በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በጋዛ ጎዳናዎች ላይ የተካሄደ ሐማስን የሚቃወም ሰልፍ
የምስሉ መግለጫ,በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በጋዛ ጎዳናዎች ላይ የተካሄደ ሐማስን የሚቃወም ሰልፍ

ከ 5 ሰአት በፊት

በጋዛ አውራ ጎዳናዎች ላይ “ሐማስ ጠቅልሎ ይውጣ!” የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች መሰማት ጀምረዋል።

በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ፍልስጤማውያን ተቃዋሚ ሰልፈኞች፣ ሐማስ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እያሰሙ ነው።

ላለፉት 20 ዓመታት ጋዛ ሰርጥን ያስተዳደረው ሐማስ አሁን ሰጥ ለጥ ብለው የሚገዙ ሰዎችን ማግኘት ይቸገራል።

ያቺ ትንሽ በፍርስራሽ የተሞላች ሰርጥ በእስራኤል የጦር ጄቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ስትደበደብ የምትውለው በሐማስ የተነሳ መሆኑን በማንሳት ተቃውሟቸውን ይገልጻሉ።

ግዛቲቱ ባለፉት 70 ዓመታት ዓይታው የማታወቀው ቀውስ ውስጥ የገባችው በሐማስ ታጣቂ ቡድን አመራሮች የተነሳ መሆኑ ቁጣቸውን የበለጠ ጨምሮታል።

“ሐማስ ቆሻሻ ነው” የሚለው መፈክር በፍርስራሽ በተሞላው የጋዛ ጎዳና ላይ የተሰማው በቅርቡ ነው።

ጋዛ ውስጥ የሚኖረው ጠበቃ እና ከዚህ በፊት የፖለቲካ እስረኛ የነበረው ሐማስን በመተቸት የሚታወቀው ሙአሚን አል ናቶር “ዓለም በጋዛ ሰርጥ ባለው ነገር ተታልሏል” ይላል።

አል ናቶር “ዓለም ጋዛ ማለት ሐማስ፤ ሐማስ ማለት ጋዛ መሆኑን ያስባል” በማለት “ሐማስን አልመረጥንም፤ አሁን ደግሞ ሃማስ ጋዛን ለመምራት እና ዕጣ ፈንታውን ከእኛ ጋር ለማስተሳሰር ቆርጦ ተነስቷል፤ ሐማስ ገለል ማለት አለበት” ሲል ተናግሯል።

ሙአሚን አል ናቶር
የምስሉ መግለጫ,ሙአሚን አል ናቶር ሐማስ በጋዛ ሰርጥ ሥልጣን ላይ መቆየት የለበትም ሲል ይናገራል

በጋዛ ሰርጥ ተቃውሞን በአደባባይ መግለጽ የሕይወት ዋጋ ያስከፍላል። ሐማሰ ተቺዎቹን የሚታገስበት አቅም የለውም።

አል ናቶር ግን የፍርሃት ንፋስ በአጠገቡ የሚነፍስ አይመስልም።

በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በዋሺንግተን ፖስት ላይ ቁጣ የተቀላቀለበት ጽሑፉን አስነብቧል።

“ሐማስን መደገፍ ማለት የፍልስጤማውያን ሞትን መደገፍ ማለት ነው። የፍልስጤማውያንን ነጻነት መደገፍ ማለት አይደለም።”

ቢቢሲ እንዲህ ሲናገር ለሕይወቱ አይሰጋ እንደሆን ሲጠይቀው “ያለውን አደጋ ተጋፍጠን መናገር አለብን” ሲል ያለማወላወል ምላሹን ሰጥቷል።

“አሁን 30 ዓመቴ ነው። ሐማስ ይህንን አካባቢ ሲቆጣጠር የ11 ዓመት ታዳጊ ነበርኩ። በሕይወቴ ምን ሠራሁ? ሕይወቴ በጦርነት እና በተባባሰ ግጭት ውስጥ ነው የባከነው” ይላል።

