
20 መጋቢት 2025
ተሻሽሏል ከ 2 ሰአት በፊት
ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ጦርነት ከባድ ውድመት የደረሰባት እና ደኅንነቷ ስጋት ውስጥ የወደቀባት ዩክሬን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ ድጋፍ በእጅጉ ተቀዛቅዞ ስጋት ውስጥ ቆይታለች።
ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለዩክሬን ሲሰጡ የነበረውን በቢሊዮን ዶላራች የሚቀጠር ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍን ያቋረጡ ሲሆን፣ ዜሌንስኪ የሚባሉትን ተቀብለው ከፑቲን ጋር ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በተጨማሪም ዩክሬን ብርቅዬ የሆኑ ውድ ማዕድናትን ለአሜሪካ እንድትሰጥ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ ቆይተዋል።
ባለፉት ወራት ይህንን በተመለከተ የአሜሪካ እና የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድርድር ሲያደርጉ ቆይተው ስምምነት ይፈረማል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ ቆይቷል።
በመጨረሻም አሁን የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ እና የዩክሬን የኢኮኖሚ ሚኒስትር ዋሽንግተን ውስጥ አሜሪካ በዩክሬን ተፈላጊ ማዕድናት ላይ ድርሻ እንዲኖራት የሚያስችል ውል ፈርመዋል።
ትራምፕ፣ አሜሪካ እስካሁን በጦርነቱ ለዩክሬን የሰጠችውን በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ድጋፍ በማዕድን ሀብቷ እንድትመልስ የነበራቸውን ፍላጎት እውን ለማድረግ ከጫፍ የደረሱ ይመስላሉ።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ባለፉት ወራት በተደረጉት ድርድሮች ላይ የአገራቸውን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ስምምነት ላለመፈረም ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም በመጨረሻ ግን ሁለቱንም ያስማማ ስምምነት መፈረሙ ተሰምቷል።
ማዕድናቱ ለምን ዓላማ ያገለግላሉ? ለአሜሪካስ ምን ይጠቅማሉ?

አሁን የተፈረመው ስምምነት
በአሜሪካ እና በዩክሬን መካከል ሲደረግ የነበረው ድርድር ከአግባቢ ወሳኝ ነጥብ ላይ መድረሱን ተከትሎ የዩክሬን የኢኮኖሚ ሚኒስትር ዩሊያ ስቪሪይድንኮ ወደ ከአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ (ገንዘብ ሚኒስትር) ጋር ስምምነት ለመፈራረም ወደ ዋሽንግትን አቅንተዋል።
ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም የኢኮኖሚ ሚኒስትሯ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ያያዛቸውን ነጥቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ዘርዝረዋል።
በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ስምምነቱ የምዕራባውያን መዋዕለ ነዋይ በዩክሬን የማዕድን፣ የጋዝ እና የነዳጅ ዘይት ፕሮጀክቶች ላይ የሚውል ድጋፍ የሚያስገኝ የመልሶ ግንባታ የኢንቨትመንት ፈንድ ይቋቋማል።
የዩክሬንን ሀብት ለመጋራት ስምምነት ቢደረስም የማዕድን ሀብቶቹ የዩክሬን ንብረት ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆን፣ ማዕድናቱ የሚወጡባቸውን አካባቢዎችንም የምትወስነው ዩክሬን ትሆናለች።
አጋርነቱ እኩል 50/50 በመሆን የሚለማ ሲሆን፣ በስምምነቱ ዩክሬን ለአሜሪካ ምንም ዓይነት የዕዳ ግዴታ እንደማይኖርባት ሚኒስትሯ አመልክተዋል።
በስምምነቱ አሜሪካ በዩክሬን ለሚካሄዱት ፕሮጀክቶች የሚውል መዋዕለ ነዋይ አፍሳሾችን እና ቴክኖሎጂን በማምጣት ሚና ይኖራታል።
- ዜሌንስኪ ክሬይሚያን ለሩሲያ አሳልፈው ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑ ‘እንደሚያስቡ’ ትራምፕ ተናገሩ28 ሚያዚያ 2025
- ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ ወታደሮችን ማሰማራቷን አመነች28 ሚያዚያ 2025
- ሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ስምምነቱን ‘ከባድ’ ካደረጉ አሜሪካ እንደማታሸማግል ትራምፕ ተናገሩ19 ሚያዚያ 2025
