
ከ 7 ሰአት በፊት
- ማስገንዘቢያ፡ ቢቢሲ ስለጤና የሚያትማቸው ጽሑፎች ለአጠቃላይ መረጃ ካልሆነ በስተቀር የሐኪም ምክርን አይተኩም።
ጥፍር ጥቅሙ ምንድነው? ብሎ መንደርደር ደግ ነው።
የጣት ጥፍር ከሥር ያለውን የቆዳ ጫፍ ከአደጋ ይጠብቃል።
ሌላስ?
ቢያሳክከን ማን እንደ ጥፍር። ከማንም ቀድሞ ይደርሳል።
አንዳንዴ አንዳንድ ቦታችንን በማከክ የሚሰማንን ልዩ እርካታ ምስጋናውን ለጥፍራችን ካላደረስን ንፉግነት ነው።
ሌላስ?
አንድን ነገር መላጥ ብንፈልግ ጥፍር ከሌለን እንዴት ይሆናል?
የአውራ ጣት ጥፍር ሲታመም መላጥ እንዴት ፈተና እንደሆነ ያኔ ይገባናል።
የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን ሌላ ነው። ጥፍራችን ስለ ጤናችን ምን እንደሚናገር ይመረምራል።
ጥፍር ያሳስባል?
ስለ ጥፍር ሲነሳ ሁሉም ሰው አንድ ነገር ያውቃል።
አንዳንድ ጊዜ ከጥፍራችን ወደ ላይ የሚወጡት ነጭ ጭራ የሚመስሉ ነገሮች የካልሺየም እጥረት የሚያመጣቸው ናቸው።
ይህ ግን ምን ያህል እውነት ነው? ወደ ኋላ ላይ እንመለከታለን።
ስለ ጥፍር መሠረተ-ሥሪት (Anatomy) በአጭሩ እንዲህ እንበል።
ጥፍሮች የቆዳ ቅጥያዎች ናቸው። የተሠሩት ደግሞ ከኬራቲን ነው። ኬራቲን የጣት ጫፍን ከአደጋ የሚከላከል የፕሮቲን ሥሪት ነው።
በጥፍራችን ግርጌ ላይ የግማሽ ጨረቃ ቅርፅ ያለው ነገር ደግሞ ‘ሉኑላ’ ይባላል። የጥፍር ዕድገት ማዕከል ልንለው እንችላለን።
የጥፍር ሴሎች እዚያ ተወልደው፣ አድገው እና ደድረው ነው ኋላ ደንበኛ ጥፍር ሆነው ብቅ የሚሉት። እስኪፈለጉ ታዲያ ተቀያሪ ወንበር ላይ ይቀመጣሉ። ጥፍር ሲያልቅ ይተካሉ።
ከዚያ ቀጥሎ የሚገኘው አካል ደግሞ ባክቴሪያ እና ፈንገስ ወይ ደግሞ ሌላ በሽታ አምጪ ተህዋሲያን አልፈው እንዳይገቡ ዘብ የሚቆም መከላከያ ነው።
ስለ ጥፍር መሠረታዊ ሥሪት ይህን ያህል ካልን ይበቃል።
ይልቅ ሐኪሞች በምርመራ ወቅት ጥፍራችንን ለምንድነው የሚመለከቱት?
ስለ ጤናችን የሚነግራቸው ነገር ስላለ ነው።
ኩላሊት በሽታ ወይ ደግሞ የቆዳ በሽታ ወይም ሌላ በሽታ እንዳለብን ጥፍር ጥቆማ ይሰጣል።

የከባድ በሽታ ምልክት?
