
ከ 1 ሰአት በፊት
ከሁለት ወራት በፊት እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባ ምግብ፣ ነዳጅ እንዲሁም መድሃኒትን ሙሉ በሙሉ አገደች።
ከጥቂት ጊዜ በኋላም ከሃማስ ጋር ለሁለት ወራት ያህል የቆየው የተኩስ አቁም አብቅቶ ወታደራዊ ጥቃቶች ተጠናክረው ቀጠሉ።
እስራኤል ይህንን የምታደርገው ሃማስ ያገታቸውን እስራኤላውያን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ መሆኑን ትገልጻለች።
የዓለም ምግብ ድርጅት እና የፍልስጤማውያን ስደተኞች ድርጅት በቅርቡ ያላቸውን የምግብ ክምችት በሙሉ ተጠቅመው መጨረሳቸውን ገልፀዋል።
በዚህም የተነሳ እስራኤል በጋዛ የጣለችውን እገዳ እንድታነሳ ዓለም አቀፍ ጫናዎች እየጨመሩ ናቸው።
በጋዛ የጅምላ ረሃብ አይቀሬ መሆኑን የሚገልጹ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሰላማዊ ሰዎችን ሆን ብሎ ማስራብ የጦር ወንጀል ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በጋዛ የሚገኙ የመመገቢያ ማዕከላትን የሚደግፈው መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ድርጅት አኔራ ቡድን መሪ የሆኑት ሳሚ ማታራ “ሰዎች እኛ በምናቀርብላቸው ምግብ ላይ ነው ተደግፈው ያሉት። በገበያው ላይ ያለውን ገዝተው ለመመገብ ምንም የገቢ ምንጭ የላቸውም። በገበያውም ቢሆን ምግብ እምብዛም አይገኝም” ይላሉ።
“ከዚህ በፊት ሩዝ በስጋ እናበስል ነበር።አሁን እርዳታ እንዳይገባ ስለታገደ ስጋም ሆነ አትክልት የለም።”
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታዎች ኃላፊ ቶም ፍሌቸር “እርዳታ እና የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወትን ማትረፍ ለድርድር መቅረብ የለባቸውም” ሲሉ ሐሙስ ዕለት አስጠንቅቀዋል።
“እርዳታ ማገድ ሰላማዊ ዜጎች እንዲራቡ ያደርጋል።ያለ መሰረታዊ ሕክምና ድጋፍ ያስቀራቸዋል። ክብራቸውን እና ተስፋቸውን ይገፍፋል። ጭካኔ የተሞላበት የጋራ ቅጣተን ያንጸባርቃል። እርዳታን ማገድ ይገድላል።”
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች ጥቂት የመመገቢያ ማዕከሎች በሚሰጡት ድጋፍ ላይ ነው ሕይወታቸውን የመሰረቱት።
በካሃን ዩኒስ የሚገኘው በአሜሪካን ኒር ኢስት ሪፊውጂ (አኔራ) የሚደገፈው ማዕከል በየዕለቱ 6000 ያህል ሰዎችን ይመግባል።
እስራኤል ለረዥም ጊዜ የቆየውን እገዳ ካላነሳች በቅርቡ ለጋዛውያን ብቸኛ ተስፋ የሆነው የምገባ ማዕከል ለሚመግባቸው ዜጎች የሚያቀርበው አይኖርም።
በምገባ ማዕከሎቹ መጋዘን ውስጥ ያለው ምግብ ክምችት እየተሟጠጠ ነው።

- ቀጣዩ የኢራን እና የአሜሪካ የኒውክሌር ድርድር ተራዘመከ 2 ሰአት በፊት
- በመቶ ሺዎች ያስገጠሙት ማይክሮቺፕ በሰውነትዎ ውስጥ እንዲቀበር ይፈቅዳሉ?ከ 5 ሰአት በፊት
- የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት በዩክሬን የሚካሄደው ጦርነት “በቅርብ ጊዜ ውስጥ” አይቆምም አሉከ 4 ሰአት በፊት
