
ከ 8 ሰአት በፊት
የአልኮል መጠጦች ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ይጠጣል፤ የብዙ ድግሶች ማድመቂያ ተደርጎም ይወሰዳል።
ሰውነትን ስለሚያፍታታ በቀላሉ ከሰዎች ጋር ለማውራት የሚጠቀሙበትም ሰዎች አሉ።
ሲደሰቱ፣ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር ሲቀላቀሉ ወይም ሲያዝኑም ወደ መጠጥ ፊታቸውን የሚያዞሩ ጥቂቶች አይደሉም።
እንደ ቀይ ወይን ያለ መጠጥን ሳያበዙ መጎንጨት ለጤና እንደሚጠቅም ጥናቶች ከዚህ ቀደም ጠቁመዋል።
አሁን ግን የዓለም ጤና ድርጅት የትኛውም መጠን ያለው የአልኮል መጠጥ በጤና ላይ አሉታዊ ውጤት አለው ብሏል።
ለመሆኑ የአልኮል መጠጦች በሰው ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት ዋናዎቹ የትኞቹ ናቸው?
ምግብ ነክ ዘገባዎችን የሚሠራው የቢቢሲ አምድ የመጠጥን ጉዳቶች እንደሚከተለው ቃኝቷል።
ካንሰር እና ሞት
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ በመላው ዓለም በየዓመቱ በመጠጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ሞቶች 2.6 ሚሊዮን ይጠጋሉ።
የአልኮል መጠጥ የአንጀት እና የጡት ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎችም የካንሰር ዓይነቶች ያጋልጣል።
የዓለም ጤና ድርጅት በሠራው ጥናት፣ የተወሰነ የሚባለው የመጠጥ መጠን ከ1.5 ሊትር ያነሰ ወይን፣ ከ450 ሚሊ ሊትር ያነሰ አረቄ እና መሰል መጠጦች ወይም ከ3.5 ሊትር ያነሰ ቢራ ነው።
የድርጅቱ አዲስ መመሪያ የሚጠቁመው ጤናማ የሚባል የመጠጥ መጠን እንደሌለ ነው።
“መጠጥ ከመጀመሪያው ጠብታ ጀምሮ ሰዎችን ይጎዳል” ይላል ድርጅቱ።
- የአባቶች መጠጣት በልጆች አጠቃላይ ጤና እና ባህሪ ላይ ምን አይነት ጉዳት አለው?8 መስከረም 2024
- መልካም ጓደኝነት እና ማኅበራዊ ሕይወት ለጤና እና ለረዥም ዕድሜ ያላቸው ጠቀሜታ27 ነሐሴ 2024
- በቀን ስንት ስኒ ቡና መጠጣት ይመከራል? ለምን?28 ነሐሴ 2024
መጠጥ መቀነስ
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጠጥ መጠን ቀንሷል።
እአአ በ2010 ከነበረው የ5.7 ሊትር የመጠጥ መጠን በ2019 ወደ 5.5 ሊትር ወርዷል።
በእንግሊዝ፣ በርክሻየር የምትኖረው የ44 ዓመቷ አና ታይት መጠጥ ሙሉ በሙሉ አቁማለች።
“በጣም እጠጣ ነበር ባልልም በየሳምንቱ አርብ እጠጣ ነበር። ሁለት ቢራ እና ሁለት ጂን ከሥራ በኋላ እወስዳለሁ። ከዚያ ከባለቤቴ ጋር ወይን እጠጣለሁ” ትላለች።
ቀስ በቀስ ይሄ ልማድ ወደ ቅዳሜ ተሻገረ። ብዙም ሳይቆይ ሐሙስ እና እሑድም ትጠጣ ጀመር።
ማራቶን ለመወዳደር ልምምድ ስትጀምር ግን አሠልጣኟ መጠጥ እንድታቆም ነገሯት።
እሷም ባለቤቷም መጠጥ ቀነሱ። ከዚያም አቆሙ።
“በጣም ትልቅ ለውጥ ነበር። አሁን የተሻለ ስሜት እና ጥንካሬ ይሰማኛል” ትላለች።
ኤሚሊ ሀውንስቲን የምትኖው ጀርመን፣ ባቫሪያ ነው። መጠጥ እንድታቆም ጓደኞቿ ረድተዋታል።
“ካልጠጣሁ ጥሩ ምሽት ማሳለፍ አልችልም ነበር” የምትለው ኤሚሊ ከመጠጥ በኋላ ጠዋት የሚፈጠረው ህመም (hangover) ያሰቃያት ነበር።
“እሑድ ከእንቅልፌ ስነሳ ቅዳሜ ምን እንደተከሰተ አላውቅም ነበር። መጠጥ ለማቆም ወሰንኩ።”
አሁን ባሳየችው ለውጥ ደስተኛ ናት።

ሳይንስ ተሳስቷል?
