
ከ 4 ሰአት በፊት
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጥያቄ የአንድ አዛውንት ዕድሜን አስቆጥሯል። እነዚህ ጥያቄዎች መልካቸውን እየቀያየሩ አሁንም ድረስ አሉ። ከፊሎቹ ጥያቄዎች ምላሽ ሲያገኙ፣ ቀሪዎቹ አሁንም ድረስ እንደ አዲስ እየተጠየቁ አሉ።
የሠራተኞች ጥያቄ ጅማሮ በአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት ነው። ከእነዚህ ጥያቄዎች ቀዳሚዎቹ የሥራ ሁኔታን እና መደራጀትን የተመለከቱ ነበሩ። እነዚህ ጥያቄዎች በየመሥሪያ ቤታቸው ማኅበራትን የመመሥረት እና ለእነዚህ ማኅበራት ሕጋዊ ዕውቅና ማስገኘት ከጥያቄዎቻቸው ቀዳሚው ነበር።
በኢትዮጵያ ሠራተኞችን በደመወዝ ማስተዳደር የተጀመረው በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ነበር። ሆኖም ግን በአገሪቱ የግሉ ኢንዱስትሪ መነቃቃት የጀመረው በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው።
ነገር ግን ሠራተኞች የሚተዳደሩበት በመንግሥት ደረጃ የወጣ ሕግ እንዳልነበር፤ አቶ ተፈራ ኃይለ ሥላሴ “የኢንዱስትሪ እና የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ዕድገት” በተሰኘው መጣጥፋቸው ላይ አስፍረዋል።
አቶ ተፈራ በዚሁ መጣጥፋቸው “አሠሪው በመሰለው ደሞዝ እና የሥራ ሁኔታዎች ሠራተኛ የሚያስተዳድርበት አካሄድ ነበር የሰፈነው” ሲሉ ያክላሉ።
ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1936 ዓ.ም. የፋብሪካዎች መቆጣጠሪያ አዋጅ መውጣቱን አቶ ተፈራ ይገልጻሉ። የአዋጁ ዋና ትኩረት፤ “ፋብሪካዎች ስለሚሠሩበት ሁኔታ እና በውስጣቸው የሚተከሉት መሳሪያዎች በሠራተኞች ላይ አደጋ እንዳያደርሱ” መመሪያ ማውጣት ነበር።
“በ1952 ዓ.ም. ፍትሐ ብሔር ሕግ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የሠራተኞችን የሥራ ሁኔታዎችን የሚደነግጉ እና የሥራ ክርክሮች የሚፈቱበት ሥርዓት በማቋቋም ረገድ ምንም ዕድገት አልታየም” ሲሉ ያክላሉ።
የአሰሪ እና ሠራተኛ መብቶች እና ግዴታዎችን የደነገገው የፍትሐ ብሔር ሕግ፤ “የጌታ እና የሎሌ የነበረውን የአሠሪ እና ሠራተኛ ግንኙነትን” ማሻሻሉን አቶ ተፈራ ይገልጻሉ።
ነገር ግን የፍትሐ ብሔር ሕጉ መደበኛ የቀኑን እና የሳምንቱን የሥራ ሰዓቶች ባለመወሰኑ “ሠራተኛውን ለብዝብዛ አጋልጦታል።” የሥራ ክርክር የሚፈታበትን ሥርዓት አለማቋቋሙ ሌላኛው የፍትሐ ብሔር ሕጉ ውስንነት ነበር።
ከፍትሐ ብሔር ሕጉ መውጣት አራት ዓመት በኋላ እነዚህን ውስንነቶች የሚሸፍነው የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ በ1956 ዓ.ም. ወጣ። አዋጁን ተከትሎ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ያልተካተቱት የሥራ ሰዓት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የሕዝብ በዓላት፣ የዓመት ፈቃድን እና ሌሎች የሥራ ሁኔታዎችን በማሻሻል ደንብ ወጣ።
የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጁ የሠራተኛ ማኅበራትን በተመለከተም ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነበር። የፍትሐ ብሔር ሕጉ ሠራተኞች የሙያ የሥራ ማኅበር ማቋቋም እንደሚችሉ ቢደነግግም፤ የማኅበሩን ተግባራት ግን አልደነገገም ነበር።
ዶ/ር አዳነ ካሴ “The Formative Period of the Ethiopian Labour Movement, 1962-1974” በተሰኘ ጥናታዊ ጽሁፋቸው “በ1948 የተሻሻለው ሕገ መንግሥት እና የፍትሐ ብሔር ሕጉ ላይ አንዳንድ የሠራተኛ ጉዳዮች ቢካተቱም የሠራተኛ ግንኙነት ተገቢ ትኩረት አልተሰጠውም” ይላሉ።
- በፍልስጤም የተንቀሳቃሽ ትምህርት ቤት ዲዛይን ውድድር ‘ያሸነፉት’ ኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች26 ሚያዚያ 2025
- በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው ስለሚባለው ‘አፈሳ’ የነዋሪዎች ስጋት30 ሚያዚያ 2025
