
ከ 4 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ በኪየቭ ላይ በምትፈጽመው ከባድ የአየር ጥቃት “ደስተኛ አለመሆናቸውን” ገለፁ።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን “አቁም” ሲሉ የተናገሩ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሩሲያ ላይ ሊወሰድ ስለሚችል ተጨማሪ እርምጃ ያሉት ነገር የለም።
ሐሙስ ምሽት በዩክሬን ዋና ከተማ ላይ ሩሲያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 12 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ነው የተባለውን ተከታታይ እና ከባድ ጥቃት ተከትሎ በሁለቱም ወገኖች ላይ “ከፍተኛ ጫና ማድረግ” ጦርቱን ያስቆመዋል ብለዋል።
ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በሚያደርጉት ጥረት ላይ ሩሲያ የምትፈጽማቸው ጥቃቶች እንቅፋት ሆነዋል።
በትሩዝ ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የተቹት ዶናልድ ትራምፕ “አስፈላጊ አልነበረም፤ እንዲሁም በጣም መጥፎ ጊዜ ነው፤ ቭላድሚር አቁም!” ብለዋል።
ሩሲያ ተከታታይ ጥቃቶችን እየፈጸመች ያለው የሰላም ጥረቱ አካል ተደርጎ የቀረበው እና ሩሲያ በቁጥጥሯ ስር ያደረገቻቸውን ግዛቶችን ኪየቭ እንድትቀበል ግፊት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።
ሐሙስ ዕለት ትራምፕ ከኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በዋይት ሐውስ በተገናኙበት ወቅት “ለየትኛውም ወገን ውግንና የለኝም፤ የምወግነው ሕይወትን ማትረፍ ላይ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ደቡብ አፍሪካን በሚጎበኙበት ወቅት ስለ ተፈጸሙት ጥቃቶች የተናገሩ ሲሆን፣ አሜሪካ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ሩሲያ ላይ የተሻለ ጫና ማድረግ ትችል ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዜሌንስኪ “ሩሲያ ላይ በሚገባ ጫና ከተደረገ ስምምነት ላይ መድረስ እንችላለን ብለን እናምናለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
- በጋዛ ጎዳናዎች ላይ እየጎሉ የመጡት ሐማስን የሚቃወሙ ፍልስጤማውያን ሰልፈኞችከ 5 ሰአት በፊት
- ግብፅ እና ጂቡቲ የቀይ ባሕር አስተዳደር የተጎራባች ሀገራት “ብቸኛ ኃላፊነት” እንደሆነ መስማማታቸው ተገለጸ24 ሚያዚያ 2025
- ቻይና የዶናልድ ትራምፕን ታሪፍ ለመቋቋም ምን ዓይነት እርምጃዎችን ልትወስድ ትችላለች?ከ 5 ሰአት በፊት
የዩክሬን ፕሬዝዳንት የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ አቋማችውን ይቀይሩ እንደሆን ተጠይቀው፤ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗ በራሱ “ትልቅ ማመቻመች ነው” እንዲሁም “የተኩስ አቁም የመጀመርያው እርምጃ መሆን አለበት” ብለዋል።
“ሩሲያ ለተኩስ አቁም ዝግጁ መሆኗን ከገለፀች ዩክሬን ላይ የምተፈጽማቸውን ድብደባዎች ማቆም አለባት። ዩክሬናውያን ናቸው ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ ያለው። ምክንያቱም እኛ ነን ጥቃት እየተፈፀመብን ያለነው ማንም አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ የፈጸመችው ጥቃት ዜሌንስኪ የደቡብ አፍሪካ ጉብኝታቸውን አቋርጠው እንዲመለሱ አድርጓቸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሩሲያ በኃይል የተቆጣጠረቻቸውን መሬቶች ለሰላም ስምምነቱ ሲሉ ለመስጠት መስማማት አለባቸው ሲሉ ተናግረው ነበር፥።
ረቡዕ ዕለት ትራምፕ የዩክሬን እና የሩሲያን ጦርነት ለማቆም የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ “በጣም ቅርብ” ነን ብለው የነበረ ሲሆን ዜሌንስኪ ግን ከአሜሪካ የቀረባላቸውን ሃሳብ ጦርነቱን “ከማራዘም ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም” በማለት ውድቅ አድርገዋል።
ዜሌንስኪ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሩሲያ በ2014 በቁጥጥሯ ስር ያዋለቻትን ክሬሚያ ለመስጠት እምቢተኛ ሆነዋል።
ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሰላም ሰምምነቱን በተመለከተ የአሜሪካን እቅድ ይፋ አድርገዋል።
ከእቅዱ መካከል የሁለቱም አገራት ወታደሮች አሁን ባሉበት እንዲቆዩ እና የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎቹን በተመለከተ ዩክሬንም ሆኑ ሩሲያ አሁን ይዘዋቸው ባሉ ግዛቶች ላይ እንዲስማሙ የሚል ነበር።
ዋይት ሐውስ የትራምፕ አስተዳደር ክሬሚያን የሩሲያ አካል አድርጎ እውቅና የመስጠት እቅድ ስለመኖሩ ተጠይቆ ሲመልስ ትራምፕ ጦርነቱ እንዲያበቃ ብቻ ነው ፍላጎታቸው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ” የመጨረሻውን መስመር አሳይተናቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሁለቱም መስማማታቸውን እንዲገልጹ እንጠብቃለን። ነገር ግን ትናንት ምሽት ወደ ኪየቭ የተወነጨፉት ሚሳዔሎች ሁሉንም አካላት ይህ ጦርነት ለምን መቆም እንዳለበት አስታውሷል” ብለዋል።