
ከ 43 ደቂቃዎች በፊት
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለው ጦርነት እያዘገመ ቀጥሏል፤ የተቃውሞ ድምጾች ግን እየበረከቱ ነው።
በቅርብ ሳምንታት ከሁሉም የሠራዊቱ ቅርንጫፎች የተወጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ተጠባባቂ ወታደሮች፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ መንግሥት ውጊያውን እንዲያቆም እና ትኩረቱን ስምምነት በመፈጸም በሐማስ ተይዘው ያሉ 59 ታጋቾች ማስመለስ ላይ እንደያደርግ የሚጠይቅ ደብዳቤ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ከ18 ወራት በፊት ጥቂት የእስራኤል ወታደሮች፤ ሐማስን ማሸነፍ እና ታጋቾችን ማስመለስ የሚለው የጦርነት አመክንዮ ላይ ጥርጣሬ አንስተው ነበር።
ጥር ላይ የተደረገው የተኩስ አቁም እና አብሮት የመጣው ከ30 በላይ የሚሆኑ ታጋቾች መመለስ ጦርነቱ በቅርቡ ያበቃል የሚል ተስፋን በብዙዎች ዘንድ ፈጥሮ ነበር።
ነገር ግን እስራኤል በመጋቢት አጋማሽ የተኩስ አቁሙን መጣሷን እና ወደ ጦርነት መመለሷን ተከትሎ ይህ ተስፋ ጨልሟል።
የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ የቀድሞ ኃላፊ የነበሩት ዳኒ ያቶም፤ “እስራኤል ወደ ከፋ ስፍራ እያመራች ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል” ይላሉ።
“ኔትያናሁን በዋንኛነት የሚያሳስበው የራሱ ጥቅም እንደሆነ እንረዳለን። ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ዝርዝር ውስጥ የራሱ ፍላጎት እና የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር የማድረግ ፍላጎት እንጂ ታጋቾቹ የሉም” በማለት ይናገራሉ።
የአሁኑ ደብዳቤ ላይ የፈረሙት አብዛኞቹ እንደ ያቶም ሁሉ ለረጅም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲተቹ የነበሩ ናቸው። የተወሰኑት ሐማስ መስከረም 2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተነሳው ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ በተካሄዱ ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች ላይ የተሳተፉ ናቸው።
ያቶም ግን ድምጻቸውን ለማሰማት የወሰኑት በዚህ ምክንያት አለመሆኑን ይናገራሉ።
“ስሜን ጽፌ የፈረምኩት እና በተቃውሞ ሰልፎች ላይ የምሳተፈው በፖለቲካዊ ምክንያት አይደለም፤ በብሔራዊ ምክንያት እንጂ” ይላሉ። “ሀገሬ መንገዷን ልትስት መሆኑ እጅጉን ያሳስበኛል” ሲሉ ያክላሉ።
በሚያዝያ ወር መጀመሪያ የወጣው የመጀመሪያው ግልጽ ደብዳቤ አንድ ሺህ በሚሆኑ የአየር ኃይል ተጠባባቂ እና ጡረታ በወጡ ወታደሮች ተፈርሟል።
- በፍልስጤም የተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ዲዛይን ውድድር ‘ያሸነፉት’ ኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች26 ሚያዚያ 2025
- በጋዛ ጎዳናዎች ላይ እየጎሉ የመጡት ሐማስን የሚቃወሙ ፍልስጤማውያን ሰልፈኞች25 ሚያዚያ 2025
- የእስራኤል መከላከያ ወታደሮቹ የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኛን መግደላቸውን አመነ25 ሚያዚያ 2025

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ፈራሚዎቹ፤ “የጦርነቱ መቀጠል የትኛውንም የተነገረለትን ግብ አያሳካም” በማለት ደብዳቤያቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን ጦርነቱ “የታጋቾችን ሞት ያስከትላል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የደብዳቤው ፈራሚዎች፤ ጋዛ ውስጥ በሕይወት እንዳሉ በሚገመቱት 24 ታጋቾች ላይ ጊዜው ከማለቁ በፊት እስራኤላውያን የእነርሱን ፈለግ እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
“የሚያልፈው እያንዳንዱ ቀን ሕይወታቸውን ይበልጥ አደጋ ውስጥ እየከተተው ነው። እያንዳንዱ የማንገራገር ቅጽበት አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነው” ብለዋል።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ምርጥ ተዋጊዎች እና የስለላ ክፍሎችን እንዲሁም ተሸላሚ ወታደራዊ አዛዦችን ጨምሮ ከሁሉም የሠራዊቱ ቅርንጫፍ በሚያስብል ደረጃ ተመሳሳይ ደብዳቤዎች ሲወጡ ተስተውሏል።
በአጠቃላይ 12 ሺህ ፈራሚዎች ተሳትፈዋል።