- በአቶ ጌታቸው የሚመራው ህወሓት ‘ትግራይ ሊብራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ የሚባል አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁም ነው29 ሚያዚያ 2025

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ሕገ መንግሥቱ ለሠራተኞች ማኅበር የማቋቋም መብት ቢሰጥም የፍትሐ ብሔር ሕጉ የሠራተኞች ማኅበራትን እንደ ሌሎች ማኅበራት ስለቆጠራቸው፤ የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ድንጋጌ እስከ ወጣበት ጊዜ ድረስ የአሠሪ እና የሠራተኞች ማኅበራት አልነበሩም።
ከዚህ ድንጋጌ በኋላ ግን በተለይ ሠራተኞች በማኅበር ተደራጅተው ሕጋዊ ዕውቅና አግኝተው ለመመዝገብ አፍታም አልወሰደባቸውም። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር (ኢሠአማ) ውልደቱን አገኘ።
ድንጋጌው ሠራተኞች የሠራተኛ ማኅበራትን የመመሥረት መብት ከመስጠቱ በተጨማሪ ለሠራተኛ ማኅበራት አመራሮች እንዲሁም ለሠራተኞች እኩል የመደራደር አቅምን ፈጥሯል።
አቶ ተፈራ ኃይለ ሥላሴ፤ “በትምህርት ደረጃ ከሠርቶ አደሩ ከፍ ብለው የሚታዩ” ያሏቸው (white collar workers) በማኅበር የመደራጀት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው ያስታውሳሉ።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ማኅበራትን እና በ100 ሺዎች አባላትን በስሩ የያዘው ኢሠአማ የሠራተኞችን ጥያቄ ለመንግሥት ለማቅረብ ዓመታት ፈጅቶበታል።
ከኢሠአማ ምሥረታ በኋላ ባሉት አስር ዓመታት ውስጥ ከሠራተኞች ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ጫን ያለ ጥያቄም ሆነ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ አልሰጠም።
ከመንግሥት በኩል በሠራተኞች እና በማኅበራት ላይ የሚያርፈውን ጡጫም በተመለከተ ተቃውሞውን አያሰማም ነበር።
ዶ/ር ሳሙኤል አንድሪያስ በፋብሪካዎች ውስጥ ያሉ የሠራተኛ ማኅበራት ለጠሯቸው የሥራ ማቆም አድማዎችም ድጋፉን እንደነፈጋቸው በአንድ ጥናታቸው ላይ አስፍረዋል።
ኢሠአማ ጠንካራ ጥያቄዎች ያቀረበው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ማገባደጃ ላይ ነው። ኢሠአማ በ1966 ዓ.ም. አጋማሽ 17 ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን አቀረበ።
እነዚህ ጥያቄዎች ግን የሠራተኛው መብት እና ጥቅም ላይ ያተኮሩ ብቻ አልነበሩም። ከአገሪቱ የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር የተያያዙ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችንም አካታትዋል።
ኢሠአማ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል፣ የደመወዝ ማሻሻያ፣ የሠራተኛ ጡረታ ፈንድ ከገቢ ታክስ ነፃ እንዲሆን፣ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ መባረር እንዲቀር፣ አዲስ ማኅበራትን መመሥረት እና የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ይገኙበታል።
ኢሠአማ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ “የሠራተኛው መብት እና ጥቅም እንዲጠበቅ በማለት በየጊዜው የተጠየቁት የሠራተኛው ጉዳዮች ምንም ዓይነት ውጤት ባለማግኘታቸው ለመጨረሻ ጊዜ” ጥያቄ ማቅረቡን ያትታል።
ኢሠአማ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መሠረት ምላሽ ባለማግኘቱ ለአራት ቀን የቆየ የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ።
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 1/1966 ዓ.ም. ከኢሠአማ ስምምነት ላይ ደረሱ።