ሐማስ እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 የፖለቲካ ተገዳዳሪዎቹን ፋታህ የተባለውን ፓርቲን በኃይል በማስወገድ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ከእስራኤል ጋር ሦስት ትልልቅ ጦርነቶች እና ሁለት አነስተኛ ግጭቶች አካሂዷል።

“በሐማስ ካለው ጭቆና በተቃራኒ፤ የሰብዓዊነት ድምጻችንን እንድናሰማ ይፈልጋል” ይላል አል ናቶር።

ኦዴይ አል ሩባይ
የምስሉ መግለጫ,የኦዴይ አል ሩባይ ቤተሰቦች ለልጃቸው ግድያ ሐማስን ተጠያቂ ያደርጋሉ

ምንም እንኳ ሐማስ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ቢሆንም ተቃዋሚዎቹን ለመቅጣት ግን ጊዜ አያጣም።

በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ የ22 ዓመቱ ኦዴይ አል ሩባይ በጋዛ ከተማ ከሚገኝ የመጠለያ ጣቢያ በታጠቁ ሰዎች ተወስዷል።

ከሰዓታት በኋላ አስከሬኑ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ተጥሎ ተገኝቷል።

ገለልተኛ የሆነው የፍልስጤም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኦዴይ ከመሞቱ በፊት ድብደባ ተፈጽሞበት ነበር ሲል ገልጿል።

“የመኖር መብትን የጣሰ እና ከሕግ ውጪ የተፈጸመ ግድያ” ሲል ሞቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጿል።

አል ሩባይ በቅርቡ በተካሄደው ፀረ ሐማስ ሰልፍ ላይ ተሳትፏል።

ቤተሰቦቹ ለሞቱ ሐማስን ተጠያቂ አድርገው ፍትህ ጠይቀዋል።

ከመሞቱ ጥቂት ቀድም ብሎ ባሉት ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሠራጨው ተንቀሳቃሽ ምሥል ላይ የሐማስ ታጣቂዎች እየከታተሉት መሆን በመግለጽ ያለውን ፍራቻውን አጋርቷል።

በፍርሃት እያማተረ “ጋዛ የሙታን መንፈስ ከተማ ሆናለች” ብሎ ነበር።

“ወዴት መሄድ እንዳለብኝ ጠፍቶኝ ቆሜያለሁ። ለምን አንደሚከታተሉኝ አላውቅም። አፈራረሱን፤ ውድመትን አመጡብን።”

በቀብሩ ላይ የተገኙ ጥቂት ሰዎች ሞቱን ለመበቀል የዛቱ ሲሆን፣ ሐማስ ጋዛን ለቅቆ ይውጣ ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

አሚን አቤድ ባለፈው በጋ ወር ላይ ሐማስን ተቃውሞ ለመናገር በመድፈሩ ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ገጥሞት ነበር።

ፊታቸውን በጭንብል የሸፈኑ ታጣቂዎች ያለርህራሄ ደብድበውታል። በዚህም የተነሳ በርካታ የሰውነቱ አጥንቶቹ የተሰባበሩ ሲሆን፣ ኩላሊቱ ከጥቅም ውጪ ሆኗል።

አቤድ ሕይወቱ ቢተርፍም ከደረሰበት አሰቃቂ ጉዳት ለመትረፍ ከአገር ውጪ ሄዶ መታከም ነበረበት።

አሚን አቤድ
የምስሉ መግለጫ,ለረዥም ጊዜ ሐማስን በመቃወም የሚታወቀው አሚን አቤድ በታጣቂዎች ከባድ ድብደባ ተፈጽሞበታል

አሁን መኖሪያውን በዱባይ ያደረገው አቤድ፣ በጋዛ በሚደረጉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ላይ ይሳተፋል።

አቤድ የሐማስ አመራሮች ቁጥር እየተመናመነ መሆኑን ያምናል።

“የሐማስ አቅም እየመነመነ ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“አክቲቪስቶች እና ንጹሃን ዜጎችን ዒላማ ያደርጋል፤ ሌሎችን ለማስፈራራት ሲል ይደበድባቸዋል ይገድላቸዋል። ነገር ግን አቅሙ በፊት የነበረውን ያህል አይደለም።”

