የጳጳሳት ሥዕል

ከ 5 ሰአት በፊት

ቀጣዩን የሮማ ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ መስፈርቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በፍጥነት እየተስፋፋች ያለችበት አካባቢ ከሆነ በእርግጠኝነት ከአፍሪካ ሊሆን እንደሚችል መተንበይ ይችላል።

ከየትኛውም የዓለም ክፍል በተለየ በአፍሪካ የካቶሊክ እምነቱ ተከታዮች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እያደገ ነው።

እየጨመረ ያለው የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር በመላው ዓለም ካሉ አህጉራት አንጻር ሲወዳደር ከግማሽ በላይ የሚሆነው እድገት የተመዘገበው በአፍሪካ ነው።

ከዚህ ቀደም ከ1500 ዓመት በፊት አፍሪካዊ መሆናቸው የሚታመነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳስ ገላሲያስ ቀዳማዊ ቤተ ክርስቲያኒቱን በርዕሳነ ሊቀ ጳጳስነት አገልግለዋል።

የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በቀጣይነት የሚመራውን አባት የሚመርጡት ካርዲናሎች ሲገናኙ ውሳኔያቸውን ይህ እውነታ ተጽዕኖ ያሳድርበት ይሆን?

ናይጄሪያዊው ካህን አባ ስታን ቹ ኢሎ አመራሩ ዓለም አቀፍ ምዕመኑን የሚያንፀባርቅ መሆን እንዳለበት በመግለጽ “አፍሪካዊ ጳጳስ ቢኖር በጣም ትልቅ ነገር ነው” ይላሉ።

አባ ስታን ቺ ኢሎ ካርዲናሎቹ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲሁም “ተሰሚነት ያለውን ጳጳስ” ሊመርጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“ተግዳሮቱ በቫቲካን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ሹመት ላይ ያለ አፍሪካዊ ካርዲናል የለም፤ ያ እንቅፋት መሆኑ አይቀርም” ይላሉ።

“ጳጳስ ሆነው ለመሾም ብቃት ያላቸው፣ በዓለም የካቶሊክ ማኅበረሰብ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው አፍሪካዊ ካርዲናሎችን የምናስብ ከሆነ መልሱ ምንም የለም የሚል ነው።”

በአውሮፓውያኑ 2013 ለቦታው ከፍተኛ ተፎካካሪ የነበሩትን ጋናዊው ካርዲናል ፒተር ተርክሰን እንዲሁም በ2005 የፖፕ ቤኔዲክት 16ኛ ምርጫን የመሩትን ናይጄሪያዊው ካርዲናል ፍራንሲስ አሪንዜን በመጥቀስ ሁኔታው በተቃራኒ የቆመ መሆኑን ያስረዳሉ።

ፖፕ ፍራንሲስ የሊቀ ጳጳስነት ሹመታቸውን በአውሮፓውያኑ 2013 ሲረከቡ በአፍሪካ የነበሩት ካርዲናሎች ቁጥር 8 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 12 በመቶ ከፍ እንዲል አድርገዋል።

“ፖፕ ፍራንሲስ ለአፍሪካ ያላቸውን ቀናነት ስንመለከት . . . እዚህ አንዴት እንደተደረሰ ብዙዎቻችንን የሚያስገርም ነገር ነው” ይላሉ አባ ቹ ኢሎ።

ፖፕ ፍራንሲስ በጵጵስና ዘመናቸው 10 የአፍሪካ አገራትን የጎበኙ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪም አሳይቷል።

አፍሪካውያን ከዓለም የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቁጥር አንጻር 20 በመቶውን ይይዛሉ። እአአ በ2022 ቁጥራቸው 272 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ በ2023 ወደ 281 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።

በኢንዲያና ኖተርዳም ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት አባ ፓውሊነስ ኢኬቹክዉ ኦዶዞር ጳጳሳት ከመጡበት አህጉር የሚሰጠው ትኩረት ከማይመቻቸው አፍሪካዊ ካቶሊኮች መካከል ናቸው።

በናይጄሪያ ለተወለዱት የካቶሊክ ቄስ ይህ ለውክልና በሚል የሚቀርብ ውትወታ ምቾት የሚነሳ ተግባር ነው።

“ሰዎች አፍሪካውያን የእምነቱ ተከታዮች በዚህን ያህል ቁጥር እያደጉ ስለሆነ ለምን አፍሪካዊ ጳጳስ አይሾምም እያሉ ነው። ከአፍሪካ ወይንም ከአውሮፓ ስለመጣህ ቀዳሚነት ሊሰጥህ የሚገባ ዕጩ መሆን አለብህ ብለው ከሚያስቡት መካከል አይደለሁም” ይላሉ።

“ከየትኛውም አካባቢ መጣህ ልክ ስትመረጥ የሁሉም ጉዳይ ጉዳይህ ይሆናል። አንድ ሃሳብ ብቻ ነው ያለህ፤ ሰዎቹ ከየትኛውም አካባቢ ቢሆኑ፣ ቁጥራቸው ምንም ያህል ቢሆን፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ጉዳይህ በክርስቶስን አምሳል ቤተ ክርስቲያኒቱን መገንባት ነው።”

አክለውም ለጳጳሱ በጣም አስፈላጊው ነገር “የቤተ ክርስቲያኒቷ ሥነ መለኮት የበላይ ጠባቂ መሆን ነው” ብለዋል።

“ጳጳሱ ባሕልን በሚገባ የሚያውቅ መሆን ይኖርበታል” ያሉት ፕሮፌሰር አባ ኦዶዞር ያንንም ተጠቅሞ ለሰዎች አቅጣጫ የሚሰጥ ይሆናል ይላሉ።

