መሳርያ የምታስተካክል የሩሲያ ወታደር

ከ 7 ሰአት በፊት

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

ክሬምሊን ይፋ ያደረገው ይህ የተኩስ አቁም የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማብቃት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ከሐሙስ ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም. ጠዋት ጀምሮ እስከ ግንቦት 3/2017 ዓ.ም. የሚቆይ ይሆናል ተብሏል።

የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ በምላሹ “ቢያንስ ለ30 ቀናት የሚቆይ” አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ክሬምሊን የፋሲካ በዓልን በማስመልከት ለ30 ሰዓታት የዘለቀ የተኩስ አቁም እንደሚያደርግ ገልጾ የነበረ ቢሆንም በደቂቃዎች ውስጥ ግጭቱ በመቀጠሉ ሳይሳካ ቀርቷል።

በዩክሬን የተኩስ አቁም ለማድረግ ከ20 ጊዜ በላይ ሙከራ የተደረገ ቢሆንም አንዳንዶቹ በደቂቃ ውስጥ በመፍረሳቸው፣ ሁሉም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በቅርቡ የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ይፋ የተደረገው የተኩስ አቁም ውግያው እንዲቀንስ ያደረገ ቢሆንም፣ ውግያ ባለመቆሙ ላለመሳካቱ ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርሳቸው ይካሰሳሉ።

ክሬምሊን ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ፑቲን “ሰብዓዊነትን መሰረት በማድረግ” የተኩስ አቁም ለማድረግ ወስነዋል ብሏል።

መግለጫው አክሎም “ሩሲያ ዩክሬንም ተመሳሳዩን እርምጃ መውሰድ እንዳለባት ታምናለች” ብሏል።

“በዩክሬን በኩል የተኩስ አቁሙን ለመጣስ የሚደረግ ማንኛውም እርምጃ የሩሲያ ፌዴሬሽን መከላከያ ኃይል ተመጣጣኝ እና ውጤታማ ምላሽ ይሰጣል” ሲል ያስጠነቅቃል።

“ሩሲያ አሁንም የዩክሬንን ቀውስ ከስሩ ለመፍታት የሚደረግ የሰላም ንግግር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የምትቀበል ሲሆን፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ለሚደረግ ገንቢ ውይይትም ዝግጁ መሆኗን ትገልጻለች።”

መግለጫውን ተከትሎ የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሲቢሃ “ሩሲያ እውነት ሰላምን የምትፈልግ ከሆነ የተኩስ አቁም አሁኑኑ ማድረግ አለባት” ብለዋል።

“ለምን እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ እንቆያለን?” ሲሉ የጠየቁት ሚኒስትሩ፣ “አሁን ተኩስ የሚቆም ከሆነ፣ ለ30 ቀናት መዝለቅ ከቻለ፣ ለታይታ ሳይሆን እውነት ይሆናል” ብለዋል።

ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት አገራቸው “ለዘላቂ እና ሙሉ የተኩስ አቁም ዝግጁ ናት። እኛ ሁሌም የምንጠይቀው ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ነው” ብከዋል።፥

የዋይት ሐውስ ፕሬስ ኃላፊ ካሮላይን ሌቪት፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በሁለቱም አገራት መሪዎች ላይ ያላቸው ትዕግስት እየተሟጠጠ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ቋሚ የሆነ የተኩስ አቁም ማየት ይፈልጋሉ።”

“ቭላድሚር ፑቲን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ለማድረግ ማስታወቃቸውን አውቃለሁ። ፕሬዝዳንቱ [ትራምፕ] ግድያው እንዲቆም ቋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ግልጽ አድርገዋል። የሚፈሰውን ደም ይቁም” ብለዋል።

ይህ የፑቲን መግለጫ የተሰማው በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ውስጥ አሜሪካ “በጣም ወሳኝ ሳምንት” ስትል በጠራችበት ወቅት ነው።

አሜሪካ በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ እያሸማገለች የመትገኝ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ግን ምንም ዓይነት ለውጥ የማያዩ ከሆነ ጥረታቸውን እንደሚያቋርጡ አስጠንቀቀዋል።

ፑቲን በበኩላቸው ለዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ ሰላም እንደምትፈልግ ለማሳየት ጥረት እያደረጉ ነው።