
28 ሚያዚያ 2025
አሜሪካ በሁቲ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ባለው የሰሜን ምዕራብ የየመን ክፍል ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች ተይዘው በሚገኙበት ማዕከል ላይ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 68 ሰዎች መገደላቸውን የታጣቂ ቡድኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሚኖሩባት የመን ዛሬ ሰኞ ማለዳ በተጸመው ጥቃት ቆስለው በአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከቦታው ከወጡት ሰዎች መካከል ቢያንስ አንድ ኢትዮጵያዊ እንዳለ እየተገለጸ ነው።
አል ማሲራህ የተባለው የሁቲ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳለው ሳዓዳ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ማዕከል ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከሞቱት በተጨማሪ አብዛኞቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው 47 ሰዎች ቆስለዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት የማቆያ ማዕከል ውስጥ የነበሩት ስደተኞች አፍሪካውያን መሆናቸው ከመገለጹ ውጪ የየት አገራት ዜጎች እንደሆኑ ለጊዜው የወጣ ዝርዝር መረጃ የለም።
ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በቀይ ባሕር በኩል በሕገ ወጥ አደገኛ የጀልባ ጉዞ ወደ የመን የሚጓዙት አብዛኞቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገራት የሚነሱ ስደተኞች ናቸው።
ዜናውን በምሥል አስደግፎ ያሠራጨው የቴሌቪዥን ጣቢያ በአንድ የወደመ ሕንጻ ፍርስራሽ ሥር የተቀበሩ የበርካታ ሰዎች አስከሬኖችን የሚያሳዩ አሰቃቂ ምሥሎችን አቅርቧል።
ሳዓድ ውስጥ የሚገኘው የስደተኞች ማቆያ ማዕከል ዛሬ ሰኞ ማለዳ 11 ሰዓት አካባቢ አራት ጊዜ በከባድ የጦር መሳሪያ በተመታበት ወቅት በውስጡ 115 አፍሪካውያን ስደተኞች እንደነበሩ የአል ማሲራህ ዘገባ አመልክቷል።
በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ወዲያውኑ ያልታወቀ ሲሆን፣ የቴሌቪዥን ጣቢያው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የበርካታ ሰዎችን አስከሬን ከግንብ ፍርስራሾች ውስጥ ሲያወጡ እና የብረት ስብርባሪዎች ወለሉን የሸፈኑት በከፊል የፈረሰ ግድግዳ እና ጣሪያ ያለው ቤትን አሳይቷል።
በጥቃቱ ከሞቱት በተጨማሪ በርካታ ስደተኞች ክፉኛ መቁሰላቸው ከየመን እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እያመለከቱ ሲሆን፣ ሮይተርስ የዜና ወኪል ደግሞ አንድ በጥቃቱ ቆሰሎ የተረፈ ኢትዮጵያዊ “እናቴ” እያለ በአማርኛ ሲጣራ መሰማቱን ዘግቧል።
ቢቢሲ በስደተኞቹ ማዕከል ምን ያህል ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ እና ጉዳት የደረሰባቸው ስንት እንደሆነ ለማወቅ ጥረት እያደረገ ነው።
በሁቲ የሚመራው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር “ሆን ተብሎ” በሰላባዎቹ ላይ የተፈጸመ የቦምብ ጥቃት መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱ “የጦር ወንጀል” ነው በማለት አውግዞታል።
- አሜሪካ በየመን ባካሄደችው የአየር ጥቃት ከ800 በላይ ዒላማዎችን መምታቷን አስታወቀች28 ሚያዚያ 2025
- ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን በየመን የታቀደ ምሥጢራዊ ጥቃትን ጋዜጠኛ ባለበት የማኅበራዊ ሚዲያ ቡድን በማጋራታቸው ቁጣ ተቀሰቀሰ25 መጋቢት 2025
- በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የነበሩባቸው ጀልባዎች ተገልብጠው 180ዎቹ ደብዛቸው ጠፋ8 መጋቢት 2025

