ተብላልተው የሚዘጋጁ ምግቦች እና መጠጦች

ከ 4 ሰአት በፊት

የሰው ልጅ የተብላሉ ምግቦችን መመገብ የጀመረው ጥንት ነው። የተብላሉ ምግቦች ለጤናችን ጎጂ ወይስ ጠቃሚ የሚለው ጥያቄ ግን ብዙ የከረመ አይደለም።

በተለያዩ ሕዝቦች እና ባሕሎች ውስጥ ያሉ ምግቦች ይዘታቸው ይለያይ እንጂ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ከተብላሉ በኋላ ለገበያ ወይም ለምግብነት መቅረባቸው ነው።

የሰው ልጅ ምግብ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ለማድረግ ነው ማብላላት አሊያም መዘፍዘፍ የሚለውን መላ ያመጡት። ለዚህ ነው ጋብርኤል ቪንዴሮላ “እያንዳንዱ ባሕል ምግብ የሚያብላላበት የራሱ መንገድ አለው” የሚሉት።

በአርጀንቲና ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጋብርኤል “አሁን አሁን ምግብን ማብላላት እየተለመደ መጥቷል። አልፎም በኢንዱስትሪ ደረጃ ምግብን ማብላላት ተጀምሯል” ይላሉ።

ምግብን ከማዕድ ቤታችን ይልቅ በኢንዱስትሪ ደረጃ አብላልቶ ማስቀመጥ የራሱ ጥቅሞች እና ጉዳቶች አሉት። ይህ መንገድ ኬሚካል ያላቸው ማቆያዎችን ባይጠቀምም ተጨማሪ ነገሮች እንደሚጨመሩት ኪንግስ ኮሌጅ ለንደን በቅርቡ በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሱፐርማርኬቶችን በመዳሰስ ያወጣው ጥናት ይጠቁማል።

ሕጉ በሚፈቅደው መጠን ሰው ሰራሽ ማጣፈጫ፣ ስኳር እና ጨው በእነዚህ ምግቦች ላይ ይጨመርባቸዋል።

ታድያ እኒህ የተብላሉ ምግቦች ለጤናችን ጠቃሚ ናቸው ወይንስ ልክ በፋብሪካ እንደተዘጋጁ (ፕሮሰስድ) ምግቦች ከምግብ ሳህናችን ላይ ልናወስግዳቸው ይገባል?

የተብላሉ ምግቦች

የተብላሉ ምግቦች ጥቅም

የሰው ልጅ ምግብን የማብላላት ጠቀሜታን በሳይንሳዊ መንገድ አጥንቶ መረዳት የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። በምዕራቡ ዓለም ለተብላሉ ምግቦች ያለው ፍላጎት እየጨመረ የመጣው በጤና እና በሰው አካል የመፍጨት አቅም መካከል ያለው ግንኙነት ግልፅ እየሆነ ስለመጣ ይመስላል።

ምግብ ማብላላት አሊያም በእንግሊዝኛው ‘ፈርሜንቴሽን’ የምንለው ሒደት እንደ ስታርች እና ስኳር ያሉ ካርቦሀይድሬቶችን በባክቴሪያ እና በእርሾ (ይስት) የመሰባበር መንገድ ነው።

ምግብን ለማብላላት ጥቅም ላይ የሚውሉ በጣም በርካታ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ እርጎ ትልቅ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

“ምግብን ማብላላት አዳዲስ ውህድ ይዘቶችን (ባዮአክቲቭ ኮምፓውንድስ) ሊፈጥር ይችላል። ኦርጋኒክ አሲድ እና ፔፕታይድ ምግብ ሲብላላ የሚገኙ ለጤናችን ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች ናቸው” ይላሉ አየርላንድ የሚገኙት የምግብ ተመራማሪ ፖል ኮተር።

አንዳንድ የተብላሉ ምግቦች ካልተብላሉ ምግቦች ጋር ሲነፃፀሩ ብዙ የምግብ ይዘት (ኒውትሪሽን) አላቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ፕሮባዮቲክ የሆኑ ለመፈጨት የቀለሉ ናቸው።

