
ከ 4 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት “በቅርብ ጊዜ ውስጥ አይቆምም” ሲሉ ተናገሩ።
ቫንስ የአሜሪካ አስተዳደር የተደቀነበት ጥያቄ ለሦስት ዓመታት ያህል የዘለቀው ጦርነት እንዲቆም ለማስቻል ሩሲያ እና ዩክሬን “እንዴት ወደ መካከል” ማምጣት ይቻላል የሚለው መሆኑን አብራርተዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም “እነርሱ [ሩሲያ እና ዩክሬን] ወደ ስምምነት መጥተው ይህንን ከባድ ጦርነት የማቆም ኃላፊነት አለባቸው” ብለዋል።
የቫንስ አስተየየት የተሰማው ኪየቭ እና ዋሺንግተን አሜሪካ የደህንንት ድጋፍ ለማድረግ በምላሹ የዩክሬንን ብርቅዬ ማዕድናት ትርፍ ለመጋራት ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ነው።
ቫንስ ይህንን አስተየየት የሰጡት ከፎክስ ኒውስ ጋር የትራምፕን አስተዳደር በሚመለከት ረዘም ያለ ቃለምልልስ ባደረጉበት ወቅት ሲሆን አስተዳደሩ የዩክሬን ጦርነትን የያዘበትን መንገድ ተከላክለዋል።
“እውነት ነው [ዩክሬናውያን] በመወረራቸው ተናድደዋል” ያሉት ቫንስ ” ነገር ግን ለጥቂት ማይሎች ግዛት በሚል በዚህም በዚያም በኩል በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን እያጣን መቀጠል አለብን?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ትራምፕ በዚህ ሳምንት ዩክሬን ምናልባት ሩሲያ እአአ በ2014 በወረራ የያዘችባትን ክሬሚያን የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚል አሳልፋ ለመስጠት ትፈልግ ይሆናል ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከዚህ ቀደም ግን የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ በኃይል የተቆጣጠረችውን ግዛት እንደማይሰጡ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በማጣቀስ ተናግረዋል።
- በመቶ ሺዎች ያስገጠሙት ማይክሮቺፕ በሰውነትዎ ውስጥ እንዲቀበር ይፈቅዳሉ?ከ 5 ሰአት በፊት
- ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪያቸውን ከሥልጣን አንስተው ለተባበሩት መንግሥታት አምባሳደርነት በእጩነት አቀረቡከ 5 ሰአት በፊት
- አብዛኛዎቹ በአሜሪካ የሚሸጡት አይፎኖች በቻይና እንደማይመረቱ አፕል ገለጸከ 4 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሐሙስ ዕለት ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ሌላ ቃለ ምልልስ ላይ በሁለቱ አገራት ግጭት ላይ በቅርቡ “መግባባት” ላይ መደረስ እንዳለበት ተናግረው ነበር።
አለበለዚያ ግን አሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ዶናልድ ትራምፕ “በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንዳለብን መወሰን ይኖርባቸዋል” ብለው ነበር።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ሳምንት ለሦስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ማወጃቸው ይታወሳል።
የተኩስ አቁሙ የሚደረገው የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያበቃበትን በዓል ታሳቢ በማድረግ ሲሆን ሚያዝያ 30/2017 ዓ.ም. የሚጀምር ይሆናል።
የዩክሬኑ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ የፑቲንን መግለጫ ተከትሎ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ወድያውኑ ጠይቀዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ሐሙስ እለት ማታ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የዩክሬን ደቡብ ምስራቅ ከተማን ደብድበው 14 ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል።
ሞስኮ በበኩሏ ዩክሬን በገበያ ስፍራ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ፈፍማለች ስትል ትከስሳለች።
እንደ ሩሲያ ባለስልጣናት ገለፃ ከሆነ ሩሲያ በምትቆጣጣረው ደቡብ ዩክሬን በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሰባት ሲገደሉ 20 ደግሞ ተጎድተዋል።
ኪየቭ ውንጀላውን ያስተባበለች ሲሆን ጥቃቱ ወታደሮችን ዒላማ ያደረገ ነበር ብላለች።