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች መርጃ (አይኦኤም) በሳዓዳ ስደተኞች ላይ “የሕይወት መጥፋት መከሰቱን በሚያመለክቱት ሪፖርቶች በጽኑ ማዘኑን” ገልጿል።
“ምንም እንኳን አይኦኤም በስደተኞቹ ማዕክል ውስጥ የማይሠራ ቢሆንም ክስተቱን በቅርበት እየተከታተልነው ሲሆን፣ በሚያስፈልገው ሁሉ ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠና ነን” ብሏል።
በተጨማሪም “በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ወገኖች የሲቪሎችን ደኅንነት መጠበቅን ቅድሚያ እንዲሰጡ እና ዓለም ዓቀፍ ሕጎችን በሙሉ እንዲያከብሩ ጥሪ እናቀርባለን።”
አሁን በአሜሪካ ጥቃት በስደተኞች ማቆያ ላይ ደረሰ ስለተባለው ጉዳት ከአሜሪካ ጦር ሠራዊት በኩል ወዲያውኑ የተሰጠ ምላሽ የለም።
ነገር ግን ይህ ጉዳት የመድረሱ ዜና የተሰማው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሁቲዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲጠናከር ትዕዛዝ ከሰጡ ከሳምንታት በኋላ ሠራዊቷ የመን ውስጥ ከ800 በላይ ዒላማዎችን መምታቱን ካሳወቀ ከሰዓታት በኋላ ነው።
የአሜሪካ ጦር በፈጸማቸው ተከታታይ መጠነ ሰፊ የአየር ድብደባዎች “በመቶዎች የሚቆጠሩ የሁቲ ተዋጊዎች እና በርካታ የሁቲ ቡድን መሪዎች” እንዲሁም የቡድኑን የሚሳዔል እና የድሮን ፕሮግራሞችን የሚቆጣጠሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር ተገድለዋል ብሏል።
የሁቲ አስተዳደር ባለሥልጣናት በበኩላቸው በአሜሪካ የተፈጸሙት ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ያሳወቁ ሲሆን፣ በቡድኑ አባላት ላይ የደረሰው ጉዳት ግን ጥቂት መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በሁቲ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር የአሜሪካ አየር ኃይል በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ በሚገኘው ራስ ኢሳ በተባለው የነዳጅ ማምረቻ ላይ በፈጸመው ተከታታይ ጥቃት ቢያንስ 74 ሰዎች ሲገደሉ፣ ሌሎች 171 ሰዎች መቁሰላቸውን ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ በጥቃቱ የራስ ኢሳ ነዳጅ ማምረቻን ማውደሙን እና ይህም “ሁቲዎች ዘመቻዎችን የማካሄድ አቅማቸውን የሚያዳክመው ከመሆኑ በተጨማሪ ለሽብር ተግባራቸው ከምርቱ የሚያገኙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ገቢን ያሳጣል” ብሏል።
ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በርካታ ስደተኞች አደገኛውን የቀይ ባሕር መስመርን በሕገ ወጥ መንገድ በማቋረጥ ከባሕር ላይ አደጋ ከተረፉ ወደ የመን እንደሚገቡ ይታወቃል።
ስደተኞቹ በጦርነት በምትታመሰው የመን በኩል በማቋረጥ የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ወደ ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት ይጓዛሉ።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደሚለው ስደተኞቹ ብዝበዛ፣ ጥቃት እና ጦርነት በሚካሄድባቸው ቀጣናዎች በአደጋ ውስጥ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
በዚህም በባሕር ላይ ጉዞ ከሚደርስባቸው አደጋ በተጨማሪ የመን ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ለጉዳት እንደሚጋለጡ ሲዘገብ ቆይቷል።
ምንም እንኳን በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት የደኅንነት ስጋት ቢኖርም ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከ60 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ የመን የገቡ ሲሆን፣ በአብዛኛውም ምንም ድጋፍ አያገኙም።