
ከ 5 ሰአት በፊት
ቻይና በፕሬዝዳንት ትራምፕ ለተጣለባት ከፍተኛ ታሪፍ አጸፋ ከቦይንግ ለመግዛት አዝዛቸው የነበሩ አውሮፕላኖችን እንዲመለሱ ማድረጓን የአሜሪካው አውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኃላፊ አስታወቁ።
በሁለቱ አገራት መካከል የንግድ ውዝግብ መባባሱን ተከትሎ ለቻይና ተልከው የነበሩ ሁለት የቦይንግ አውሮፕላኖች የተመለሱ ሲሆን፣ ሌላ ሦስተኛ አውሮፕላን እንደሚከተል የቦይንግ ዋና ሥራ አሰፈጻሚ ኬሊ ኦርትበርግ ተናግረዋል።
የግዙፉ አውሮፕላን አምራች ኃላፊ ለሲኤንቢሲ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት 50 አውሮፕላኖችን ለቻይና ለመሸጥ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ገዢዎቹ ግን አውሮፕላኖቹን ለመቀበል ፍላጎት እንደሌላቸው አሳይተዋል።
በፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ የ145 በመቶ ታሪፍ መጣሏን ተከትሎ ቻይና ወደ አገሯ በሚገቡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ የ125 በመቶ ታክስ ጥላለች።
የቻይና የአጸፋ ምላሽ ያሰጋቸው ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ከቻይና ጋር ያለው የንግድ ግንኙነት እንደሚሻሻል ተስፋቸውን ገልጸው፤ የተጣለው ታሪፍ “በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ፣ ነገር ግን ዜሮ እንደማይሆን” ተናግረዋል።
ነገር ግን የቦይንግ ሥራ አስፈጻሚ “ቻይና በተጣለባት ታሪፍ ምክንያት ያዘዘቻቸውን አውሮፕላኖች መቀበል አቁማለች” ሲሉ የትራምፕ ውሳኔ ያስከተለውን ውጤት ገልጸዋል።
- በምሥራቅ ጎጃም በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ23 ሚያዚያ 2025
- የአሜሪካ ድምጽ ወደ ሥራ እንዲመለስ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ23 ሚያዚያ 2025
- በኢትዮጵያ “ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለረሃብ” መጋለጣቸውን የዓለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ22 ሚያዚያ 2025
ቦይንግ ከአሜሪካ ውጪ ላሉ ገበያዎች 70 በመቶ የሚሆኑትን የንግድ አውሮፕላኖች በማቅረብ በአገሪቱ ከፍተኛውን ምርት ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ተቋም ነው።
ለአውሮፕላኖቹ ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት መኖሩን የገለጸው ቦይንግ ተገንብተው ለገበያ ዝግጁ የሆኑትን ቻይና አልቀበልም ያለቻቸውን 41 አውሮፕላኖች ለሌሎች አየር መንገዶች ለመሸጥ የሚያስችለውን አማራጭ እየገመገመ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጸሚው ገልጸዋል።
ኬሊ ኦርትበርግ በአንድ ውይይት ላይ አሜሪካ ከቻይና ጋር ስለገባችበት የንግድ ጦርነትን በተመለከተ ከፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር በተደጋጋሚ እየተነጋገሩ መሆናቸውን እና መግባባት ላይ እንደሚደረስ ተስፋ እንዳላቸው አመልክተዋል።
ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት በዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በተዘጋጀ ጉባኤ ላይ ከቻይና ጋር “ወሳኝ የንግድ ስምምነት” ላይ እንደሚደረስ ተናግረዋል።
የቦይንግ ሥራ አስፈጻሚ እንደገለጹት በአውሮፕላን ምርቶቻቸው ላይ የታሪፍ ጫና የገጠመው ከቻይና ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካ 10 በመቶ አጠቃላይ ታሪፍ በመጣሏ በጃፓን እና በጣሊያን ገበያዎቹ ላይ ተመሳሳይ የገበያ ችግር እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ቦይንግ ባጋጠሙት ተከታታይ ችግሮች እና ሠራተኞቹ በመቱት አድማ ምክንያት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የአውሮፕላኖች ምርቱ ቀንሶ ነበር።
ባለንበት ዓመት ቦይንግ የ737 ማክስ ጄቶቹን ምርት ብዛት በወር 38 ለማድረስ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።