ቬሎ የለበሱ ሙሽሮች

ከ 9 ሰአት በፊት

ሙሽሪት ኤቭንሊን ሴክጋላካን ነጭ የሙሽራ ቬሎ ለብሳ ከሺርሊይ ሞላላ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው እየሄዱ ነው። ኤቭንሊን ከአንድ በላይ ጋብቻን በሚያበረታታው የደቡብ አፍሪካ ቤተክርስቲያን በሚፈፀም የበርካቶች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተደራቢ ሚስት ለመሆን ተቃርባለች።

ከእነርሱ ጀርባ ሙሽራው ሌሲባ ሞላላ በጆሃንስበርግ ደቡብ ምዕራብ ክፍል በሚገኘው በዓለም አቀፉ ጴንጤቆስጤ ቤተክርስቲያን ከሌላ ሴት ጋር ጋብቻ እየፈፀመ ነበር።

ከአንድ በላይ ሚስት የማግባት (ፖሊጋሚ) የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ በፋሲካ ዕለት ከተፈፀሙት 55 ጋብቻዎች መካከል አንዱ ነበር።

ከእነዚህ ጋብቻዎች መካከል ወደ ቤተሰባቸው ተጨማሪ ሚስት ያመጡት ሰባቱ ጥምረቶች ነበሩ። ሆኖም ሁሉም ጋብቻዎች ወደ ፊት ሌላ ሚስት ወደ ቤተሰባቸው እንደሚቀላቅሉ ተናግረዋል።

በታዳሚዎች በተሞላው አዳራሽ ውስጥ “ከአንድ በላይ ጋብቻን የፈቀደው እግዚአብሔር ነው” ሲሉ ደጋግመው ይናገራሉ።

ሺርሊይ የሞላላ ሁለተኛ ሚስት ናት። በትዳር ለ25 ዓመታት ቆይተዋል። ሺርሊይ ከዚህ ቀን ቀደም ብሎ “ተደራራቢ ጋብቻ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም መሠረቱ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ነው” በማለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ዋቢ አድርጋለች።

ሺሪሊይ ለጋብቻው በባለቤቷ የመጀመሪያ ሚስት መመረጧንም ትናገራለች። እርሷ አሁን በሕይወት የለችም። ሆኖም ሦስተኛዋ ሚስት ቤተሰቡን ተቀላቅላለች።

የ48 ዓመቷ ሺርሊይ እንደምትለው ሌላ የትዳር አጋር የመጨመሩ ሒደት ከመንፍሳዊ ሕይወት እንደጀመረ በመገልጽ፣ ይህም አዲስ የምትቀላቀለውን ሚስቱን እንደ እህት እና እንደ ጓደኛ ለመቀበል ሁኔታውን ቀላል አድርጎልኛል ትላለች።

“እኛ [የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ሚስቶች] አንድ ዓይነት ልብስ እስከመልበስ ድረስ ተግባብተን ነበር። ይህን ከሞላላ ቤተሰብ ነው የተማርኩት። ለኤቭሊንም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ የቻልኩትም ለዚያ ነው” ብላለች።

ኤቭንሊን (በቀኝ) ባለፉት ወራት ሞላላን (ከኋላ የሚታየው) ለማግባት ስትዘጋጅ ሺርሊይ (በግራ) ምሥጢረኛዋ ሆና እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።
የምስሉ መግለጫ,ኤቭንሊን (በቀኝ) ባለፉት ወራት ሞላላን (ከኋላ የሚታየው) ለማግባት ስትዘጋጅ ሺርሊይ (በግራ) ምሥጢረኛዋ ሆና እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።

የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ በይፋ ከመጀመሩ በፊት ያለምንም ቃለ መሃላ ቀለበት ያሰሩ ሲሆን፣ እኩለ ቀን ላይ ከአዳራሹ ውጪ የተሰበሰቡት እድምተኞች የተለያዩ ቀለማት ባሏቸው አልባሳት ተውበው እና በመዝሙሮች ታጅበው ሥነ ሥርዓቱን እያደመቁት ነበር።

በሺዎች የሚቆጠሩት እድምተኞች መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አብረው ይዘምራሉ።

