
30 ሚያዚያ 2025
ከሁለት ሳምንት በፊት ጀምሮ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ወጣቶች ከመንገድ እየታፈሱመሆናቸውን ወላጆች፣ ወጣቶች እና ፖለቲከኞች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየገለፁ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማ ነዋሪዎችም በግዳጅ የታፈሱ ወጣቶችን እንደሚያውቁ እና እነርሱም ባለባቸው ስጋት የተነሳ ድንገት ከተያዝን በሚል “ገንዘብ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ” ተናግረዋል።
ቢቢሲ ከአዲስ አበባ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በአዳማ ከተማ የሚገኝ እና ከመንገድ ላይ ታፍሰው ታጉረውበታል የተባለን አንድ መጋዘን ተመልክቷል።
ይህ የማጎርያ መጋዘን በመንግሥት ባለቤትነት ስር ያለ ሲሆን በርካታ ወጣቶች በአዳራሹ አካባቢ ተሰብስበው ይታያል።
የመጋዘኑ መግቢያ አካባቢ ሰዎች እንዳይቀርቡ ገመድ የተወጠረ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ሚሊሺያ የደንብ ልብስን የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ ያደርጉለታል።
ከመጋዘኑ ውጪ ልጆቻቸው እዚያ መጋዘን ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦች እንዲሁም ባሎቻቸው የተያዙባቸው ሴቶች ተሰብስበው ይታያሉ።
የተወሰኑት ሴቶች ጨቅላ ሕጻናትን ያዘሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው የሚሰጥ ውሃ እና ምግብ ይዘዋል።
ቢቢሲ በዚህ የማቆያ መጋዘን አካባቢ ከተሰበሰቡ ሰዎች እንደተረዳው ወጣቶቹ ከመንገድ ላይ ከታፈሱ በኋላ በፀጥታ አካላት ወደዚህ ቦታ የመጡ ናቸው።
በኅዳር ወር የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር አካላት እና የፀጥታ ኃይሎች ሕጻናት እና የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ በርካቶችን የመከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ በሚል በግዳጅ እንደያዙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በአዳማ ነዋሪ የሆነ እና ለደኅንነቱ በመስጋት ስሙን ከመናገር የተቆጠበ ወጣት ጓደኞቹ ከመንገድ ላይ ተይዘው መታሰራቸውን በመግለጽ እርሱም ስጋት እንደገባው ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግሯል።
“ከምሽቱ 1 ሰዓት ከሆነ መንገድ ላይ አስቁመው ይወስዱሃል። ማንም ለምን እንደተያዝክ አይነግርህም። በመኪና ጭነው ይወስዱሃል” ሲል ያለውን ሁኔታ ገልጿል።
አክሎም “ገንዘብ ካለህ ግን ከተያዝክ በኋላም የመለቀቅ ተስፋ አለህ” ይላል።
“ባለፈው ምሽት እንዴት እንደተረፍኩ እኔ እና ፈጣሪ ነን የምናውቀው። መያዝ ብቻ ሳይሆን ገንዘብ ትጠየቃለህ። እንድትለቀቅ የምትፈልግ ከሆነ ገንዘብ እንድትከፍል ትጠየቃለህ” ሲል ይናገራል።
በቅርቡ ጓደኞቹ የደረሰባቸውንም በመግለጽ ሲያስረዳ “ሦስት ጓደኞቼን ሳር ተራ [አዳማ] አካባቢ በቁጥጥር ስር አዋሏቸው። በአስር ሺዎች የሚቆጠር ብር ጉቦ እንዲከፍሉ ተጠየቁ። ከዚያም እነርሱ ለመልቀቅ የግድ ሦስት ሰዎችን መተካት ነበረባቸው፤ የእነርሱን ቦታ ከተማ ውስጥ ዞር ዞር ብለው ሌሎች ሦስት ሰዎችን ይዘው ካመጡ በኋላ ነው እነዚህ ሦስቱን የለቀቁት” ይላል።
- በኦሮሚያ ክልል ሕጻናትን ጨምሮ በርካቶች “ለመከላከያ ምልመላ” በሚል በግዳጅ መያዛቸው ተገለጸ5 ታህሳስ 2024
- በአቶ ጌታቸው የሚመራው ህወሓት ‘ትግራይ ሊብራል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ የሚባል አዲስ ፓርቲ ሊያቋቁም ነው29 ሚያዚያ 2025
