
ከ 7 ሰአት በፊት
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ኮርኔይ አገራቸው ከአሜሪካ ተገቢው አክብሮት እንደሚገባት ገልፀው በንግድ እና ደኅነንነት ጉዳዮች ላይ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ወደ ውይይት የሚገቡት “በራሳችን ፍላጎት መሰረት ነው” ብለዋል።
ምርጫው ሲጠናቀቅ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ካርኔይ ዋሽንግተን ለጉብኝት የሚሄዱት የካናዳን ሉዓላዊነት ያከበረ “ኮስተር ያለ ንግግር የሚኖር ከሆነ” ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል።
እንደ ካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ከሆነ ካርኔይ እና ትራምፕ በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን በቅርቡ ተገናኝቶ ለመወያየት ተስማምተዋል።
የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ “ሁለቱ መሪዎች በካናዳ አስፈላጊነት ላይ እንዲሁም እንደ ነጻ እና ሉዓላዊ አገር ከዩኤስ ጋር በሁለቱ አገራት የጋራ ጥቅም ላይ አብሮ ለመስራት ተስማምተዋል” ብሏል።
ትራምፕ የካናዳን ምርጫ ያሸነፉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ካርኔይን እንኳን ደስ አለዎት ማለታቸውም ተሰምቷል።
ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ከተመረጡ በኋላ በተደጋጋሚ ካናዳን “51ኛዋ የአሜሪካ ግዛት” ስለማድረግ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ማክሰኞ ዕለትም ከዋይት ሐውስ ተመሳሳይ አቋም ተንፀባርቋል።
የዋይት ሐውስ ምክትል ቃል አቀባይ አና ኬሊ “ምርጫው ዶናልድ ትራምፕ ካናዳን የአሜሪካ 51ኛ የተወደደች ግዛት ማድረግ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ የለም” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት ካርኔይ እና ሊብራል ፓርቲያቸው የካናዳን ምርጫ በድል ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር የዶናልድ ትራምፕ ሃሳብ “ፈጽሞ በጭራሽ የሚሆን አይደለም” ብለዋል።
“እውነቱን ለመናገር፣ ማንኛውም አገር እንኳ ቢሆን . . . ፓናማ ወይንም ግሪን ላንድ አልያም ሌላ አገር ቢሆን የሚሆን አይመስለኝም” ብለዋል።
ይኹን አንጂ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ የምንደርስ ከሆነ እና ከአውሮፓ ኅብረት እና ዩኬ ጋር የንግድ አጋርነታችነንን የምናጠናክር ከሆነ “ሁለታችንም የምናሸንፍበት መንገድ ይኖራል” ሲሉ ተናግረዋል።
- የግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ እና የሱዳኑ አልቡርሃን በ’አባይ ተፋሰስ የውሃ ደኅንነት’ ላይ መወያየታቸው ተገለፀ29 ሚያዚያ 2025
- በአቶ ጌታቸው የሚመራው ህወሓት ‘ትግራይ ሊብራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ የሚባል አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁም ነው29 ሚያዚያ 2025
- በካናዳ በተደረገው ምርጫ የሊብራል ፓርቲ ማሸነፉ ተገለፀ29 ሚያዚያ 2025
አሜሪካ ለካናዳ የንግድ ድርጅቶች ትልቋ ገበያቸው ናት።
የካናዳ ምርቶች 75 በመቶ ማረፊያቸው የአሜሪካ ገበያ ሲሆን ካናዳ የአሜሪካ ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ አቅራቢ አገር ናት።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 አሜሪካ ከካናዳ ጋር ያላት የንግድ ጉድለት 45 ቢሊዮን ዶላር ተገምቷል።
የካናዳ እና አሜሪካ ግንኙነት እየተቀዛቀዘ የመጣው ዶናልድ ትራምፕ “51ኛዋ ግዛት” ለማድረግ እንደሚፈልጉ ከተናገሩ በኋላ ሲሆን፣ የቀድሞውን የካናዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን የአሜሪካ ግዛት አስተዳዳሪዎችን በሚጠሩበት መንገድ “ገዢ” ሲሉ መጥራታቸውም ግንኙነታቸው ላይ ጥላ እንዲጥልበት አድርጓል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በዓለማችን የተለያዩ አገራት ላይ ታሪፍ ሲጥሉ ትኩረት ካደረጉባቸው ቀዳሚ አገራት መካከል ካናዳ ትገኝበታለች።
መጀመርያ ላይ ዶናልድ ትራምፕ ከካናዳ በሚመጡ ምርቶች ላይ አጠቃላይ የ25 በመቶ ታሪፍ የጣሉ ሲሆን በሁሉም የአልሙኒየም እና ብረት ምርቶች ላይ ደግሞ ተጨማሪ የ25 በመቶ ቀረጥ ጥለዋል።
ካናዳ በምላሹ 42 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ታሪፍ የአሜሪካ ምርቶች ላይ በመጣል ምላሽ ሰጥታለች።
ካርኔይ ከትራምፕ ጋር ንግግር የሚኖረው “በእነርሱ መመርያ መሰረት ሳይሆን በእኛው በራሳችን ፍላጎቶች ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“የምጣኔ ኃብት እና የደህንንት አጋርነቶች ይኖሩናል፤ ይህ ግን ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ ነው የሚሆነው” ብለዋል።