የፋእናንስ ህጉን የተቃወሙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያን አደባባእ በመውጣት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል

ከ 7 ሰአት በፊት

ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የግብር ጭማሪን በመቃወም አደባባይ የወጡ የተቃዋሚ ሠልፈኞችን የገደሉ የኬንያ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ምርመራ እንዲደረግ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድረጅቶች ዳግም ጥያቄ አቀረቡ።

በኬንያ ፓርላማ አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሦስት ኬንያውያንን አስመልክቶ ቢቢሲ አፍሪካ አይ የሰራውን የምርምራ ዘገባን ተከትሎ በርካታ ኬንያዊያን የተቆጡ ሲሆን ፍትሕንም ጠይቀዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዲሁም የኬንያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በምርመራ ዘገባው ላይ የተለዩ የፀጥታ ኃይል አባላት “ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸው” ብለዋል።

የኬንያ መንግሥት ቃል አቀባይ አይዛቅ ማዋራ በሰጡት ምላሽ “እያንዳንዱ ሕይወት አስፈላጊ ነው” ካሉ በኋላ ፖሊስን የሚቆጣጠረው ተቋም ምርምራ እያደረገ መሆን ገልጸው፣ የቢቢሲን ዘገባ “ለአንድ ወገን ያደላ” ሲሉ ተችተዋል።

“ምርመራውን የሰሩ አካላት የመንግሥትን አስተያየት ማካተት ነበረባቸው. . . . ፍትኃዊ እና ሚዛናዊ ይሆን ነበር” ብለዋል።

“ለምሳሌ ፓርላማ በእሳት ሲቃጠል አሳይተዋል። ነገር ግን ማን እንዳቃጠለው አላሳዩም። በፓርላማው ላይ የደረሰውን ውድመት አሳንሰው ለማቅረብ የፈለጉ ይመስላል” ሲሉም አክለዋል።

የተቃዋሚ ሠልፈኞቹ በፋይናንስ ረቂቅ ሕጉ ላይ የነበራቸው ጥያቄ ተገቢ ነበር ያሉት ቃል አቀባዩ “በሁከት እና በብጥብጥ የምትመራ አገር ልትኖረን አትችልም” ብለዋል።

ቢቢሲ የምርመራ ዘገባው ላይ መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ማክሰኞ እለት በኬንያ ፓርላማ በምርመራ ዘገባው ላይ አጭር ውይይት የተደረገ ሲሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ጆን ኬሪ ቢቢሲ “የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ ያስተናግዳል” ሲሉ ተችተውታል።

ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል ሚሌ ኦዲያምቦ ደግሞ መንግሥት እና ፓርላማው መገናኛ ብዙኃንን ሳይከለክሉ የተቃዋሚ ሠልፈኞቹ ላይ የደረሰውን “በተረጋጋ ሁኔታ” መመልከት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኦዲያምቦ “የቢቢሲ ምረምራ ዘገባ በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል. . . መገናኛ ብዙኃንን ልናስቆም አንችልም” ብለዋል።

የምርመራ ዘገባው ከመተላለፉ በፊት ምላሹን አንዲሰጥ የተጠየቀው የኬንያ ፖሊስ፣ ራሱን እንደማይመረምር ገልፆ የኬንያ ፖሊስን እንቅስቃሴዎች በገለልተኛነት የሚቆጣጠረው ተቋም ለቀረቡበት ውንጀላዎች ምርመራ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግሯል።

የኬንያ መከላከያ ኃይል በበኩሉ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ የቀረበበትን ውንጀላ ለመመርመር ስልጣን ያለው አካል በፓርላማው አካባቢ ተሰማርተው በነበሩ አባላት ላይ የቀረበውን ውንጀላ ተከትሎ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳላቀረበ ገልጿል።

‘ብለድ ፓርላመንት’ የተሰኘው የቢቢሲ አፍሪካ አይ የምርመራ ዘገባ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሰኔ 25 2024 የአገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች የፋይናንስ ሕጉን ተቃውመው አደባባይ በወጡ ወጣቶች ላይ የወሰዱትን የጭካኔ እርምጃ የሚያሳይ ነው።

ከፍተኛ ተቃውሞ ያስተናገደው የፋይናንስ ሕግ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ያለመ መሆኑን መንግሥት ይገልጻል።

የኬንያ መንግሥት ይህ የታቀደ ገቢ ከውጪ የሚኖረውን ብድር ለመቀነስ ያለመ ነው ቢልም ከፍተኛ ተቃውሞ አስተናግዷል።

ቢቢሲ ለዚህ የምርመራ ዘገባው ከ5000 በላይ ምስሎችን የተመለከተ ሲሆን ሦስት ተቃዋሚ ሠልፈኞችን ተኩሰው የገደሉ የፀጥታ ኃይሉን የደንብ ልብስ ለብሰው በተቃውሞ ሠልፉ አካባቢ የተመደቡ የፖሊስ እና የመከላከያ አባላትን ለመለየት ችሏል።

የኬንያ የፀጥታ ኃይሎች የፋይናንስ ሕጉን ተቃውመው በተለያየ አካባቢ አደባባይ የወጡ 65 ሠልፈኞችን መግደላቸው ሲነገር፤ 89 ሰዎች ደግሞ የገቡበት እንዳልታወቀ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ተናግረዋል።

እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ ከሆነ የፋይናንስ ሕጉን ተቃውመው አደባባይ የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳረገዋል።

የኬንያ መንግሥት የሞቱት 42 ሰዎች ብቻ ናቸው ሲል ቁጥሩን ዝቅ ያደርጋል።