ሁለቱ ሴቶች መጠጥ በማቆማቸው ጠቀሜታ አግኝተዋል።
በካናዳ ከሱስ ጋር የተያያዙ ጥናቶች በሚያካሂደው ተቋም ውስጥ የሚሠሩት ዶ/ር ቲም ስቶክዌል፣ የዓለም ጤና ድርጅት ስለ መጠጥ ያወጣውን ማሳሰቢያ ይጋራሉ።
“አልኮልን መጠጣት ሲጀመር ነው ጉዳቶቹ የሚጀምሩት” ይላሉ።
መጠነኛ መጠጥ እና ሞት ያላቸውን ትስስር በተመለከተ 107 ጥናቶችን ተመልክተዋል።
መጠጥ ሲበዛ ከመቶ ሰዎች በአንዱ ሞት እንደሚከሰት እና አነስተኛ በሚባል መጠጥ ከአንድ ሺህ ሰዎች በአንዱ ላይ ሞት እንደሚከሰት ጥናቶቹ ይጠቁማሉ።
የተወሰነ መጠጥ የሚለው ምጣኔ ከአገር አገር ይለያያል።
ዶ/ር ቲም እንደሚሉት፣ መጠጥ በአነስተኛ መጠን አይጎዳም የሚለው እሳቤ የመጣው በተገቢው ሁኔታ ባልተሠሩ ጥናቶች ነው።
ስለ ሰዎች የቀደመ የመጠጥ ልማድ ሳይጠየቅ የተሠሩ ጥናቶች እንደሆኑ ያስረዳሉ።
“የተወሰነ አልኮል የሚጠጡ ሰዎች ጥሩ ገቢ ያላቸው እና የተመጣጠነ ምግብ የሚወስዱ ናቸው። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሠሩ ሲሆን፣ የተሻለ የሕክምና ተደራሽነትም አላቸው” ይላሉ።

መጠጥ ይጠቅማል?
ከመጠጥ ጋር የተያያዙ ጉዳቶች አሳሳቢ ናቸው? በሚለው ላይ የተለየ ዕይታ ያላቸውም አሉ።
በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ዴቪድ ስፒግሌተር፣ “አንድ ወይም ሁለት ብርጭቆ መጠጣት ምን ይጎዳል? የሚለውን ለማወቅ የሚደረገው ጥረት እምብዛም አይገባኝም” ይላሉ።
“መኪና ሲነዳ ወይም ሕይወትም ሲኖር ስለ ጉዳት እና ጥቅም እንደምናስብ ሁሉ መጠጥም በአወንታዊ እና አሉታዊ አማካይ ላይ ያለ አድርገን መውሰድ አለብን” ሲሉም ያክላሉ።
መጠጥ ያለውን ጉዳት በትክክለኛ መጠን መለካት ይቻላል ብለው አያስቡም።
አልኮል ጠቃሚ ነው ወይም ጎጂ ነው ከሚለው ቡድን ውስጥ ባይሆኑም፣ መጠነኛ መጠጥ መጠጣት ያዘወትራሉ።
“መጠጥ በሕይወት የመኖር ምጣኔን ይቀንሳል። ከ50 ዓመት በላይ መጠጣት ወይም አንድ ቀን መጠጣት በየቀኑ ከሕይወት ላይ 15 ደቂቃ ይሰርቃል። ሆኖም ግን አሳማ መብላት እና ቴሌቭዢን መመልከትም ጎጂ ናቸው” ሲሉ ያስረዳሉ።
ሰዎችን የትኛውን መንገድ መከተል እንዳለባቸው ምርጫቸው እንደሆነ ያምናሉ።
“መጠጥ የሚያስደስታችሁ ከሆነ ጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ጋር ማመጣጠን አለባችሁ” ይላሉ።