- የቢቢሲን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ የኬንያ ፖሊስ እና መከላከያ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ዳግም ጥያቄ ቀረበ30 ሚያዚያ 2025
Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአዳማ የሚኖሩ ሌሎች ወጣቶች ድንገት በምሽት በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋልን በሚል ገንዘብ ይዘው አንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።
ይህ ስጋት የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቻቸውም መሆኑን የተናገረው የአዳማ ነዋሪ “ወጣት ነኝ፤ ቤተሰብ መሥርቻለሁ። ልጅ አለኝ። ከተያዝኩ በሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነኝ። ስለዚህ ሰዎች በብዛት ከሚታፈሱበት አካባቢ ርቄ ለመንቀሳቀስ እሞክራለሁ። ገፍቶ ከመጣ በሚል ደግሞ የምለቀቅበት ብር በኪሴ ይዤ እንቀሳቀሳለሁ” ይላል።
በአዳማ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የሚያውሏቸው ሰዎች ቁጥር ለእያንዳንዱ ፀጥታ አባል እና ወረዳ አመራር ተተምኖ የተሰጠ መሆኑን እነዚህ ግለሰቦች ይናገራሉ።
ቢቢሲ በአዳማ ከተማ የሚካሄደውን አፈሳ እንዲሁም በአስተዳደሩ ላይ ስለሚቀርቡ ውንጀላዎች በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዳማ ከተማ ነዋሪ “አመራሮቹ ምን ያህል ሰዎች እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯቸዋል፤ ስለዚህ ያገኙትን ያፍሳሉ። የተጣለባቸውን ኮታ ለመሙላት ሲሉ ጫማ በመጥረግ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ሊስትሮዎች ሳይቀር በቁጥጥር ስር ያውላሉ” ብለዋል።
ሌላ የአዳማ ከተማ ነዋሪ በበኩሉ በተለያዩ አካባቢዎች ከመንገድ ላይ የሚታፈሱ ወጣቶች ላይ ድብደባ እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደሚፈጸም ይናገራል።
ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊት እየታፈሱ በአዳራሽ ውስጥ ተይዘው ስለሚገኙ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት የግዳጅ ምልመላ ነው ስለሚባለው ጉዳይ ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
እስካሁን ድረስ የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ሆነ የፌደራል መንግሥት በግዳጅ እየታፈሱ ስለሚታሰሩ ሰዎች ያሉት ነገር የለም።
ከመከላከያ ሚኒስቴር የምልመላ መስፈርት ውጪ በግዳጅ የተያዙ ሕጻናትን እና ሰዎችን ለማስለቀቅ ቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ ጭምር እንዲከፍሉ ባለሥልጣናት ማስገደዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኅዳር 26/2017 ዓ.ም. በምርመራ እንደደረሰበት መግለጹ ይታወሳል።
በወቅቱ አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል የሚሊሻ አባላት ወጣቶችን ለመከላከያ ሠራዊት አባልነት ምልመላ በሚል ከያዙ በኋላ ለመልቀቅ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገደዱ መሆኑን ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በአንዳንድ አካቢዎች የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ከመስፈርት ውጪ የተደረገ ምልመላ መሆኑን በመግለጽ በክልሉ የፀጥታ አካላት የተያዙ ሰዎች ከማቆያ ስፍራዎች እንዲለቀቁ ያደረጉ መሆኑን መገንዘቡን ኢሰመኮ አመልክቷል።