ሆኖም ጥያቄዎቹ “በዚህ ያህል ጊዜ ለፓርላማ ይቀርባል፤ ይኼኛው ጥያቄ በኮሚቴ ይታያል” ከሚሉ ሽንገላዎች ውጪ ይሄ ነው የሚባል ተጨባጭ ምላሽ አልሰጠም።
አጼ ኃይለ ሥላሴ እና መንግሥታቸው ለሠራተኞች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጡ የየካቲት አብዮት እሳቸውንም ባለሟሎቻቸውንም ጠራርጎ ወሰዳቸው።
የኢሠአማ 17 ጥያቄዎች ለሠራተኛው በቀጥታ ካስገኙት ጥቅም ይልቅ በጥቅል ለሥርዓት ለውጥ ያበረከቱት ሚና የላቀ ነው።
ጥያቄዎቹም ሠራተኛውን ብቻ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ከሌሎች የሕብረተሰቡ ክፍሎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥያቄዎች ጋር ተዳብለው የቀረቡ ነበሩ።
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጥያቄ እና ደርግ
ከ50 ዓመት በፊት የፈነዳውን አብዮት ተከትሎ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የገባው ወታደራዊ መንግሥትም የሠራተኞችን ጥያቄ ያስተናገደበት አኳዃን፤ “ከእጅ አይሻል ዶማ” ዓይነት ነበር።
የቀድሞው የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊ ኢብራሂም፤ “በጠቅላላው የሠራተኛ ማኅበራት አጠቃላይ መብቶቻቸው ክፉኛ የተጣሱበት ሁኔታ ነበር” ይላሉ።
አቶ ዳዊ አክለውም፤ “የሠራተኛው እንቅስቃሴ ላይ በደርግ ጊዜ አንዲት ጸጋ ብቻ ናት የነበረችው፤ ይሄም የሠራተኛ ማኅበራቱ ቁሳዊ የሆነ መሠረት ጥሏል” ሲል ያክላሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አመራር የነበሩት አቶ ክፍሉ ታደሰ “የደርግ እና የሠራተኛው እንቅስቃሴ በቅራኔ የተሞላ ነበር” ይላሉ። ለዚህም በማሳያነት የሚያነሱት የሠራተኛ ማኅበራት ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች የደርግ ምላሽ በመሳሪያ የታጀበ መሆኑን ነው።
ዶ/ር ሳሙኤል አንድሪያስ ከአብዮቱ በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ያነሳሉ።
ከ1967 እስክ 1969 ባሉት ሦስት ተከታታይ መስከረሞች የሥራ ማቆም አድማዎች በተለያዩ የስኬት ደረጃዎች መደረጋቸውን፣ ነገር ግን አንዳቸውም ግን በ1966 ዓ.ም. የካቲት መጨረሻ ከተደረገው ጋር አይስተካከሉም ይላሉ።
የወታደራዊው መንግሥት አጸፋም የከፋ እንደነበር የሚገልጹት አጥኚው በ1967 በተሞከረው የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት 100 ሰዎች መደገላቸውን እና 1600 ሰዎች መታሰራቸውን ጽፈዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል “Trade Union Resurgence in Ethiopia” በተሰኘው ጥናታዊ ጽሁፋቸው በወታደራዊው አስተዳደር የሠራተኞች ደመወዝ ላይ ይሄ ነው የሚባል ለውጥ እንዳልነበር አስፍረዋል።

“የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ”
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ከአራት ሥርዓቶች በኋላም ከስልሳ ዓመታት በፊት ለጠየቋቸው ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አሁንም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን እየጠየቀ ነው።
የአገሪቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ጉልህ መሻሻል ቢያሳዩም የሠራተኞች ጥያቄ ግን አሁንም ባለበት እየረገጠ ነው። የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ የሠራተኛ ማኅበራትን ማደራጀት “ትልቅ ተግዳሮት” እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ።
አቶ ካሳሁን “ብናደራጅም ባደራጀነው ማግስት ይፈርሳል፤ አደራጅተን ስንመጣ መሪዎቹ ይባራራሉ እነሱን ወደ ሥራ ለማስመለስ ፍርድ ቤት እንመላለሳለን” ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።