በተጨማሪም አሜሪካ የአየር መከላከያ ሥርዓትን ጨምሮ ለዩክሬን አዲስ የድጋፍ አቅርቦቶችን ልትሰጥ እንደምትችልም ተጠቅሷል።
አሁን በአሜሪካ እና በዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊ ለመሆን በዩክሬን ፓርላማ መጽደቅ ይኖርበታል።
ይህ ስምምነት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በድርድሩ ወቅት አጥብቀው ሲጠይቁ የነበረውን የደኅንነት ዋስትናን የሚሰጥ ስለመሆኑ እስካሁን በግልጽ የተባለ ነገር የለም።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ያወጣው መግለጫ ላይ ግን “ለሩሲያ የጦር እንቅስቃሴ የገንዘብ እና ሌላ ድጋፍ የሚያደርግ መንግሥትም ሆነ ግለሰብ በዩክሬን የመልሶ ግንባታ ሂደት ውስጥ ተጠቃሚ አይሆንም” ተብሎ ተጠቅሷል።
ትራምፕ በበኩላቸው አሁን የተደረሰው ስምምነት አሜሪካ ለጦርነቱ እስካሁን ያፈሰሰችውን ገንዘብ የሚያስመልስ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ‘ኒውስኔሽን’ ለተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ በስልክ እንደተናገሩት “ባይደን 350 ቢሊዮን ዶላር ሰጥቷቸዋል” ስምምነቱ ከዚያ በላይ የሚያገኙበት መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ዩክሬንን ለመደገፍ 350 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች በማለት በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ትክክለኛው መጠን እሳቸው ካሉት በእጅጉ ያነሰ ነው።
የአሜሪካ በዩክሬን ውስጥ መገኘት ሩሲያ በአካባቢው የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሊገታው ይችል እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ እንደዚያ እንደሚያስቡ አመልክተዋል።
ብርቅዬ ማዕድናት ምንድን ናቸው?
“ብርቅዬ ማዕድናት” በዘመናዊው ቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የ17 ተመሳሳይ ኬሚካል ንጥረ ነገሮች የጋራ ቃል ነው።
እነዚህ ንጥረ ነገሮች ስማርት ስልኮችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ የህክምና መሳሪያዎች እና ሌሎችንም ለማምረት ወሳኝ የሚባሉ ናቸው።
እነዚህም ስካንዲየም (Sc)፣ ይትሪየም (Y )፣ ላንታነም (La )፣ ሴሪየም (Ce)፣ ፕራሲዮድሚየም (Pr )፣ ኒዮዲሚየም (Nd )፣ ፕሮምቲየም (Pm )፣ ሳምሪየም (Sm)፣ ዩሮፒየም (Eu)፣ ጋዶሊኒየም (Gd)፣ ቴርቢየም (Tb)፣ ዳይስፕሮሲየም ( Dy )፣ ሆሊየም (Ho)፣ ኤርምየም ( Er ) ፣ ቱሊየም (Tm) እና ሉተቲየም (Lu ) ናቸው።
ማዕድኖቹ “ብርቅዬ” በመባል የሚታወቁት ንጹህ ሆነው ማግኘት በጣም ባለመለመዱ ነው። አንዳንዶቹ በመላው ዓለም ይገኛሉ።
ብርቅዬ ማዕድናቱ እንደ ቶሪየም እና ዩራኒየም ካሉ ራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ። በዚህ ምክንያትም ለመለየት ብዙ መርዛማ ኬሚካሎችን ይፈልጋል። ይህም የማውጣቱን ሂደት አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ እና ውድ ያደርገዋል።

ዩክሬን የትኞቹ ማዕድናት አሏት?
ዩክሬን በአውሮፓ ኅብረት “ወሳኝ ጥሬ እቃዎች” ተብለው ከተገለጹ 30 ንጥረ ነገሮች ውስጥ 21 ያህሉ ያሏት ሲሆን፣ ይህም 5 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ክምችት የሚይዝ ነው።
እነዚህ ንጥረ ነገሮች በአብዛኛዎቹ በደቡባዊ የዩክሬን ክሪስታል ሺልድ በዋነኛነትም በአዞቭ ባሕር ስር ይገኛሉ። አብዛኞቹ እነዚህ ግዛቶች በአሁኑ ጊዜ በሩሲያ ቁጥጥር ስር ናቸው።
እንደ ፎርብስ ዩክሬን ገለጻ ከሆነ 70 በመቶ ያህሉ በዶኔስክ፣ በዲንፕሮፐትሮቭስኪ እና ሉሃንስክ ግዛቶች የሚገኙ ናቸው። አብዛኞቹ እነዚህ ቦታዎች ደግሞ በሩስያ ቁጥጥር ስር ናቸው።
ብርቅ ከሚባሉት በተጨማሪ ዩክሬን በጣም ወሳኝ የሚባሉትን እንደ ሊቲየም ያሉ ማዕድናትም አሏት።
እንደ የዩክሬን መንግሥት ከሆነ አገሪቱ ወደ 450 ሺህ ቶን የሚጠጋ የሊቲየም ክምችት አላት። ማውጣት ለመጀመር ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ወደ ተግባር አልተገባም።
ሩሲያ ቢያንስ ሁለት የሊቲየም ክምችቶችን ተቆጣጥራለች።
በኪሮቮራድ ክልል የሚገኘው የሊቲየም ማዕድን ክምችት በዩክሬን ቁጥጥር ስር ነው።
ትራምፕ እነዚህን ማዕድናት ለምን ፈለጉ?