ባለፈው ወር የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከመፍረሱ በፊት የሐማስ ተዋጊዎች ያላቸውን አቅም እና ተቀባይነት ለማሳየት ይጥሩ ነበር።

አሁን ግን እስራኤል በድጋሚ ያለርህራሄ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ታጣቂዎቹ የተደበቁ ሲሆን፣ የጋዛ ሰላማዊ ነዋሪዎች የጦርነት ዳፋውን እየተጋቱ ይገኛሉ።

ከአንዳንድ በቅርቡ ከተደረጉ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የሚሰማው የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ለዓመት ከስድስት ወር ያለ ማቋረጥ በፈፀመው ጥቃት የተነሳ ለሐማስ ያላቸው ፍራቻ ተሟጥጦ ጠፍቷል።

በቅርቡ በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ጫፍ በምትገኘው ቤይት ላሂያ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዓይን ምስክሮች የአካባቢው ነዋሪዎች የሐማስ ታጣቂዎች ከመንደራቸው ሆነው የትኛውንም ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ አንዳያደርጉ መከልከላቸውን እና መቃወማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሚያዝያ ወር የሐማስ ታጣቂዎች ጃማል አል ማዝናን በተባሉ አዛውንት ቤት ለመግባት ሲሞክሩ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

“ሮኬቶችን እና በቤት ውስጥ የተሠሩ ተወንጫፊዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ለመተኮስ ፈለጉ” ያሉት የዓይን እማኙ “ነገር ግን ተቃወሟቸው” ብለዋል።

ተቃውሞው ወዲያውኑ ተባብሶ ቤተሰቦች እና ዘመዶች አል ማዝናንን በመደገፍ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስም በርካቶች የቆሰሉ ሲሆን፣ ነገር ግን አካባቢውን ለቅቀው ለመሄድ ተገደዋል።

በቅርቡ በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ጫፍ በምትገኘው ቤይት ላሂያ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል
የምስሉ መግለጫ,በቅርቡ በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ጫፍ በምትገኘው ቤይት ላሂያ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ የፀረ ሐማስ መፈክሮች ተሰምተዋል

“ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ ፍርሃት አልተሰማቸውም” ብለዋል ሁኔታውን መከታተላቸውን የተናገሩት የዓይን ምስክር።

“ተጋፈጥዋቸው፤ ታጣቂዎቹ እቃቸውን ሰብሰብው እንዲሄዱ ነገርዋቸው። እዚህ አንፈልጋችሁም። ውድመት፣ ጥፋት እና ሞት ያመጣብንን መሳሪያችሁን እዚህ አንፈልግም አሏቸው” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

በሌላ አካባቢ በተካሄዱ ተቃውሞዎችም ሰላማዊ ዜጎች በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ታጣቂዎች ከሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች አካባቢ እንዲርቁ ጠይቀዋል።

ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ ዋጋ ያስከፍላል። በጋዛ ከተማ የሐማስ ታጣቂ አንድ የተቃውሞ ሰልፈኛን ተኩሶ ገድሏል።

ጦርነቱ ሊቆም ይችላል የሚለው ተስፋ እየሰለለ መምጣቱን ተከትሎ የጋዛ ነዋሪዎች ቁጣቸውን በሐማስ እና በእስራኤል ታጣቂዎች ላይ እየገለፁ ነው።

በጋዛ ለደረሰው ቀውስ ማንን ተጠያቂ እንደሚያደርግ የተጠየቀው አሚን አቤድ “ምርጫው በኮሌራ እና በወረርሽኝ መካከል ነው” ይላል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋዛ ጎዳናዎች ላይ የታየው ፀረ ሐማስ ተቃውሞ አመጽ የተቀላቀለበት አይደለም።

ነገር ግን የጋዛ ሰርጥን ለ20 ዓመታት ያስተዳደረው ሐማስ ቀስ በቀስ ሥልጣን ከእጁ እተንሸራተተ ይመስላል።