ትራምፕ በድጋሚ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ነው በስማቸው ክሪፕቶከረንሲ የከፈቱት
የምስሉ መግለጫ,ትራምፕ በድጋሚ ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ነው በስማቸው ክሪፕቶከረንሲ የከፈቱት

ከ 3 ሰአት በፊት

ትራምፕ ከወራት በፊት ለገበያ ላቀረቡት ክሪፕቶከረንሲ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ላፈሰሱ ገዢዎች የዕራት ግብዣ እንደሚያዘጋጁ ቃል ከገቡ በኋላ ዋጋው በከፍተኛ ደረጃ አሻቀበ።

የዚህ የፕሬዝዳንቱ ክሪፕቶከረንሲ ድረገጽ “በዓለም ላይ ፍጹም የተለየ ግብዣ” ባለው በዚህ ምናባዊ ገንዘብ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው 220 ኢንቨስተሮች፤ ከግንቦት ወር አጋማሽ በኋላ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በሚደረግ የዕራት ግብዣ ላይ እንሚታደሙ አመልክቷል።

የክሪፕቶ መገበያያ መድረክ የሆነው ‘ኮይንቤዝ’ እንዳለው የዕራት ግብዣ እንደሚኖር ከተነገረ በኋላ የትራምፕ ክሪፕቶከረንሲ ($Trump) ዋጋ በ70 በመቶ ጨምሯል። ነገር ግን ገንዘቡ ለገበያ ይፋ ከተደረገበት ባለፈው ጥር ወር ከነበረው ዋጋ ዝቅ ያለ ነው ብሏል።

ይህ የዲጂታል ገንዘብ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ግንኙነት ካላቸው ከክሪፕቶ ጋር ከተያያዙ በርካታ ሥራዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ትራምፕም ራሳቸውን “የክሪፕቶው ፕሬዝዳንት” እያሉ ይጠራሉ።

ዋሽግንተን ውስጥ በሚገኘው የትራምፕ የጎልፍ ክለብ ውስጥ ከሚካሄደው የዕራት ግብዣ በተጨማሪ ከፍተኛውን ክሪፕቶከረንሲ ለገዙ 25 ኢንቨስተሮች “ፍጹም የተለየ የታዋቂ ሰዎች ግብዣ ከፕሬዝዳንቱ ጋር” እንሚኖር ድረ ገጹ አስታውቋል።

በግብይት ላይ ያለው የትራምፕ ምናባዊ ክሪፕቶከረንሲ በአሁኑ ጊዜ 2.5 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ዋጋ አለው። ምናባዊ ገንዘቡ መጀመሪያ ለገበያ የቀረበው ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት ምርጫውን አሸንፈው ባለፈው ጥር ሥልጣን ከመረከባቸው ከቀናት በፊት ነበር።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ክሪፕቶ ለገበያ ከቀረበ ኋላ በዘርፉ ከተሰማሩ በርካታ ሰዎች ትችት እና ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር።

በተጨማሪም ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ፣ ትራምፕ ሥልጣን በተረከቡበት ዕለት የራቸውን ክሪፕቶከረንሲ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

‘ሜም ኮይንስ’ ተብለው የሚጠሩት እነዚህ የክሪፕቶ ሳንቲሞች ወደፊት አትራፊ ይሆናል ብለው በሚያስቡ ሰዎች ወይም በኢንተርኔት ላይ እየተስፋፋ በመጣው ልምድ ለታዋቂ ሰዎች እና ለሌሎችም ድጋፍ ለማሳየት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ዶናልድ ትራምፕ ከወራት በፊት ወደ ሥልጣን ከተመለሱ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክሪፕቶከረንሲን የሚመለከት አዲስ ሕጎች እና ደንቦችን የሚያዘጋጅ ግብረ ኃይል ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ ወሳኝ የቢትኮይን እንዲሁም ሌሎች ምናባዊ ገንዘቦችን የሚጨምር የዲጂታል ሀብት ክምችት እንዲኖራት ትዕዛዝ ሰጥተዋል።