የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች

ከ 24 ደቂቃዎች በፊት

በደቡብ አፍሪካ ከአርባ በላይ ኢትዮጵያውያን ያለፈቃዳቸው በአንድ ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው ዛሬ ሐሙስ ጠዋት ማግኘቱን የጆሃንስበርግ ፖሊስ አስታወቀ።

የአካባቢው ፖሊስ ቃል አቀባይ ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የፖሊስ አባላት በአካባቢው ቅኝት ሲያደርጉ የሰሙትን ድምጽ እና ጩኸት ተከትሎ ነው ሕገ ወጥ ስደተኞች ናቸው ያሏቸውን ኢትዮጵያውያን በተዘጋባቸው ቤት ውስጥ ማግኘት የተቻለው።

በጆሃንስበርግ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ በምትገኘው ሳንድተን የመኖሪያ አካባቢ በሚገኘው ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው የተገኙት ኢትዮጵያውያን 44 ናቸው።

ፖሊስ እንዳለው ከእነዚህ ሕገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል 27ቱ አዋቂዎች እና ቀሪዎቹ 17 ታዳጊ ልጆች ሲሆኑ፣ ፖሊስ ያሉበትን ማወቅ የቻለው በተዘጋ ቤት ውስጥ ሲጮኹ በተሰማው ድምጽ ነው።

ነገር ግን ከመካከላቸው እንግሊዝኛም ሆነ የአገሬውን ቋንቋ የሚናገር ባለመኖሩ አስተርጓሚ ተፈልጎ ዝርዝር መረጃ እስከሚገኝ ድረስ በተገኙበት ቤት ውስጥ እንዴት እንደገቡ እና ምን እንዳጋጠማቸው ለጊዜው ፖሊስ ለማወቅ እንዳልቻለ የፖሊስ ቃል አቀባይ ማቪላ ማሶንዶ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ያሉበት ቦታ በፖሊስ ታውቆ በተያዘበት ጊዜ፣ የቤቱ ባለቤትም ሆነ እዚያ ቤት ውስጥ ቆልፎ ያስቀመጣቸው ግለሰብ አልተገኘም ወይም አምልጧል ተብሎ ይታመናል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪካ አገራትን በማቋረጥ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚገቡ ሲሆን፣ በዚህ ሂደትም በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የተለያየ እንግልት እና ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ከዚህ በፊት የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል፤ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማድረስ የሚደረገው የሰዎች ዝውውር አሳሳቢ መሆኑን ከዚህ በፊት ገልጸው ነበር።

ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያቀኑት ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ጉዞ የሚያደርጉት እና እንዲቆዩ የሚደረጉበት ሁኔታ ለጤና እና ለሕይወት አደገኛ እንደሆነ ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ክስተቶች ያሳያሉ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ቢያንስ 64 ኢትዮጵያውያን በታፈነ ሁኔታ በተሽከርካሪ ሲጓዙ ሕይወታቸው አልፈ ሞዛምቢክ ውስጥ የተገኙ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይጓዙ የነበሩ የ30 ኢትዮጵያውያን አስከሬን በጅምላ ተቀብሮ መገኘቱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያውያኑ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፍሉ ሲሆን፣ በመንገድ ላይ ከባድ እንግልትን እንሚያልፉም ይነገራል።

ስደተኞቹ ደቡብ አፍሪካ ከደረሱ በኋላም ያለ በቂ ምግብ እና ውሃ ያለፈቃዳቸው በተጨናነቀ ሁኔታ በአንድ ስፍራ ታጉረው እንደሚቀመጡ ፖሊስ ከዚህ በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።

በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ በተመሳሳይ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በጆሃንስበርግ ከተማ በአንድ ቤት ውስጥ ታግተው የቆዩ እና ኢትዮጵያዊ ናቸው ተብሎ የሚታመኑ 26 ሰዎችን ማግኘቱን አስታወቆ ነበር።

በቤቱ ውስጥ ከተገኙት ስደተኞች መካከል አስራ አምስቱ እርቃናቸውን የነበሩ ሲሆን፣ በቤቱ አቅራቢያ የተገኙት ቀሪዎቹ 11 ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ፖሊስ በወቅቱ ገልጿል።