የአቶ ካሳሁን አማካሪ የሆኑት የቀድሞው የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊም በተመሳሳይ፤ “ዛሬም ሠራተኞችን ለማደራጀት እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ይሄ ሁሉ ሕግ እያለ ማደራጀት አትችልም። ከተደራጀ በኋላ ያፈርሱታል ከተደራጀ በኋላ የማኅበር መሪ ያባርራሉ” ይላሉ።
ኢሠማኮ ሠራተኞችን ለማደረጃት ችግር የሚገጥመው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቋቋሙት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ነው።
አቶ ዳዊ “የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሠራተኞችን ለማደራጀት አምስት ዓመት ነው የፈጀው” ሲሉ ይናገራሉ። በተመሳሳይ አቶ ካሳሁን ፎሎ “ዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ 103 ድርጅቶች አሉ፤ እዚያ ውስጥ አንድም ሠራተኛ ማኅበር አልተደራጀም” ይላሉ።
“ዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ይወሰን የሚለው ጥያቄ የተነሳው በ1966 ዓ.ም. ነው። የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ቦርድ ተቋቁሞ ይወሰናል ነው ያለው። ነገር ግን ዛሬም ቦርድ ተቋቁሞ ይወሰናል እያልን ነው ያለነው” ሲሉ አቶ ዳዊ በምሬት ይናገራሉ።
አቶ ዳዊ ኢብራሂም የሠራተኞች ጥያቄ እስካሁን ድረስ ምላሽ ማግኘት ያልቻለው፤ “ኢትዮጵያ ሥርዓት መዘርጋት ስላልቻለች ነው” ይላሉ።
አቶ ክፍሉ ታደሰ በበኩላቸው ምክንያት የሚሉትን “ከደርግ ጀምሮ በንጉሡም ጊዜ ያው ነው፤ የመጡት ሁሉም ሥርዓቶች አምባገነኖች ናቸው፤ በነጻነት የሚደራጅ፣ በነጻነት ሃሳቡን የሚገልጽ፣ በነጻነት መሰብሰብ የሚችል፣ በነጻነት የሚተች፣ በምርጫ ሂደት ላይም የፈለገውን እመርጣለሁ የሚል አቆጥቁጦ እንዲያብብ አይፍልጉም” ሲሉ ያስቀምጣሉ።
“መብት አይሰጥም ይታገሉለታል እንጂ” የሚሉት አቶ ክፍሉ፤ “ሠራተኛው በራሱ ጉልበት በራሱ ጥረት መብቱን ካላስከበረ መንግሥት ለሠራተኛው ሊቆምለት አይችልም። ሠራተኛውን አደራጅቶ አደባባይ ወጥቶ መሞገት መቃወም ሃሳብን ማሰማት ያስፈልጋል” ሲሉ መፍትሄ ያሉትን ይጠቁማሉ።
ከ2015 ዓ.ም. የ“ሜይዴይ” ሰልፍ መከልከል በኋላ የሠራተኛው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል የሚል ተስፋ በኢሠማኮ አመራሮች በኩል ተፈጥሯል። ይህ ተስፋ የኢሠማኮ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ከተወያዩ በኋላ የመጣ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውይይቱ ወቅት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የሚወስነውን ቦርድ ለማቋቋም ቃል መግባታቸውን አቶ ካሳሁን ይገልጻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሠራተኞች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቃል በመግባት የመጀመሪያው መሪ አይደሉም። ከእሳቸው በፊት የነበሩ መሪዎችም ለሠራተኛው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፤ አሁንም ግን ሠራተኛው እነዚያኑ ጥያቄዎች እየጠየቀ ነው።
ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንደሚቋቋም የሚደነግገው አዲሱ የአሠሪ እና ሠራተኛ አዋጅ የጸደቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው።
ይህ አዋጅ ከጸደቀ አምስት ዓመታት ቢያልፉም እስካሁን ግን የደመወዝ ወለል አለመቋቋሙን ልብ ይሏል።
ከሃምሳ ዓመታት በፊት የተነሱት እና አሁንም ድረስ ሠራተኛው ያነገባቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ከዚህስ በኋላ ምላሽ ለማግኘት ምን ያህል ጊዜ ይጠይቅ ይሆን?
____
ይህ ጽሁፍ ከዚህ ቀደም ወጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ማሻሻያ ተደርጎበት በድጋሚ የቀረበ ነው።