“በሕክምና ትምህርት ቤት ከተማርኳቸው ቁም ነገሮች ውስጥ አንዱ ‘የጥፍር መቆልመም’ የሚባል ነገር ነው። ይህን በታማሚዎች ላይ መፈለግ የመጀመሪያ ተግባር ነው፤ ይህ በጥፍር እና ጥፍሩ በተዘረጋበት ቆዳ መካከል ያለው ቦታ ቅርጽ ሲቆለመም የሚታይበት ነው” ይላሉ በብሪስቶል ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና የኅብለሰረሰር (ነርቭ) መምህር የሆኑት ዳን ባምጋርድት።
በሌላ ቋንቋ ጥፍራችን የማንኪያ ጫፍ ቅርፅ ሲኖረው ማለት ነው።
የጥፍሩ ሥር ቆዳ ይለሰልሳል። ጥፍሩ ከጣት ምንጣፍ ጋር ልጥፍ ከማለት ይልቅ የተንሳፈፈ ይመስላል። የጣቶች ጫፍ ጎበጥ ይላል። ጫፉ ሲታይ ያበጠ ጣት ይመስላል።
እንዲህ ዓይነት ጥፍር ዝቅተኛ የደም ኦክሲጅን መጠን ምልክት ነው። አንዳንድ ጊዜ ከሳንባ ካንሰር ጋር ይዛመዳል ።
የልብ ቧንቧ መተላለፊያ ኢንፌክሽን ምልክትም ሊሆን ይችላል።
ሐኪሞች ይህን ምልክት በበሽተኞች ላይ ከተመለከቱ በአስቸኳይ ራጅ እንዲነሱ ያዛሉ። ምክንያቱም የሳንባ ካንሰር እንደሚሆን ስለሚጠረጥሩ ነው።
እንዲህ ዓይነት የማንኪያ ጫፍ የመሰለ ቆለማማ ጥፍር የሚያጋጥመው ግን ከስንት አንዴ ነው።
- ከቢቢሲ አማርኛ ዜና እና ታሪኮች በቀጥታ እንዲላክልዎ የዋትስአፕ ቻናላችን አባል ይሁኑ5 ታህሳስ 2024
- በአዲስ አበባ ብዙ ሰዎች ‘የቫይታሚን ዲ’ እጥረት አለባችሁ የሚባሉት በስህተት ነው?13 የካቲት 2025
- የሽንታችን ቀለም ስለጤናችን ምን ይነግረናል? ምን ዓይነት ቀለም ሲኖረው ነው ሊያስጨንቀን የሚገባው?27 ጥር 2025
ነጫጭ ምልክቶች
ጥፍር ላይ ያሉ ነጭ ነጠብጣቦች – ሉኮኒቺያ በመባል ይታወቃሉ።
ብዙውን ጊዜ የቫይታሚን ወይም የማዕድን እጥረት ምልክት ተደርገው ይወሰዳል።
ይሁን እንጂ ይህን የሚደግፉ ማስረጃዎች አስተማማኝ የሚባሉ አይደሉም።
አንድ ጥቂት ሰዎች የተሳተፉበት ጥናት ጥፍራቸው ላይ ነጫጭ ነጠብጣቦች ያሉባቸው ሰዎች የዚንክ እና የካልሲየም እጥረት አለባቸው ማለት እንዳልሆነ አመላክቷል።
ይሄ ነጭ የጥፍር ነጠብጣብ ብዙውን ጊዜ ጥፍር ሲጎዳ የሚመጣ ነው። ለምሳሌ ጣታችንን በር ሲቀረጥፈው። ወይ ደግሞ ከባድ ነገር ጣታችን ላይ ሲወድቅ ይፈጠራል።
በጣት ላይ ልዩ ልዩ ቀለሞች ሲታዩ አንዳንድ ጊዜ የሚያመላክቱት ነገር ሊኖር ይችላል።
ለምሳሌ ጥፍራችን ንጣቱ ከበዛ ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ነጭነት ከተቀየረ በደም ወስጥ ያለ የፕሮቲን እጥረት መኖሩን ያመላክታል። ይህ ደግሞ ከኩላሊት፣ ከጉበት እና ከስኳር በሽታ ጋር ይያያዛል።
የጉበቱ ጉዳይ ከአልኮል ሱሰኝነት ጋር ሊመጣ ይችላል።
በሌላ በኩል ከጥፍር ሥር ሰማያዊ ምልክት ከታየ የሰውነት ኦክሲጂን እጥረት ሊሆን ይችላል። ይህ ከልብ ህመም ጋር የሚያያዘ ነው።
በጥፍር ሥር ጥቁር መስመሮች ከታዩ ያልተለመደ የቆዳ ካንሰር ምልክት ሊሆንም ይችላል። መመርመር አይከፋም።

የፈንገስ ምልክቶች
ሐኪሞች በሽተኛውን በሚመረመሩበት ጊዜ የጥፍሩን ቀለም ብቻ ሳይሆን ውፍረት እና ቅርፅ ላይ ለውጦችን ማየት ይፈልጋሉ ።
ለምሳሌ በጤናማ ጥፍር ከታች ያለው የጥፍር ወለል ከነጭ ይልቅ ሮዛማ ቀለም መሆን አለበት።
ሌሎች ቀለሞች ግን ቀላል የጥፍርን ኢንፌክሽን ወይም አሳሳቢ የጤና ሁኔታን ሊያመለክቱ ይችላሉ።
በሐል ዩኒቨርሲቲ የቁስል ፈውስ እና ተያያዥ ጉዳዮች መምህር የሆኑት ሆሊ ዊልኪንሰን “በእግር ጣቶችዎ ላይ በተለይም በጣት ጥፍርዎ ላይ ነጭ ወይም ቢጫ ቀለም ካዩ ይህ የፈንገስ ኢንፌክሽን ምልክት ሊሆን ይችላል” ይላሉ ።
በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ለቀላል የፈንገስ የጥፍር ኢንፌክሽኖች ያለሐኪም ማዘዣ መድኃኒት መግዛት ይቻላል። ሆኖም ኢንፌክሽኑ የቆየ ከሆነ ሐኪም ማየት ይመከራል።
“ብዙ ጊዜ ሰዎች በጥፍር ላይ የቀለም ለውጥ ሲመለከቱ ኢንፌክሽን መሆኑን አይገነዘቡም። ቸል ይሉታል። ያኔ በጣም መጥፎ ወደሚሆንበት ደረጃ ይደርሳል” ይላሉ ዊልኪንሰን።
የሚፈረካከሱ ጥፍሮች

የጥፍር ቅርጽ መሠረታዊ የጤና ችግሮችን ሊያመላክት ይችላል።
ጤናማ የእግር ጣት እና የጣት ጥፍር በአመዛኙ ሾጣጣ መሆን አለበት። ደግሞም ጫፉ አካባቢ ወደ ውጭ ትንሽ ጥምዘዝ ይላል።
ጥፍር የሰመጠ ወይ ደግሞ ጎድጎድ ያለ ነገር ሊኖረው አይገባም። ጎድጎድ ካለ ‘ኮይሎንቺያ’ የሚባለው ችግር አለበት ማለት ነው።
ይህ ችግር ያለበት ጥፍር ወደ ውስጥ ጥምዝዝ ይላል። ቀጭን እና ስስ ነው። እንዲሁም የሚፈራርስ ይመስላል።
አንዳንድ የዚህ ችግር ሰለባዎች ጥፍራቸው እንደ ጎድጓዳ ሳህን ገባ ያለ ይሆናል። ፈሳሽ የሚያቁር ይመስላል።
ይህ ነገር ምናልባት የደም ማነስ ሊሆን ይችላል።
ሰውነታችን ወደ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍል ማድረስ ያለበት ኦክሲጂን እያደረሰ አይደለም ማለት ነው። ለምን? በቂ ጤናማ የደም ተሸካሚ ሴሎች ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ አይደለም።
የደም ማነስ የአይረን ማነስ ነው። ሐኪም ማየት ጥሩ ነው።
በሌላ በኩል፣ በጥፍራችን የምናያቸው አንዳንድ ለውጦች የአመጋገብ ጉድለቶችን ብቻ ሊያመለክቱ ይችላሉ።
አንዳንድ ሰዎች ጥፍራቸው ላይ አግድም ሸንተረሮች አሉባቸው። በቁም ሳይሆን በአግድም በጥፍሮቻቸው ላይ የሚሄዱ መስመሮች ይታያሉ።
ይህ የፕሮቲን እጥረት አመላካች ነው። የስኳር በሽታ እና የደም ቧንቧ ኢንፌክሽን ምልክትም ሊሆን ይችላል።
ስብና ኮሌስትሮል በደም ቧንቧ አካባቢ ተከማችተው የደም ዝውውር እያስተጓጎሉ እንደሆነ ምልክት ሊሆን ይችላል። መመርመር ጥሩ ነው።
በዌልስ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ የሕፃናት ሐኪም የሆኑት ሜሪ ፒርሰን “በጥፍራችን የአግድም መስመሮች መኖር የዚንክ እጥረት አመላካች ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
የተሰባበሩ ጥፍሮች ደግሞ የቫይታሚን ቢ7 እጥረት ምልክቶች ናቸው።
የሕይወት ዘይቤ?
አንዳንድ ጊዜ ጥፍሮቻችን ስለ ጤናችንም ሆነ ስለ አመጋገባችን ምንም አይነግሩንም። ስለ አኗኗር ዘይቤያችን ብቻ ይጠቁሙናል።
ለምሳሌ የሚፋፋቅ ጥፍር ‘ኦኒኮሽቺያ’ በመባል ይታወቃል። የጥፍር ቀጫጭን ንብርብሮች በቀጥታ ከነጩ የጥፍር ጠርዝ ሲለዩ እና ወደ ኋላ ሲላጡ የሚከሰት ነው።
በኒውዮርክ የሚገኘው የማውንት ሲናይ ዩኒቨርስቲ የቆዳ ሕክምና ፕሮፌሰር ጆሽዋ ዘይችነር “ይህ ነገር በጣም ደጋግሞ እጅን ከመታጠብ፣ ወይ ደግሞ ከጥፍር መድረቅ እና ከጥፍር ቀለም አጠቃቀም የሚመጣ ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
በአጠቃላይ ጥፍርዎን አልፎ አልፎ እንዲመለከቱት ሐኪሞች ይመክራሉ። በቅርጽ፣ በቀለም ወይ ደግሞ በገጽታው (Texture) አንዳች ጉልህ ለውጥ ካዩ፣ ሐኪም ዘንድ መሄድ ጥሩ ነው። ታዲያ ሳይዘገዩ መሆን አለበት።