April 24, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ
በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ወንዞች ብክለትን ለመከላከል የሚያስችለው ደንብ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለው አንድ ወር ገደማ ጊዜ ውስጥ፤ ደንቡን የተላለፉ ግለሰቦች እና ተቋማት 75.7 ሚሊዮን ብር ቅጣት መቀጣታቸውን የከተማይቱ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ። የደንብ ጥሰቶች ምጣኔ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ64 በመቶ መቀነሱንም ባለስልጣኑ ገልጿል።
ይህን የተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የቅንጅታዊ ስራዎችን በዛሬው ዕለት በገመገመበት መርሃ ግብር ላይ ነው። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በባለስልጣኑ በቀረበ ሪፖርት ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የህገወጥ ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድን ለመከላከል መቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎች ይገኙበታል።
በሪፖርቱ ከተጠቀሱት እርምጃዎች የተወሰኑቱ መሰረት ያደረጉት፤ የአዲስ አበባ “ወንዝና የወንዝ ዳርቻን ስለማልማት እና ከብክለት ለመከላከል” ባለፈው ታህሳስ ወር የወጣውን ደንብ ነው። ከየካቲት ወር ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ይህ ደንብ፤ በመዲናይቱ ያሉ ወንዞችን “አደገኛነት” ባላቸው ደረቅም ይሁን ፈሳሽ ቆሻሻ በሚበክሉ ድርጅቶች ላይ አንድ ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚጥል ነው።

ከመኖሪያ ቤቶች የሽንት ቤት አሊያም ማንኛውንም ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መልቀቅ እስከ 300 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣም በደንቡ ተደንግጓል። በደንቡ የተካተተው ዝቅተኛው ሁለት ሺህ ብር ቅጣት፤ በወንዝ እና በወንዝ ዳርቻ ክልል ውስጥ የሚጸዳዱ ሰዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
በዛሬው መርሃ ግብር ላይ የአፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስታንዳርዳይዜሽን ዝግጅት አገልግሎት አሰጣጥ እና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ቀጸላ፤ ደንቡ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ወዲህ ድንጋጌዎችን የተላለፉ 229 ድርጅቶች እና 179 ግለሰቦች መቀጣታቸውን አስታውቀዋል። ካለፈው የካቲት ወር መጨረሻ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ደንቡን በመተላለፍ ከተቀጡ ድርጅቶቹ እና ግለሰቦቹ የተሰበሰበው የገንዘብ ቅጣት መጠን በድምሩ 75.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አቶ ዳንኤል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው ተቋማቸው ከቅጣት ይልቅ ግንዛቤ ማስጨበጥን እንደሚያስቀድም አስረድተዋል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት የደንብ ጥሰቶች የቀነሱትም፤ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በሰሯቸው “የግንዛቤ መፍጠር” ስራዎች እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የወንዞች ብክለትን፣ የቆሻሻ አወጋገድ እና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ የወጡ አዋጆች እና ደንቦች “በርካታ” መሆናቸውን የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ “በየአይነታቸው እና በየደረጃቸው የየራሳቸው የተጣለ ቅጣት” እንዳላቸው አስረድተዋል። ይሁን እንጂ በወንዞች ዳርቻ ላይ የሚፈጸሙ ብክለቶችን በተመለከተ የሚተገበሩ ቅጣቶች “ሰፊ እና በርከት” ያሉ እንደሆኑ ገልጸዋል።
መስሪያ ቤታቸው በወንዞች እና ዳርቻዎች ላይ የሚፈጸሙ ብክለቶችን የተመለከቱ ቅጣቶችን ተፈጻሚ የሚያደርገው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ጋር በመተባበር እንደሆነ ሻለቃ ዘሪሁን አመልክተዋል። “ቅጣቱ [የሚፈጸመው] የፍሳሽ አይነት ናሙና በመውሰድ፣ ላብራቶሪ በማስገባት፤ ‘ምን አይነት አደጋ ሊያስከትል ይችላል?’ የሚለውን በመረዳት፤ በተጨባጭ የላብራቶሪ ውጤት የሚያስቀጣውን የቅጣት ደረጃ በማስቀመጥ ነው ” ሲሉ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሂደቱን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)