በፕሮፌሰሩ አመለካከት በቫቲካን በሥልጣን ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በአፍሪካ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችን የሚያሳስባቸው ነገር በሚመለከት የተሻለ መሥራት ይኖርባቸዋል።

“ለአፍሪካውያን ግድ እንደሌላቸው ወይንም እምነታቸው ከሚጠበቀው ትንሽ ዝቅ ያለ ወይንም የተበረዘ እና ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው የማይገባ” እንደሆነ ተደርጎ እንደሚቆጠር አንደሚሰማቸው ተናግረዋል።

“አፍሪካውያን ጉዳያቸው አጀንዳ መሆን እያለበት እንዳልሆነ ከተሰማቸው፣ ያኔ ሰዎች መጠየቅ ይጀምራሉ። ምናልባት ልንሰማ የምንችለው የራሳችን ሰው እዚያ ሲኖር ነው ማለት ነው ሊሉ ይችላሉ።”

በደቡብ አፍሪካ የካቶሊክ መነኮሳት መስቀል ተሸክመው

ፖፕ ፍራንሲስ ድሆችን እና ግፉዓንን የሚረዱ ተደርገው ስለሚቆጠሩ በአፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ነበራቸው።

ለምሳሌ 55 ሚሊዮን ተከታዮች በሚገኙበት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ዘረፋ በተመለከተ ተቃውመው ተናግረው ነበር።

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳ የተፈጠረውን መከፋፈል ለማስታረቅ የሄዱበት ርቀት ከፍተኛ ሙገሳን አስገኝቶላቸዋል።

ይኹን እንጂ ፖፕ ፍራንሲስ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ በነበራቸው አቋም የተነሳ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የአፍሪካ ጳጳሳት ጳጳሱ ቀሳውስት በ2023 የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጥንዶችን ሊባርኩ ይችላሉ ብለው ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ውድቅ አድርገዋል።

ከዚያ በኋላ ቫቲካን መባረኩ “ግለሰቦቹ የገቡበትን ለማጽደቅ አልያም የሁኔታውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አይደለም” ስትል ማብራሪያ የሰጠች ሲሆን፣ “በበርካታ አገራት ከአጭር ጊዜ የዘለለ የመጋቢነት ስልት የሚጠይቅ ጠንካራ የሆነ የባሕል እንዲሁም ሕጋዊ ሁኔታዎች አሉ” ብላለች።

በአፍሪካ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በሕግ የተከለከለ መሆኑን ተከትሎ በርካታ አፍሪካውያንን የእምነቱ ተከታዮችን በአንድነት እንዲቆሙ አድርጓል።

ቀጣዩን የሊቀ ጳጳስነት ምርጫ በታዛቢነት እንደሚከታተሉ የተገለፁት ሦስት አፍሪካዊ ካርዲናሎች፣ ቱርክሶን፣ የጊኒው ሮበርት ሳራ እንዲሁም የኮንጎው ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖርን ለውጥ ተቃዋሚ ናቸው።

የኮንጎው ካርዲናል “የተመሳሳይ ፆታ አፍሪቃያን ጥምረት ከባሕል ያፈነገጠ እና ከመነሻው ሰይጣናዊ ነው” ይላሉ።

ካርዲናል ሳራ በ2015 ለሲኖዶሱ “ልክ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ናዚ ፋሺዝም እና ኮሙኒዝም እንደነበሩት ሁሉ አሁን ደግሞ የምዕራባዊ ሃሳብ የሆነው የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ጉዳይ፣ ጽንስ ማቋረጥ እንዲሁም እስላማዊ አክራሪነት ማለት ነው።”

ካርዲናል ቱርክሶን ጋና በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ላይ ከበድ ያለ ቅጣት ለመጣል የወሰደችውን እርምጃ ተችተው፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት “በማያሻማ መልኩ ሃጥያት ነው” ብለዋል።

ፓፕ ፍራንሲስ በ2015 በአፍሪካ ጉብኝት ሲያደርጉ

ኦዶዞር ምንም እንኳ አፍሪካዊ ካርዲናሎች ቁጥራቸው ቢጨምርም በቤተክርስትያኒቱ ያላቸው ሥልጣን አነስተኛ መሆኑ ላይ ይስማማሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱም የእምነት አባቶች የቤተክርስትያኒቱ አመራር ወካይ እንዲሆን ፖፕ ፍራንሲስ የሠሩትን ሥራ ይስማሙበታል።

ነገር ግን “በቤተ ክርስቲያኒቱ አሁንም ብዙ የማይወራ ዘረኝነት አለ” ይላሉ ኦዶዞር።

“ያ ምናልባት አንድ አባት ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ተግባራት ቢያከናውን አፍሪካዊ ጳጳስ በመሆኑ ብቻ እንቅፋት ሊሆንበት ይቸላል” ይላሉ።

በአሁኑ ወቅት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን 252 ካርዲናሎች ያሏት ሲሆን፣ የፖፕ ፍራንሲስ ምትክን ለመምረጥ ጉባኤ ሲሰየም ከካርዲናሎቹ መካከል 138ቱ ብቻ ናቸው አዲስ ጳጳስ በመምረጡ ሂደት ድምጽ መስጠት የሚችሉት።

እነዚህ ካርዲናሎች ለድሆች እና ለተጎዱ ወገኖችን የሚያገለግሉ ጳጳስ የመምረጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

ቹ ኢሎ፣ ፖፕ ፍራንሲስ ሲመረጡ እንደነበረው የማይታሰብ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ይገምታሉ።

“እግዚአብሔር ፖፕ ፍራንሲስ የጀመሩትን የሚያስቀጥል መሪ እንዲሰጠን እጸልያለሁ። እንዲሁም እንዲህ ዓይነት ሰው ከአፍሪካ እንዲመጣ እጸልያለሁ።”