የተብላሉ ምግቦች በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ። በሕይወት ያለ ባክቴሪያ ያላቸው እና ባክቴሪያ መብላላት ላይ ሳለ የሞተባቸው ይባላሉ። ዳቦ፣ ቢራ እና ወይን የሞተ ባክቴሪያ ካላቸው መካከል ናቸው።

በሕይወት ያለ ባክቴሪያ ያላቸውን ምግቦች ስንመገብ ባክቴሪያ ‘ጉት ሚርክሮቢዮታ’ የተባለው የአፈጫጨት ሥርዓት አካል ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ለጤናችን ጠቃሚ ነው። ሰውነታችን ውስጥ ጠቃሚ የሚባሉ ባክቴሪያዎችን ሊቀላቀል ይችላል።

የተብላላው ምግብ በሕይወት ያለ ባክቴሪያ ባይኖረው እንኳ ለጤና ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ይላሉ ቪንዴሮላ። ባክቴሪያዎቹ ከመሞታቸው በፊት እንደ ፔፕታይድስ ያሉ ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ሞሌኪዩሎችን ያመርታሉ።

ነገር ግን እኒህ የጤና ጥቅሞች በሁሉም የተብላሉ ምግብና መጠጦች አሉ ማለት አይደለም።

የተብላሉ ምግቦች

የተብላሉ ምቦግቦች የአፈጫጨት ሥርዓታችንን ያግዛሉ?

የምግብ አፈጫጨት ጉዳይ በሳይንቲስቶች ዘንድ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ በርካታ ሰዎች በቂ አሰር (ፋይበር) ያለው ምግብ አይመገቡም። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በርካታ ሰዎች ከአፈጫጨት ችግሮች ቢያንስ አንዱ አለባቸው።

የተብላሉ ምግቦች በአንዳንድ ሰዎች ላይ የአፈጫጨት ችግር ሊያመጡ የሚችሉ የይዘት ውህዶችን ሊያስወግዱ ይችላሉ።

አንዳንድ ምግቦች ያዘሉት ስኳር አንጀታችን ውስጥ ገብቶ ስለማይፈጭ የአንጀት ግድግዳን የመለጠጥ ኃይል ሊኖረው ይችላል። ይህ ደግሞ ህመም ያስከትላል። የአፈጫጨት ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚመገቡትን ምግብ እንዲመርጡ ዶክተሮች ይመክራሉ።

የምግብ መብላላት ከአንዳንድ ምግቦች ላይ እንደ ግሉተን ያሉ ንጥረ ነገሮችን ሊያስወግድ ይችላል። ይህ ደግሞ ከዘመናዊ አኗኗር ጋር ተያይዞ የሚመጣ ችግር ነው።

“በጠቅላላው የምንበላው ምግብ ፋይበር ያነሰው ነው። በጣም በርካታ አንቲባዮቲክስ እና ጭንቀት አለብን፤ መልካም እንቅልፍ አናገኝም። እነዚህ ተደማምረው በሰውነታቸውን ውስጥ ያሉ ማይክሮቦችን ይጎዳሉ” ይላሉ ቪንዴሮላ።

የተብላሉ ምግቦችን ይህን ችግር የመቅረፍ ኃይል ሊኖራቸው ይችላል። “የተብላሉ ምግቦች ዋናው ጥቅም በሕይወት ያሉ ማይክሮቦችን ለሰውነታችን መስጠት ነው። ማይክሮቸቦቹ ወደ ሰውነታችን ገብተው የሰውነት መከላከል ኃይላችን እንዴት ህመምን መቆጣጠር እንዳለበት ያስተምሩታል።”

በቅርቡ ይፋ የሆነ አንድ ጥናት ሶወርክራውት (የተብላላ ጥሬ ጥቅል ጎመን) መመገብ ህመምን የመቀነስ ኃይል እንዳለው ያሳያል። ይህ ምግብ በደማችን ውስጥ ያለውን ላክቲክ አሲድ በመጨመር ሰውነታችን ውስጥ ባዕድ ነገር እንደገባ ለመከላከል አቅማችን ያሳውቃል ይላሉ አጥኚዎቹ።

የተብላሉ ምግቦች

የተብላሉ ምግቦች ጭንቀትን ይቀንሳሉ?