ማታራ የእርዳታ ድርጅቱን ባዶ መጋዘን እያሳዩ “የሚቀጥሉት ቀናት በጣም ወሳኝ ናቸው።ሁለት ሳምነት አልያም ከዚያ ያነሳ ጊዜ የሚቆይ ምግብ ብቻ ነው ያለን” ብለዋል።
“በየሳምንቱ ከመቶ በላይ ምግብ እና የንጽህና እቃዎችን የያዙ የጭነት መኪናዎችን እንቀበል ነበር።አሁን ምንም የለንም” ብለዋል።
“ለማኅበረሰብ መመገብያ ማዕከላት ሩዝ፣ምስር፣ፓስታ፣የምግብ ዘይት እና ጨው ማቅረብ አልቻልንም፤አንድ ኪሎ የማገዶ አንጨት መግዛት በጣም ውድ ሆኗል፤በየዕለቱ ምግብ ለማብሰል 700 ኪሎ ግራም ማገዶ ያስፍልገናል።”
እስራኤል ሃማስ ለተዋጊዎቹ ለመስጠት ሲል የሰብኣዊ እርዳታዎችን ዘርፎ ያከማቻል፤አልያም ገንዘብ ለመሰብሰብ ይሸጣል ስትል ትወነጅለዋለች።
የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ኤጀንሲዎች እርዳታ ወደ ሌሎች አካላት ይሄዳል የሚለውን ክስ ጥብቅ የሆነ የቁጥጥር ስርዓት እንዳላቸው በመግለጽ ያስተባብላሉ።
ማታራ በኮምፒውተራቸው ላይ የእርዳታ ተቀባዮችን ዝርዝር እየተመለከቱ “ከማንኛውም ወገን የሚመጣን ጣልቃ ገብነት ለማስወገድ በርትተን እየሰራን ነው። ትክክለኛ እና ጠንካራ የሆነ የስርጭት ሂደት አለን” ይላሉ።
“በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እርዳታ የሚቀበሉ ሰዎች ስም ዝርዝር፣ መታወቂያ ቁጥር እና አድራሻ ከተጠለሉበት ካምፕ መለያ ጋር አለን። ይህ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚሰሩት ስራ ጋር መደራረብ እንዳይኖር እና ግልጽነት ለማስፈን ይረዳል” ሲሉ ያክላሉ።

የመመገቢያ ማዕከሉ የሚያበስላቸውን ምግቦች በአህያ ጭኖ እርዳታው የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ወደ ሚገኙበት አል ማዋሲ ያጓጉዛል።
በባህር ዳርቻው አቅራብያ የሚገኘው አል ማዋሲ በጣም በተጨናነቀ ሁኔታ የሚኖሩ ተፈናቃዮች የሚገኙበት ሲሆን የምግብ እርዳታ ስርጭቱን የሚቆጣጠሩ ሰዎች በቦታው ይገኛሉ።
በክራች የሚንቀሳቀሱ አዛውንት ለሰባት ቤተሰቦቻቸው የሚሆን ሁለት እሽግ ምግብ ተቀብለው “ተመስገን አምላኬ ይህ ይበቃናል” ብለዋል።
“ስላለው ሁኔታ አትጠይቀኝ” ያሉት እኚህ አዛውንት ” ሞት አልወስድ ስላላን ብቻ ነው እየኖርን ያለነው። እውነቴን ነው የምልህ ከማለዳው ጀምሮ ቁራሽ ዳቦ እየፈለግኩ ነበር። ምንም የሚላስ የሚቀመስ ለማግኘት ተቸግሬ ነበር” ብለዋል።
ሌላ ፊታቸው ላይ ስጋት የሚነበብባቸው እናት “ያለው ሁኔታ አሳዛኝ ነው። እና ደግሞ እየባሰ ነው የሚሄደው”
“ሕይወት እዚህ አሳፋሪ ነው። መስራት ያልቻሉ ወንዶች አሉን። ምንም ገቢ የለም፤ በዚያም ላይ እቃዎች ሁሉ ውድ ናቸው። ምንም ነገር መግዛት አልቻልንም”
የተሰጣቸውን ትኩስ ምግብ እየተመለከቱ “በዚህ ሰዓት ይህ ምርጡ ነገር ነው” ብለዋል።
“ማብሰያ የለም። የምናበስለው ምግብ የለም፤ ሻይ እንኳ ለመጠጣት ስንፈልግ ቅጠል ለቅሜ በማያያዝ ነው የማፈላው” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በጋዛ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ከስድት ወር አልፎታል።
