
ከ 2 ሰአት በፊት
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ እና የሱዳኑ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን በናይል ተፋሰስ ላይ “የውሃ ደኅንነትን በጋራ ለማስጠበቅ” መወያየታቸው ተገለፀ።
የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄነራል አል ቡርሃን ሰኞ ዕለት በግብፅ ካይሮ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች በተለይም በአባይ ተፋሰስ ዙርያ መነጋገራቸውን የግብፅ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የሁለቱ አገራት መሪዎች ባወጡት መግለጫ ላይ መሪዎቹ በሱዳን መልሶ ግንባታ እና በውሃ ደኅንነት ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
የሁለቱ አገራት “የውሃ ደኅንነትን ለማስጠበቅ” መነጋገራቸውን የገለፀው የግብፅ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ፣ መሪዎቹ በውይይታቸው ወቅት “በብሉ ናይል ላይ የሚወሰድ የተናጠል እርምጃን ተቃውመዋል” ብሏል።
የሁለቱ አገራት መሪዎች በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚገኙ አገራት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የዓለም አቀፍ ሕግን ለማስከበር እንደሚሠሩ መነጋገራቸው ተገልጿል።
“በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የአመለካከት ውህደት በግብፅ እና በሱዳን ብሔራዊ ደኅንነት መካከል ባለው ጥብቅ ትስስር የተደገፈ ነው” ያለው የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት፣ በአባይ ተፋሰስ ላይ የሚኖር የውሃ ደኅንነትን በጋራ ለማስጠበቅ መነጋገራቸውን ገልጿል።
ግብፅ በሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባት ስትወተውት ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ሦስቱ አገራት በአባይ ወንዝ ላይ ባላቸው የውሃ ድርሻ ላይ መስማማት ከቻሉ ከሕዳሴ ግድብ የሚለቀቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻል አቋሟን አሳውቃለች።
ግድቡን በሚመለከት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ሳይሳካ ያለውጤት መበተኑ ይታወሳል።
ግንባታው በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቅ የተነገረው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተወሰነ ደረጃ ኃይል እያመነጨ ሲሆን፣ ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሳል የሚል ስጋቷን ስትገልፅ ቆይታለች።
- ግብፅ እና ጂቡቲ የቀይ ባሕር አስተዳደር የተጎራባች ሀገራት “ብቸኛ ኃላፊነት” እንደሆነ መስማማታቸው ተገለጸ24 ሚያዚያ 2025
- በየመን የስደተኞች ማዕከል ላይ በአሜሪካ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት የተጎዳ ኢትዮጵያዊ እንዳለ ተሰማ28 ሚያዚያ 2025
- በካናዳ በተደረገው ምርጫ የሊብራል ፓርቲ ማሸነፉ ተገለፀከ 5 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያ ግንባታውን ልታጠናቅቅ በተቃረበችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓመታት ተቃውሞዋን ስታሰማ የቆየችው ግብፅ ኢትዮጵያ እያሳየችው ካለው በቀይ ባሕር በኩል መተላለፊያ በር ከማግኘት በተቃራኒ የአካባቢውን አገራት እያስተባበረች ነው።
ባለፈው ሳምንት ግብፅ ከጂቡቲ ጋር የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ “የአስተዳደር እና የፀጥታ” ጉዳይ የውሃ አካላቱን የሚጎራበቱ አገራት “ብቸኛ ኃላፊነት” እንደሆነ ተስማማታለች።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ ታኅሣሥ ወር ላይ ወደ ግብፅ በተጓዙበት ወቅት የግብፅ መንግሥት ተመሳሳይ አቋም አንጸባርቋል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ባደረጉት ንግግር ቀይ ባሕርን ሊጠቀሙ የሚገባው “ተጎራባች አገራት ብቻ” እንደሆነ እና “ሌላ አካል” ወደ ቀይ ባሕር “እንዲገባ ሊፈቅድለት እንደማይገባ” ተናግረው ነበር።
ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳለህ ወደ ግብፅ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር በተነጋገሩበት ወቅትም በተመሳሳይ፤ “የቀይ ባሕር የአስተዳደር እና ደኅንነት ጉዳይ” የተጎራባቾቹ ሀገራት “ብቸኛ ሚና” እንደሆነ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።
በትናንትናው ዕለት በግብፅ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የተገናኙት ፕሬዝዳንት አልሲሲ እና አልቡርሃን የሁለቱ አገራት ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ለማጠናከር ተወያይተዋል።
ግብፅ ሱዳንን መልሶ ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ላይም ተሳታፊ እንደምትሆን ተገልጿል።
በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት የሱዳን ጦር ኃይሎች ዋና ከተማይቱ ካርቱምን እንደገና መቆጣጠርን ተከትሎ የተከሰቱ ለውጦች ላይ ያተኮረ እንደነበር የፕሬዝዳንቶቹ ጽህፈት ቤት በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።
በዚህ ውይይት ላይ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የሱዳን ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሁለቱ ወገኖች ተስማምተዋል።
አልቡርሃን ከግብጽ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ታሪካዊ እና ስር የሰደደ እንዲሁም “ስትራቴጂካዊ” መሆኑን መግለጻቸው በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።
አል ሲሲ በበኩላቸው ለሱዳን መረጋጋት እና የመንግሥት ተቋማት መጠናከር ያላቸውን “ድጋፍ” ገልጸው መልሶ ግንባታ ሂደቱን እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።
ካይሮ ከካርቱም ጋር የሚኖራትን ግኙነት እንደምታጠናክር የገለፁት አልሲሲ፣ ሁለቱ አገራት ባላቸው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ላይ ኩራት እንደሚሰማቸው መናገራቸውን ጽሕፈት ቤታቸው ገልጿል።