በአሜሪካ በኩል ብርቅዬ እና ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን ምርት ለመቆጣጠር ያለው ፍላጎት የሚመነጨው በአሁኑ ጊዜ የዓለምን አቅርቦት ከምትቆጣጠረው ከቻይና ጋር ባለው ውድድር ምክንያት ነው።
ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ቻይና ብርቅዬ ማዕድናትን በማውጣት እና በማቀነባበር ግንባር ቀደም ሆናለች።
ከ60 እስከ 70 በመቶ የዓለምን ምርት እና 90 በመቶ የሚሆነውን የማቀነባበር አቅምን ትሸፍናለች።
ከብሔራዊ ደኅንነት እና ከኢኮኖሚ አንፃር አሜሪካ በዚህ ጉዳይ በቻይና ላይ ያላት ጥገኝነት ለትራምፕ አስተዳደር አሳሳቢ ሊሆን ይችላል።
ከኤሌክትሪክ መኪናዎች እስከ ወታደራዊ መሳሪያዎች ያሉትን የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን ለመሥራት እነዚህ ቁሳቁሶች በጣም አስፈላጊ ናቸው።
ሁኔታው ሲታይ ተቃርኖ ይመስላል።
ትራምፕ የታዳሽ ኃይልን ሚደግፉ ፖሊሲዎችን በማስቀረት የነዳጅ ምርት እንዲስፋፋ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ ወደ ታዳሽ ኃይል ለሚደረገው ሽግግር ቁልፍ የሆኑትን ወሳኝ ማዕድናት ከየትኛውም ቦታ ማግኘትን ይፈልጋሉ።
እንዲህ ያሉት ማዕድናት ለኤሌክትሮኒክስ፣ ለወታደራዊ እና ለመርከብ መሳሪያዎች ከሁሉም በላይ ደግሞ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የመረጃ ማዕከሎችን ለመገንባት ወሳኝ ናቸው።

ትራምፕ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሠረተ ልማትን በአገራቸው ለማስፋፋት ትልቅ ግፊት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ የሆኑ በዋናነት እንደመዳብ፣ ሲሊከን፣ ፓላዲየም እና ብርቅዬ ማዕድናትን አቅርቦት ይጠይቃል።
ወሳኝ የሆኑ ማዕድናት አቅርቦት ማሽቆልቆል በመጀመሩ ምክንያት ለዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይል ዕድገት መቀዛቀዝ ዋና መንስኤ አንዱ ሆኗል።
ቻይና ብርቅዬዎቹን ጨምሮ የወሳኝ ማዕድናት ላይ የበላይነት መያዟ በአሜሪካ-ቻይና ጂኦፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ዋነኛው ምክንያት ነው ይላሉ ባለሙያዎች።
ለአስርተ ዓመታት የማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን እና እውቀቶችን በማዳበሯ ምክንያት ቻይና መቶ በመቶ የተጣራ የተፈጥሮ ግራፋይት እና ዲስፕሮሲየም አቅርቦትን፣ 70 በመቶ ኮባልትን እና 60 በመቶ የሚሆነውን የተቀነባበሩ ሊቲየም እና ማንጋኒዝ ትቆጣጠራለች ሲል የዓለም አቀፉ ታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ አስታውቋል።
በተጨማሪም በዋናነት ብርቅዬ ንጥረ ነገሮችን በአፍሪካ፣ በእስያ እና በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ በባለቤትነት በመያዝ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲኖራት ሆኗል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የወታደራዊ አገልግሎት ኮሚቴ በባይደን አስተዳደር ወቅት “የቻይናን እያደገ የመጣውን የዓለም የአቅርቦት ሰንሰለት ለመመከት አሜሪካ የራሷን ወሳኝ እና ስትራቴጂካዊ ማዕድናት አቅርቦት ማግኘቷ አስፈላጊ ነው” ብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር እንደ ዩክሬን እና ግሪንላንድ ያሉ ቦታዎችን ወደ አቅርቦቱ ሰንሰለቱ በማስገባት አዳዲስ ዘዴዎችን የሚጠቀም ይመስላል።