ከመስከረም 2016 ዓ.ም. የሐማስ ጥቃት ወዲህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ተጠባባቂ ወታደሮች የተደረገላቸውን ጥሪ የተቀበሉት በማገልገል ስሜት ነበር።
አሁን ግን ጥሪውን የማይቀበሉ ተጠባባቂ ወታደሮች ብዛት እየጨመረ ነው። ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ጥሪውን የሚቀበሉ ተጠባባቂ ወታደሮች ብዛት ወደ 50 እና 60 በመቶ ወርዷል።
ለሚያደርጋቸው ጦርነቶች በተጠባባቂ ወታደሮች ላይ በእጅጉ ለሚተማመነው ሠራዊት፤ የአሁኑ ቀውስ እ.አ.አ በ1982 ከተካሄደው የመጀመሪያው የሊባኖስ ጦርነት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ነው።
ተጠባባቂ ወታደሩ ዮአቭ (ስሙ የተቀየረ)፤ ባለፈው ክረምት በጋዛ ተሰማርቶ የነበረ ሲሆን አሁን ግን እንደማያደርገው ይናገራል።
“ሄጄ ወንድም እና እህቶቼን መርዳት እንዳለብኝ ይሰማኛል” ይላል። “ጥሩ ነገር እያደረግኩ እንደሆነ አምን ነበር፣ ውስብስብ ነገር ግን መልካም [ድርጊት]። አሁን ግን በተመሳሳይ መልኩ አልመለከተውም” ሲል ይናገራል።
እንደ ዮአቭ አገላለጽ፤ ታጋቾች በጋዛ ወሻዎች ወስጥ የሞት ስጋት ተደቅኖባቸው እያለ የእስራኤል መንግሥ እየተዋጋ ለመቀጠል መወሰኑ ስህተት ነው።
“በጣም ጠንካራ ነን፣ ሐማስን ማሸነፍ እንችላለን። ነገር ግን ጉዳዩ ሐማስን የማሸነፍ አይደለም። ሀገራችንን የማጣት ጉዳይ ነው” ይላል።

ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር፣ የእስራኤል ባለሥልጣናት እንደሚደርጉት የሀገሪቱን ሠራዊት በዓለም ላይ የላቀ ሥነ ምግባር ያለው እያሉ መግለጽ አስቸጋሪ እየሆነ እንደሚመጣ ተቺዎች ይናገራሉ።
አሚራም ሌቪን የተባሉ ጡረታ የወጡ ጄነራል በቅርቡ ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሁፍ ከከፍተኛ አዛዦች ጀምሮ ወታደሮች ትዕዛዝን ስላለማክበር ለማሰብ ጊዜው እንደሆነ ጽፈው ነበር።
“የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ የጦርነት ወንጀል የመፈጸም እና አስከፊ ሽንፈት የመከናነብ ስጋት” እንደተጋረጠበት የገለጹት ጄነራሉ፤ “እጅን ሰብስቦ ለመቀመጥ የማይቻል ነው” ብለዋል።
እስራኤልን በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እና ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሱትን ጨምሮ ተቺዎች ግን ይህ መስመር አሁንም ቢሆን መጣሱን ያነሳሉ።
ተቃዋሚዎችን የሚወርፉት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትያናሁ፤ የሚነሱትን ስጋቶች “የፕሮፓጋንዳ ውሸቶች” ሲሉ አጣጥለዋል። ይህንን ጉዳይ የሚያነሱት “በጥቂት እዚህ ግባ የማይባሉ አካላት [ናቸው]፤ የሚጮሁ፣ አናርኪስት እና ኋላ ቀር ጡረተኞች፤ ብዙዎቹም ለዓመታት ያለገለገሉ ናቸው” ሲሉ ወርፈዋል።
ይሁን እንጂ የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች፤ የተቃዋሚዎቹ ደብዳቤዎች እያደገ ያለውን ‘የቀሩት ታጋቾች ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ይሰጣቸው’ የሚል የሕዝብ አቋም የሚያንጸባርቁ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ፀረ ጦርነት የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄድባት በቆየችው ቴል አቪቭ የታጋቾች ምሥል ከፍ ተደርጎ ሲያዝ ተስተውሏል። ሌሎች ተቃዋሚዎች ደግሞ በጦርነቱ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ህጻናት ምሥሎች ይዘው መንገድ ላይ ቁጭ ይላሉ።
ደብዳቤዎቹ የፈጠሩትን ክርክር እንዲሁም እንዲህ ዓይነቶቹ በስሜት የተሞሉ ድርጊቶች ባለሥልጣናትን ሳያስቆጡ የቀሩ አይመስልም።
ሚያዝያ 12/2017 ዓ.ም. ፖሊስ “የጋዛ ህጻናት ወይም ጨቅላዎች ምሥል” እንደማይፈቀድ እንዲሁም “ዘር ማጥፋት” ወይም “ዘር ማጽዳት” የሚሉ ቃላትን የያዙ ፖስተሮችን መያዝ እንደማይፈቀድ ለተቃዋሚዎች ገልጿል።
ይሁን እንጂ ከተቃውሞዎቹ አዘጋጆች በኩል የታየውን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ ፖሊስ በፍጥነት ውሳኔውን ቀልብሷል።
ይህ በእንዲህ ባለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐማስን ለማሸነፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን ቀጥለዋል።
እንደ ኔትያናሁ ገለጻ አሁንም ቢሆን ታጋቾቹን ወደ ቤታቸው መመለሻ ብቸኛ መንገድ ወታደራዊ ጫና ነው።