April 30, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ

በአዲስ አበባ ከተማ በአርሶ አደርነት እና በአርሶ አደር ልጅነት የይዞታ ማረጋገጫ የምስክር ሰርተፍኬት እንዲሰጣቸው ካመለከቱ 27 ሺህ ያህል አመልካቾች ውስጥ፤ ሰባት ሺህ የሚጠጉት ያቀረቡት ጥያቄ “ውድቅ መደረጉን” የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። የይገባኛል መብት ጥያቄዎቹ ውድቅ የተደረጉት፤ የቀረቡት ጥያቄዎች ማጣራት ከተደረገባቸው በኋላ ትክክለኛ እንዳልሆኑ በመረጋገጡ እንደሆነ ከንቲባዋ ገልጸዋል። 

ከንቲባዋ ይህንን ያሉት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 22፤ 2017 በተካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ነው። ጥያቄውን ያቀረቡት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የምክር ቤት ተመራጭ የሆኑት እሌኒ አየለ፤ ከአርሶ አደሮች የይዞታ መብት ጋር በተያያዘ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስንተዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደሮች የይዞታ መብትን ለማረጋገጥ እያካሄደ ያለውን የመሬት ልኬት ስራ፣ የመረጃ ማደራጀት፣ የተደራጀውን የማጥራት ስራዎች የምክር ቤት አባሏ አድንቀዋል። ያቀረቡት መረጃ ትክክለኝነት ለተረጋገጠላቸው አርሶ አደሮች፤ የይዞታ መብታቸውን የሚያረጋግጥላቸውን ካርታ የማዘጋጀት ስራ “በተቀላጠፈ ሁኔታ፣ በፍጥነት እና በጥራት መሰራት” እንደሚገባውም አመልክተዋል።

“የአገልግሎት ጥራት እና ፍጥነት በተመለከተ አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ ከአርሶ አደሮች እየተነሳ ነው” ያሉት እሌኒ፤ ለዚህ ችግር መፍትሔ እንደሚበጅለት ጠይቀዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፤ ትክክለኛ አርሶ አደሮች የይዞታ መብታቸው እንዳይነፈግ እና ሌሎችም ያለአግባብ እንዳይጠቀሙ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ከንቲባ አዳነች፤ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ባለፉት የከተማይቱ ስብሰባዎችም መሰል ጥያቄዎች መነሳታቸውን አስታውሰዋል። እርሳቸው የሚመሩት የከተማይቱ አስተዳደር ለጥያቄዎቹ “የተሟላ ምላሽ” አለመስጠቱን ያመኑት ከንቲባዋ፤ የእዚህ ምክንያቱ በአርሶ አደር ስም “አላግባብ ለመጠቀም” በሚደረጉ ጥረቶች፤ “ብዙ ጫናዎች የመፍጠር ሂደቶች” ስለነበሩ እንደሆነ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ለጥያቄዎቹ ምላሽ ለመስጠት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን እና ስራው በየሳምንቱ ጭምር ግምገማ እንደሚደረግበት አዳነች አስረድተዋል። በእዚህ ሂደት ውስጥ ከወረዳ እና ከክፍለ ከተማ የተውጣጡ ስራው የሚመለከታቸው ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም የአርሶ አደር ኮሚቴ አባላት “በደንብ እንዲሳተፉበት” እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።

ይህንን ተከትሎም፤ ከልኬት እና ከወሰን ጋር የሚነሱ የአመልካቾች ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውን ከንቲባዋ ለከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል። በየክፍለ ከተማው በተደረገ ማጣራት፤ አርሶ አደር ሳይሆኑ የይዞታ ይገባኛል መብት ጥያቄ ያቀረቡ አመልካቾች እንደተደረሰባቸውም አዳነች በዚሁ ማብራሪያቸው አመልክተዋል።  

“የይገባኛል መብት አመልካቾች 27,000 ነበሩ። ከዚያ ውስጥ 6,800 ያህሉ ትክክለኛ ያልሆኑ ጥያቄዎች መሆናቸውን አጥርተን ውድቅ አድርገናል። በህዝብም አስተችተናል። ከዚያ በመለስ ያሉትን ‘ህጋዊ መብት ይገባቸዋል’ የሚለውን በደንብ ለይተን፤ በየደረጃው እየጸደቀ መጥቷል” ሲሉ ከንቲባዋ ተናግረዋል። ይህ የማጣራት ሂደት አንድ ወር ገደማ የፈጀ እንደነበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደር እና ልማት ቢሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።

በቢሮው የመብት ፈጠራ እና ይዞታ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ የኑስ አደም፤ አመልካቾች እውነተኛ መሆናቸው ከሚጣራባቸው መንገዶች ውስጥ በማመልከቻቸው በጠቀሱበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ምስክርነት አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል። አመልካቾች በጠቀሱት አካባቢ በሚኖሩበት ወቅት የእርሻ ስራ ገቢ ግብር መክፈላቸውም እንደዚሁ በማጣራት ሂደቱ እንደሚታይ ምክትል ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

በማጣራት ሂደቱ “አርሶ አደር ነን ብለው” ያመለከቱ ሆኖም አለመሆናቸው የተረጋገጠባቸው እንዲቀነሱ መደረጋቸውን አቶ የኑስ ገልጸዋል። ሂደቱ ሲጠናቀቅ የአመልካቾች መረጃ ለአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ እንደሚላክ እና በዚህ ላይ በመመስረት የይዞታ መረጋገጫ ካርታ እንደሚዘጋጅም ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሁለት ዓመት በፊት ካደረገው ተመሳሳይ የማጣራት ስራ በኋላ ለ3,451 አርሶ አደሮች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት መስጠቱን አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)