
ከ 4 ሰአት በፊት
አፕል የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ አቅጣጫ በመከተል አብዛኛዎቹ በአሜሪካ የሚሸጡ አይፎኖች እና ሌሎች መሣሪያዎችን ከቻይና ውጭ ማምረት መጀመሩን አስታወቀ።
በመጪዎቹ ወራት ለአሜሪካ ገበያ የሚቀርቡት አብዛኛዎቹ አይፎኖች በሕንድ የሚመረቱ ሲሆን ቬትናም ደግሞ እንደ አይፓድ እና አፕል ዎች ላሉት ምርቶች ዋና ማዕከል ትሆናለች ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ቲም ኩክ ተናግረዋል።
ትራምፕ ቁልፍ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ከአዲሱ ታሪፍ ውጭ ለማደረግ ቢወስኑም ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም ወደ አሜሪካ ከሚያስገባቸው ምርቶቹ በዚህ ሩብ ዓመት ተጨማሪ ወደ 900 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊከፍል እንደሚችል ተገምቷል።
የትራምፕ አስተዳደር አፕል ማምረቻውን ወደ አሜሪካ እንዲያዘዋውር እንደሚፈልግ ደጋግሞ ተናግሯል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ኩባንያዎች በዋሽንግተን የንግድ ፖሊሲዎች ለተቀሰቀሰው ዓለም አቀፍ የንግድ ለውጥ ምላሽ ለመስጠት እየጣሩ ይገኛሉ።
ሐሙስ ዕለት ከባለሀብቶች ጋር ስለ ኩባንያው የፋይናንስ አፈጻጸም ውይይት ያደረጉት ቲም ኩክ ዋና ትኩረታቸውን በአሜሪካ ስላላቸው ኢንቨስትመንቶች ለማድረግ ያለሙ መስለዋል።
ኩክ ውይይቱን የከፈቱት ኩባንያው በሚቀጥሉት አራት ዓመታት በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች 500 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸውን ዕቅድ በማስታወስ ነው።
በተጨማሪም አፕል ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡ ምርቶችን የአቅርቦት ሰንሰለት እየቀየረ ቢሆንም በዚህ እርምጃ ዋነኛ ተጠቃሚ ለመሆን የተዘጋጁት ሕንድ እና ቬትናም ናቸው ብለዋል።
“በአሜሪካ ውስጥ የሚሸጡት አብዛኛዎቹ አይፎኖች የሚመሩበት አገር ሕንድ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን” ሲሉ ኩክ ተናግረዋል።
ቬትናም በበኩሏ “በአሜሪካ የሚሸጡት ሁሉም አይፓዶች፣ ማክ፣ አፕል ዎች እና ኤርፖዶች” ዋና የማምረቻ ማዕከል ትሆናለች።
ከአሜሪካ ውጭ ለሚሸጡት አብዛኛዎቹ ምርቶች ቻይና ዋና ማምረቻ አገር ሆና ትቀጥላለች ብለዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ “ታሪፍ እንደሚጥል” ካስታወቀ በኋላ የአፕል አክሲዮን ዋጋ አሽቆልቁሎ ነበር።
የታሪፉ ዓላማ ኩባንያዎች ማምረቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዲያዞሩ ለማድረግ ነው።
አስተዳደሩ ዕቅዶቹን እንዲያስተካክል ከፍተኛ ጫና ገጥሞት ነበር። ታሪፉ ሥራ ላይ ውሎ ብዙም ሳይቆይ ግን ስልክ እና ኮምፒውተሮችን ጨምሮ የተወሰኑ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ከታሪፍ ነጻ እንደሆኑ አስታውቋል።
- ያልተመለሰው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ጥያቄ ከትላንት እስከ ዛሬ1 ግንቦት 2025
- በመቶ ሺዎች ያስገጠሙት ማይክሮቺፕ በሰውነትዎ ውስጥ እንዲቀበር ይፈቅዳሉ?ከ 5 ሰአት በፊት
- ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸውን ከሥልጣን አንስተው ለተባበሩት መንግሥታት አምባሳደርነት በእጩነት አቀረቡከ 5 ሰአት በፊት
ለጊዜው በአሜሪካ እና በቻይና መካከል የተቀሰቀሰው የንግድ ጦርነት የአፕል ሽያጭ ላይ ተጽዕኖ አላሳደረም።
ኩባንያው በዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቋል።
አማዞን የሚደርስበትን ጫና ለማወቅ ሪፖርቱ በትኩረት ሲጠበቅ ቢቆይም ሽያጩ ባለበት መቀጠሉ ተናግሯል።
በዚህም በቀዳሚው ሩብ ዓመት በሰሜን አሜሪካ ያለው የኢ-ኮሜርስ ንግድ ከአምናው 8 በመቶ ከፍ ብሏል።
በሚቀጥሉት ወራትም ተመሳሳይ እድገት እንደሚያስመዘገብ ተገምቷል።
የአማዞን ኃላፊ አንዲ ጃሲ እንዳሉት ኩባንያው እንደ ኮቪድ ወረርሽኙ ባሉ ክስተቶች ወቅት ከበፊቱ የበለጠ ጠንካራ ሆኖ መውጣት ቢችልም “ታሪፎች ስለመረጋጋታቸው እና መቼ እንደሚሆን ማናችንም አናውቅም” ብለዋል።
“ብዙውን ጊዜ ፈታኝ ሁኔታዎችን ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ማስተናገድ እንችላለን። ይህ እንደገና ሊከሰት ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”
የሞር ኢንሳይትስ እና ስትራቴጂ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓትሪክ ሙርሄድ እንዳሉት የአይፎን አቅርቦት ሰንሰለት ወደ ሕንድ መቀየሩ “አስደናቂ” ነው።
“ይህ ከጥቂት ዓመታት በፊት (ኩክ) ቻይና ብቻ አይፎን ታመርታለች ከሚለው የተቀየረ ነው” ሲሉ ሙርሄድ ተናግሯል።
“አፕል ማሳየት ያለበት ብዙ ለውጥ ቢኖርም፣ ይህ ግን በጣም ጥሩ ጅምር ነው” ብለዋል።