የአውድሬ ባኬበርግ ምስል

ከ 4 ሰአት በፊት

ለ63 ዓመታት ጠፍታ የነበረችው ሴት በሕይወት እና በጤና መገኘቷን የአሜሪካዋ ዊስኮንሲን ፖሊስ አስታወቀ።

ግለሰቧ ደብዛዋ ጠፍቶ ከነበረበት የተገኘችው ፖሊስ ዳግም መዝገቧን መመርመር ከጀመረ በኋላ ነው።

አውድሪ ባኬበርግ በጠፋችበት ወቅት የ20 ዓመት ወጣት የነበረች ሲሆን፣ ሪድስበርግ በተባለች አነስተኛ ከተማ ከምትኖርበት ቤት እአአ ሐምሌ 7/1962 መውጣቷ በመዝገቧ ላይ ሰፍሯል።

የሳኡክ ካውንቲ ፖሊስ ቺፕ ሜይስተር እንዳሉት የባኬበርግ መጥፋት” ከወንጀል ጋር ወይንም ከማጭበርበር ጋር የተያያዘ ሳይሆን በራሷ ፈቃድ ነው።”

ከዊስኮንሲን ወጣ ባለ ስፍራ ትኖር ነበር ያሉት የፖሊስ ባልደረባው ተጨማሪ ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የጠፉ ሰዎችን የሚያፈላልገው መንግሥታዊ ያልሆነው ዊስኮንሲን የጠፉ ሰዎች አፈላላጊ ቡድን ባኬበርግ በጠፋችበት ወቅት ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ነበረች ብሏል።

ቡድኑ ግለሰቧ ከመጥፋቷ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ‘ባሌ ይደበድበኛል፣ ሊገለኝ ዝቶብኛል’ ስትል አመልክታ ነበር።

የ82 ዓመት አዛውንቷ ባኬርበርግ በ15 ዓመቷ ትዳር መመስረቷን ቡድኑ አክሎ ገልጿል።

በጠፋችበት ዕለት ከምትሰራበት ፋብሪካ ደመወዟን ለመቀበል ብላ ከቤት መውጣቷ በተጨማሪ ተገልጿል።

በወቅቱ የባለትዳሮቹ ሞግዚት የሆነችው የ14 ዓመት ታዳጊ እና ባኬበርግ የዊስኮንሲን ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ማዲሰን፣ ከዚያም ወደ 480 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ኢንዲያናፖሊስ የሚወስዳቸው አውቶብስ መሳፈራቸው ተገልጿል።

በዚህ ወቅት ሞግዚቷ በመረበሿ የተነሳ መመለስ ብትፈልግም ባኬበርግ ግን አሻፈረኝ በማለት ከአውቶቡስ መናሀሪያው ወጥታ ሄዳለች።

የሳኡክ ካውንቲ ፖሊስ ቢሮ መርማሪ በርካታ ፍንጮችን በመከተል ምርመራ ማድረጉ የተገለፀ ቢሆንም ምንም ተጨባጭ ማስረጃ ሳያገኝ ስድስት አስርት ዓመታት አልፈዋል።

ፖሊስ ያረጀውን ፋይል አቧራ ዳግም በዚህ ዓመት አራግፎ አጠቃላይ ክለሳ ካደረገ በኋላ ፍንጮች መገኘታቸው ተገልጿል።

በምርመራው የተሳተፈው ፖሊስ አይዛክ ሀንሰን ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን እንደተናገረው በኦንላየን ላይ የተገኘ የባኬበርግ እህት የዘር ግንድን የሚያሳይ መረጃ የጠፋችውን ሴት በማግኘት ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ባኬበርግ የምትኖርበት ከተማን ፖሊስ ማናገሩን የገለፀው ሃንሰን ከእርሷ ጋርም በስልክ ለ45 ደቂቃዎች ማውራቱን ተናግሯል።

“ይመስለኛል ዝም ብላ ወጥታ ነው የሄደችው፤ አለ አይደል ከነገሮች ለመሸሽ እና የራሷን ሕይወት ለመምራት” ሲል ከአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ ምልልስ ባደረገበት ወቅት አብራርቷል።

አክሎም “ደስተኛ ትመስላለች። በውሳኔዋ በራስ መተማማን አላት። ምንም ፀፀት የለባትም።”