የተብላሉ ምግቦች ለአእምሯችን ጤና መልካም ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ይህን በተለመከተ የተሠሩ ጥናቶች ጥቂት ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2023 በተሠራ አንድ ጥናት ባለሙያዎች ተሳታፊዎችን ለሁለት በመክፈል አንደኛውን ቡድን ዕፅዋት ላይ የተመሠረት የተብላላ ምግብ፣ ሌላኛውን ቡድን ደግሞ ያልተብላላ ምግብ እንዲመገብ አድርገው ለሦስት ሳምንታት ተከታተሉ።

አጥኚዎቹ ውጤታቸውን ሲገመግሙ የተብላላ ምግብ የተመገበው ቡድን የተለያየ ዓይነት ባክቴሪያ ያለውና በባክቴሪያ የሚመረቱ ሌሎች ንጥረ ነገሮች ያሉት ሆኖ ሲገኝ ሌላኛው ቡድን ግን ይህ የለውም።

በሌላ ጥናት ደግሞ የተብላላ ምግብ አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች የአእምሮ ጤናቸው መረጋጋት የሚስተዋልበት ሲሆን፣ የተብላላ ምግብ የማይወስዱ ሰዎች ደግሞ የፀባይ መለዋወጥ ይታይባቸዋል። የጥናቱ ውጤት ገና አልታተመም።

በሌላ ያልታተመ ጥናት ደግሞ ባለሙያዎች ለአይጥ የምዕራቡ ዓለም የሚመገበው ስኳር እና ቅባት የበዛበት ምግብ ሰጥተው ድብርት ያስከትላል ወይ? የሚለውን ለማየት ሞክረው ድብርት እንደተጫጫነው ማስተዋል ችለዋል።

ቤተ-ሙከራ ውስጥ ለነበሩት ሌሎች አይጦች ደግሞ የተብላሉ ምግቦች ሰጥተው የተሻለ ውጤት ማግኘት ችለዋል።

የተብላሉ ምግቦች ከአእምሮ ጤና በተጨማሪ ክብደት ለመቀነስ ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ነገር ግን ይህ ጥናት ገና ጥልቅ ምርምር ይጠይቃል ይላሉ ሙያተኞቹ።

ተመራማሪዎች የተብላሉ ምግቦች ለጤና ያላቸውን ጥቅም በተመለከተ በርካታ ጥናቶች ሊካሄዱ እንደሚገባ ያምናሉ። ሌላኛው የተመራማሪዎች ጥረት የተብላሉ ምግቦች ወጥ የሆነ ንጥረ ነገር እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።

የተብላሉ ምግቦች ጎጂ ሊሆኑ የሚችሉት በርካታ አሚኖ ካላቸው እንዲሁም በኢንዱስትሪ የተመረቱ የተብላሉ ምግቦች ብዙ ስኳር ሊኖራቸው መቻሉ ነው።

በጣም ብዙ ጥናት የተሠራበት የተብላላ ምግብ እርጎ ነው ይላሉ ቪንዴሮላ። በትኛውም ዓለም ቢመረት ከሁለት ዓይነት ባክቴሪያዎች ነው የሚመረተው ሲሉ ይክላሉ።

ምንም እንኳ የተብላሉ ምግቦችን በተመለከተ የተሠሩ ጥናቶች በቂ ናቸው ባይባልም፤ ባለሙያዎች እንድንመገባቸው ይመክራሉ። ነገር ግን ከአመጋገብ ሒደታችን ጋር ስናዋህዳቸው ቀስ በቀስ ይሁን ይላሉ።