
ከ 4 ሰአት በፊት
በዕድሜ የገፉ ሰዎች እንክብካቤ በሚያገኙበት ማዕከል ውስጥ ነዋሪ የሆኑት የ103 ዓመቷ አዛውንት ጆአን ፓርትሪጅ፣ በቲክቶክ ላይ ባጋሩት ቪዲዮ ምክንያት በዩናይትድ ኪንግደም በማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑት ሰዎች መካከል ለመመደብ ተቃረበዋል።
የዕድሜ ባለጸጋዋ ቲክቶክ ላይ ትኩረትን የሳቡት የመዋቢያ ሜካፕ ሲጠቀሙ የሚያሳየው ቪዲዮ ከተጋራ በኋላ ነው።
ቪዲዮው በአጭር ጊዜ ወደ 200 ሺህ በሚጠጉ ሰዎች የታየ ሲሆን፣ መዋቢያዎችን ከሚያመርት ኩባንያ ጋር ግንኙነት እንዲፈጠር በር ከፍቷል።
ይህ አጋጣሚ የተፈጠረው ዎርሴስተርሻየር የሚገኘው ሚልክሮፍት የአዛውንቶች መንከባከቢያ ማዕከል የወ/ሮ ጆአንን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ካጋራ በኋላ ነው።
አዛውንቷ ቲክቶክ ላይ ትኩረት ስበው መነጋገሪያ ከሆኑ በኋላ “ይህንን ያህል ትኩረት አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። . . . በሁኔታው በጣም ነው የደነገጥኩት እና ግራ የተጋባሁት” ብለዋል።
የዕድሜ ባለጸጋዎች መንከባከቢያ ማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ሊንድሴይ ሳርድ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ይህ የሆነው አዛውንቷ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ በሚገኙ የሜካፕ አጠቃቀም ማስተማሪ ቪዲዮዎች አማካኝነት ተነሳስተው የሠሩት ቪዲዮ በእንክብካቤ ቤቱ የቲክቶክ ገጽ ላይ ከተለጠፈ በኋላ ነው።
በመቶ ሺዎች ዕይታን ያገኘውን ቪዲዮ የተመለከተ አንድ ሰው የመዋቢ እቃዎቹን ያመረተውን ድርጅትን ጠቅሶ (ታግ አድርጎ) “ተመልከቱ ምርታችሁን እኚህ ሴት እየተጠቀሙት ነው” ማለቱን ተከትሎ ሌላ አዲስ ዕድል ተከፍቶላቸዋል።
ሰርድ እንደምትለው “እናም ጆአን እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲያደርጉ ማየቱ ያስደተው ኩባንያው፣ ከእኛ ጋር ተገናኘ። የመዋቢ እቃዎችንም በቀጥታ ለጆአን ለመላክ መፈለጉን አሳወቀን።”
- የምንጠቀማቸው ‘የሜክአፕ’ ዕቃዎች ምን ያህል አደገኛ እና የተበከሉ ናቸው?5 ሚያዚያ 2025
- በመድኃኒት እስከ 38 ኪሎ ውፍረት የቀነሱ ሴቶች ስለ ልምዳቸው ምን ይላሉ?7 ሚያዚያ 2025
- የእርግዝና መከላከያ ክኒን በእርግጥ ሴቶችን የበለጠ እንዲጨነቁ ሊያደርግ ይችላል?22 ሚያዚያ 2025

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ቪዲዮው ካገኘው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዕይታዎች በተጨማሪ ከተመልካቾች ዘንድ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አስተያየቶችን አግኝቷል። እንዲያውም በርካቶች አዛውንቷ ጆአን ተጨማሪ የውበት አጠባበቅ ትምህርቶችን እንዲያጋሯቸው ጠይቀዋል።
“ሁሉም ውብ፣ ደስ የሚያሰኙ አስተያየቶች ከወጣት ልጃገረዶች እና ትልልቅ ሴቶች ደርሰውሻል። ሁሉም እንዴት ቆንጆ እንደሆንሽ እና ቪዲዮሽን ምን ያህል እንደወደዱት የሚናገሩ ናቸው” ስትል ሰርድ ለአዛውነቷ ጆአን ነግራቸዋለች።
ጨምራም “ተጨማሪ ቪዲዮዎችን ከአንቺ ማየት ይፈልጋሉ” በማለት የደረሳቸውን አስተያየቶች እና በሰዎች ዘንድ የተፈጠረውን ስሜት ገልጻለች።
ቀልደኛዋ አዛውንትም “አይ፣ አይሆንም፣ በጣም ስላረጀሁ ወደ ሥራ መመለስ አይሆልኝም” ሲሉ ጆአን መልሰዋል።
ነገር ግን ጆአን የሚኖሩበት የአዛውንቶች እንክብካቤ ቤት የዕድሜ ባለጸጋዋ ቲክቶክ ያስገኘላቸውን አዲሱን የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪነት ሚና እንደሚደግፍ እና ተጨማሪ ቪዲዮዎችን ለመሥራት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጿል።
የአዛውንቷ የልጅ ልጅ ኒኮላ አያቷን ለመጎብኘት በመጣችበት ጊዜ ጆአን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያገኙት ዝና ለማመን የሚያስቸግር መሆኑን ተናግራለች።
“አያቴ ወደ እንክብካቤ ማዕከሉ በመጣችበት ወቅት ለመጎብኘት ስመጣ ዘና ያለ ጊዜ እንደሚኖረን አስቤ ነበር። አሁን ግን ያ የሚሆን አይመስለኝም፤ አያቴ አሁን በቲክቶክ ላይ በስፋት የሚታዩ ቪዲዮዎችን ለመሥራት ወስናለች።
“እናም ይህንን ከመደገፍ ወደ ኋላ ማለት አልችልም፤ ምክንያቱም በጣም ነው የምኮራባት። በጣም አስደናቂ ሴት ነች። ሁሌም ከአያቴ የማይገመት ነገር እንጠብቃለን” በማለት ለአያቷ ያላትን ድጋፍ እና አድናቆት ገልጻለች።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ዝናን እያገኙ ያሉት የዕድሜ ባለጸጋዋ ጆአን፣ በየትኛውም ዕድሜ ላይ ብንሆን መልካም ነገር መሥራት እና ውበትን መጠበቅ ስላለው ጥቅም ይናገራሉ።
“ለእኔ ውበት ማለት ተፈጥሮ ማለት ነው። ዕድሜያችን ምንም ይሁን ምንም ስለራሳችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ማድረግ ጥሩ ነው” በማለት ይመክራሉ።