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን በመግደል 251 አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሔድ የጀመረችው።
በጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ52,400 በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን የግዛቲቱ ጤና ሚኒስቴር ይናገራል።
እስራኤል ሐማስ ላይ የሚደረግ ወታደራዊ ጫና በቁጥጥሩ ስር የሚገኙ 59 ታጋቾችን ለማስለቀቅ ያግዛል ትላለች።
ከ2.1 ሚሊዮን ዜጎች መካከል 90 በመቶዎቹ ከመኖርያ ቀያቸው የተሰደዱ ሲሆን አብዛኞቹ በተደጋጋሚ የተፈናቀሉ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት እስራኤል በጣለችው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እገዳ፣ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲሁም ከመጋቢት 18 ጀምሮ መኖሪያቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ ከተደረጉ 500,000 ዜጎች ጋር ተያይዞ አሁን ያለው ሁኔታ “የከፋ” መሆኑን አስጠንቅቋል።
ሰላማዊ ዜጎችን ማስራብ የጦር ወንጀል ነው ያሉት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እስራኤል የጣለችውን የሰብዓዊ እርዳታ እገዳ እንድታነሳ ጫና እያደረጉ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት በተቆጣጠረቻቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ጋዛውያን እርዳታ እንዲገባ የማድረግ ኃላፊነት አለባት ሲል ተናግሯል።
ባለፈው ሳምንት አርብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ለጋዛ መልካም መሆን ይጠበቅብናል” በማለት ምግብ እና መድሃኒት ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገባ ግፊት አድርገዋል።
እስራኤል ለአሜሪካ ጥያቄ ይፋዊ ምላሽ ባትሰጥም በዚህ ሳምንት ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ጀመርን በእርዳታ እገዳው ላይ ላቀረቡት ወቀሳ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ አጣጥሎ ምላሽ ሰጥቷል።
በአልማዋሲ መጠለያ ካምፕ በሳሚ ማታር እና በመመገቢያ ማዕከላቱ ሰራተኞች ዙርያ ተሰባስበው የሚጫወቱ ሕጻናት በጣም የተጎዱ እና የከሱ ናቸው።
በጋዛ በተለይ ደግሞ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ የምግብ እጥረት መኖሩ ተገልጿል።
ማታራ በእርሳቸው እና በሠራተኞቻቸው ላይ ወደቀውን ኃላፊነት በማንሳት “ያለን አቅርቦት ካለቀ ምን እንደሚሆን አላውቅም” ይላሉ።
“ለሰዎቹ ወሳኝ የሆነውን እርዳታ እንደሚቆም ማሰብ ለእኔም ሆነ ለባልደረቦቼ በጣም ጭንቀት እና ድባቴ የሚፈጥር ስሜት አለው” ይላሉ።
“አስቸኳይ ተማጽኖ አለን'” ሲሉ በመቀጠል፣ “ተመልከቱን፣ ተስፋ መቁረጣችንን ተረዱ፤ ጊዜ ጥሎን እየበረረ መሆኑን ተረዱ። እባካችሁ መተላለፊያውን እንድትከፍቱ እንፈልጋለን” ሲሉ ተማጽኗቸውን አቅርበዋል።