቅና ይሰጥ እንደሆነ በዋይት ሐውስ ከተገኙ ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ የሚፈልጉት ጦርነቱ ሲቋጭ መመልከት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል።
“በተለየ መልኩ የምወደው የለም። በተለየ መልኩ የምወደው እንዲኖርም አልፈልገም። የምፈልገው ስምምነት ላይ እንዲደረስ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሩሲያ በሕገ ወጥ መንገድ ለተቆጣጠረችው ክሬምያ እውቅና የመስጠትን ዕቅድ መቀበል፤ ለዜሌንስኪ በፖለቲካዊ መንገድ የማይቻል ነገር ነው። ከዚህም በላይ ድንበሮች በኃይል መቀየር የለባቸውም የሚለውን ዓለም አቀፋዊ የድኅረ ጦርነት አሠራርን የሚቃረን ነው።
ዜሌንስኪ፤ ዩክሬን በክሬምያ የባሕር ሰርጥ ላይ ያላትን ጥያቄ እንድትተው የሚቀርቡለትን ምክረ ሀሳቦች በቋሚነት ሲቃወሙ ቆይተዋል።
“በዚህ ጉዳይ ምንም ንግግር የሚደረግበት ነገር የለም። ሕገ መንግሥታችንን የሚጻረር ነው” ብለዋል።
ረቡዕ ምሽት ሩሲያ በተለያዩ የዩክሬን ግዛቶች ላይ የሚሳኤል እና ድሮን ጥቃት መፈጸሟን ዩክሬን አሳውቃለች።
የዋና ከተማዋ ኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮቭ፤ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉ እንዲሁም ህጻናት እና ነፍሰ ጡር ሴትን ጨምሮ 54 ሰዎች እንደተጎዱ ተናግረዋል። የድሮን ስብርባሪዎች እሳት እንዳስነሱ እና በርካታ ሰዎች በመኖሪያ ህንጻ ፍርስራሽ ስር እንደሆኑም ገልጸዋል።
በሰሜናዊ ምሥራቅ በምትገኘው ካኪቭ ከተማም ፍንዳታ መከሰቱ ተዘግቧል።በምሥራቃዊ ዩክሬን በምትገኘው ማርሃኔትስ ከተማ የሩሲያ ድሮን ሠራተኞችን የያዘ አውቶብስ መምታቱን ተከትሎ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።
- በቢሾፍቱ ስለሚገነባው ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ አንዳንድ እውነታዎችከ 5 ሰአት በፊት
- ቻይና ከአሜሪካ ለመግዛት ያዘዘቻቸውን የቦይንግ አውሮፕላኖች እንዲመለሱ አደረገችከ 5 ሰአት በፊት
- ቀጣዩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ከአፍሪካ ሊመረጡ ይችላሉ?ከ 5 ሰአት በፊት

በትራምፕ እና ዜሌንስኪ መካከል እየተደረገ ያለው የቃላት ምልልስ፤ ብዙውን ጊዜ በቋፍ ላይ የሚገኘው የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት አንዱ ማሳያ ነው።
ባለፈው የካቲት ሁለቱ መሪዎች በዋይት ሐውስ በተደረገ ስብሰባ መካረር ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።
ረቡዕ ዕለት ትራምፕ በዋይት ሐውስ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ከዩክሬን ጋር ሲነጻጸር ከሩሲያ ጋር መደራደርን ቀላል ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል።
“ሩሲያ ዝግጁ የሆነች ይመስለኛል” ያሉት ትራምፕ፤ ከሞስኮ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ እንደተቃረቡ እንደሚያምኑ፤ ከዩክሬን ጋር ግን እዚያ ደረጃ ላይ አለመደረሱን ገልጸዋል።
“ከዜሌንስኪ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ቀላል እንደሆነ አስብ ነበር። እስካሁን ግን ከባድ ሆኗል” ብለዋል።
ቅዳሜ ዕለት በሚካሄደው የፖፕ ፍራንሲስ ቀብር ላይ መሪዎች በሚሰባቡበት ወቅት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ጋር የመገናኘት ሃሳብን ክፍት አድርገውታል።
ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳቸውን በሚያድርጉበት ወቅት የዩክሬን እና የሩሲያን ጦርነት በአንድ ቀን ውስጥ እንደሚቋጩት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢቆዩም፤ ሥልጣኑን ከያዙ 100 ቀናት ሊደፍኑ እየተቃረቡ ባሉበት በዚህ ሰዓትም ስምምነት ላይ የመድረስ ጉዳይ የሚጨበጥ አልሆነም።
የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሰክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት “ፕሬዝዳንቱ ተስፋ እየቆረጡ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “ትዕግስታቸው እያለቀ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቫንስ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነት ላይ የማይደርሱ ከሆነ አሜሪካ ሁለቱ ሀገራት እንዲሰማሙ የምታደርገውን ጥረት “ጥላ እንደምትወጣ” በመግለጽ፤ ባለፈው ሳምንት በፕራምፕ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የተሰጠውን አስተያየት አስተጋብተዋል።
የአሜረካ ባለሥልጣናት፤ የሰላም ዲፕሎማሲ በጥሩ በፍጥነት እየሄደ የነበረ በመሆኑ በሞስኮው ንግግር ላይ ለማተኮር ከለንደኑ ስብሰባ ጥለው ወጥተዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ዩክሬን እና አሜሪካ ባለሥልጣናት መካከል በለንደን እየተካሄደ የነበረው ስብሰባ የተኩስ አቁምን ለማሳካት አልሞ የነበረ ቢሆንም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ እና ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ ጥለው መውጣታቸውን ተከትሎ የስብሰባው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ቀንሷል።