
ከ 4 ሰአት በፊት
የእስራኤል መከላከያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኛን ከታንክ ላይ በተተኮሰ ጥይት መትቶ መግደሉን አመነ።
የእስራኤል መከላከያ ባለፈው ወር በጋዛ ሰርጥ ውስጥ የሞተውን የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኛን አለመግደሉን ተናግሮ ነበር።
መጋቢት 19 የእስራኤል ጦር በዲያር አል ባላህ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ቅጥር ግቢ ላይ በፈጸመው ጥቃት አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ መሞቱን ተከትሎ ጥቃቱን አለመፈጸሙን ገልጾ ነበር።
ነገር ግን ሐሙስ እለት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በወጣው መግለጫ የመጀመርያ ደረጃ የምርመራ ውጤቱ እንደሚያሳየው ቅጥር ግቢው ውስጥ በሚገኙ ሕንጻዎች በስህተት “ጠላት እንደሚገኝባቸው” በመለየታቸው ወታደሮቹ የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኛን መግደላቸውን አምኗል።
በመግለጫው ላይ አክሎም “ሕንጻው ላይ ጥቃት የተፈጸመው ጠላት መኖር አለመኖሩ ላይ ቅኝት ከተደረገ በኋላ ቢሆንም የተባበሩት መንግሥታት ተቋም መሆኑ አልተለየም ነበር” ብሏል።
የመጀመርያ ደረጃ ምርመራ ውጤቱን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማጋራቱን የገለፀው መከላከያ ሚኒስቴሩ አጠቃላይ ሪፖርቱ ሲጠናቀቅ እንደሚያስረክብ አስታውቋል።
አክሎም “የእስራኤል መከላከያ ኃይል በተፈጸመው ነገር ማዘኑን እየገለፀ፤ ወደፊት እንዲህ ኣይነት ክስተቶች እንዳይፈጠሩ እንዲሁም ከዚህ ክስተት ለመማር ተገቢውን ፍተሻ ያካሂዳል፤ በጠፋው ሕይወት የተሰማንን ሐዘን እየገለፅን ለቤተሰቦቹም መጽናናት እንመኛለን” ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ በፈጸመው ጥቃት ቬልቭ ማሪኖቭ የተባለ የቡልጋሪያ ዜግነት ያለው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኛ የተገደለ ሲሆን ሌሎች አምስት ሠራተኞች ከባድ ጉዳት አስተናግደዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ለሁለት ወር ያህል የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ የሚወስደውን ወታደራዊ እርምጃ ዳግም አጠናክሮ በጀመረበት ወቅት ነው።
- ግብፅ እና ጂቡቲ የቀይ ባሕር አስተዳደር የተጎራባች ሀገራት “ብቸኛ ኃላፊነት” እንደሆነ መስማማታቸው ተገለጸ24 ሚያዚያ 2025
- ትራምፕ ሩሲያ በኪየቭ ላይ በምትፈጽመው ከባድ ድብደባ “ደስተኛ አለመሆናቸውን” ገለፁከ 4 ሰአት በፊት
- ትራምፕ በንግድ ዙርያ ንግግር ለማድረግ ከፈለጉ የጣሉትን ታሪፍ እንዲያነሱ ቻይና አሳሰበችከ 4 ሰአት በፊት
በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉታሬስ በክስተቱ ላይ ሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ቃል አቀባያቸውም “የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅጥር ግቢዎች በሙሉ በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት እና ዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ለመከላከል እና ላለማጥቃት በሚገዙ በሙሉ የሚታወቁ ናቸው” ብለዋል።
ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ጥቃቱ በእንግዶች ማረፊያ ላይ መድረሱን ገልጾ፣ ቤቱ “ነጠል” ያለ እንደሆነ እና ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተፈጸመ መሆኑን አንደሚያምን ገልጾ ነበር።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱ በደረሰበት ዕለት “ከሚወጡት ዘገባዎች በተለየ የእስራኤል መከላከያ ኃይል በዲየር ኤል ባላህ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ቅጥር ግቢ ላይ ጥቃት አልፈጸመም፤ መገናኛ ብዙኃን ያልተጣሩ ዘገባዎችን ከመዘገብ እንዲቆጠቡ መከላከያ ሚኒስትር ጥሪ ያቀርባል” ብሎ ነበር።
ቢቢሲ የተመለከታቸው እና ያረጋገጣቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች የተጎዱ ሰዎችን የሚያሳዩ ሲሆን ሁለቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መለያ የሆነውን ሰማያዊ ጃኬት ለብሰው በድርጅቱ አምቡላንስ ሆስፒታል ሲደርሱ ያሳያል።
የእስራኤል መከላከያ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ባለፈው ወር በጋዛ የተገደሉት 15 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች “በባለሙያዎች ስህተት” መሆኑን ገልጾ ነበር።
እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት ዳግም ከቀጠለች በኋላ 1,978 ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል።
እስራኤል ሐማስ ላይ የሚደረግ ወታደራዊ ጫና በቁጥጥሩ ስር የሚገኙ 59 ታጋቾች ለማስለቀቅ ያግዛል ትላለች።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን በመግደል 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሔድ የጀመረችው።
በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ51,300 በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የግዛቲቱ ጤና ሚኒስቴር ይናገራል።