የተወሰኑት የቤተክርትያኒቱን ሰማያዊ እና ነጭ አልባሳት ለብሰዋል። ሌሎች ደግሞ ለድግሱ ይመጥናል ባሉት መንገድ ዘንጠዋል።

ለአምስት ሰዓታት በዘለቀው ድግስ ሙሽሮች በወዳጅ ዘመዶቻቸው ታጅበው ጥሩ ሆኖ ለመታየት በመሞከር ሥነ ሥርዓቱ ተካሂዷል።

አንድ ብዙ አባላት ያሉት የሙሽራዋ ሚዜዎች ሎሚ ቀለም ያለው ልብስ ለብሰዋል። በሌላ በኩል የሙሽራው ሚዜዎች ጉቺ የተባለ ብራንድ ያለው ሱፍ ለብሰው ይታያሉ።

ቀደም ብሎ የቤተክርስቲያኑ ባለሥልጣናት በቤተክርስቲያኑ መግቢያ ላይ ሁሉም ታዳሚዎች ለፕሮግራሙ የሚመጥን ልብስ መልበሳቸውን አረጋግጠዋል። ለሴቶች አጭር እና የተገላለጠ ልብስ እንዲሁም ሱሪ አይፈቀድም። ፀጉራቸውንም መሸፈን አለባቸው። ወንዶች ኮት እንዲለብሱ ነው የተፈቀደው።

ቤተክርስቲያኑ ጥብቅ የሆነ የሥነ ምግባር ደንብ ነው ያለው። በማንኛውም አገልግሎት ወቅት በአዳራሹ ውስጥ ታዳሚዎች በፆታ ተለያይተው ነው የሚቀመጡት። ‘መጀናጀንም’ አይፈቀድም።

የ67 ዓመቱ ሙሽራ ሌሲባ ሞላላ ለቢቢሲ ሲናገር “ስለ ድርብርብ ጋብቻ ያወቅኩት ወደ ቤተክርስቲያኑ መምጣት ከጀመርኩ በኋላ ነው። ሴትን በፍቅረኝነት ብቻ መያዝ አይፈቀድም ነበር። በመሆኑም አንድ ሴት ለእኔ እንደማትበቃኝ ተገነዘብኩ። ከዚያም ከሚስቴ ውጪ ከመወስለት ሌላ ሚስት ላግባ የሚል ስሜት አደረብኝ” ብሏል።

ይህ በርካቶች ትዳር የሚመሠርቱበት ሠርግ በገጠራማዋ ከተማ ዙርቤኮም በሚገኘው በቤተክርስቲያኑ ዋና መቀመጫ በዓመት ሦስት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ ይህም በፋሲካ ዕለት እንዲሁም በመስከረም እና ታኅሣሥ ወር ላይ ይካሄዳል።

እያንዳንዱ ሠርግ ከተጠናቀቀ በኋላ ሰርገኞቹ በቀይ ምንጣፍ ላይ በመረማመድ ፎቶ ይነሳሉ።

አሁን ጊዜው የቤተክርስቲያኗ መሪ ሊዮናርድ ፍሬደሪክ ጂ ሞዲስ ነው። እርሳቸው ወደ ወደ ሥፍራው ሲመጡ በሠርጉ የነበረው ድባብ ወዲያው ነበር የተለወጠው።

‘አጽናኙ’ የሚባሉት መሪው ከቤተሰባቸው ጋር ወደ ውስጥ የዘለቁት በማርሽ ባንድ፣ በፈረሰኞች እና ተከታትለው በሚጓዙ ቅንጡ ተሽከርካሪዎች ታጅበው ነበር። ከተሽከርካሪዎቹ መካከል ሚድናይት ሳፋየር ሮልስ ሮይስ የሚባለው ቅንጡ መኪና ይገኝበታል።

ፀሐይዋ መጥለቅ ስትጀምር ይፋዊ ፕሮግራሙ የሚጀመርበት ጊዜ ነበር። ተጋቢዎቹ በተነጠፈው ነጭ ምንጣፍ ላይ በዝግታ እየተራመዱ ወደ አዳራሹ ይገባሉ።

የሞላላ ሦስት ሚስቶች ተራ ሲደርስ አገኘኋቸው። ኤቭሊን በጣም ደስተኛ ነበረች።

እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ የሚካሄደው ሥነ ሥርዓቱ ሞዲሴ አዲስ ጥንዶች እና ሌሎች ሚስቶቻቸውን ከባረኩ በኋላ ተጠናቋል። ሆኖም ዝግጅቱ ምሽቱን ቀጥሏል።

እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ከሰርግ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ እንደዚህ ትልቅ አይደለም። የተለያዩ ባህል እና ሃይማኖት ባለባት ደቡብ አፍሪካ በአንድ ጊዜ በርካታ የጋብቻ ሥነ ሥርዓትን መፈፀም የተለመደ አይደለም።

የቤተክርስቲያኗ መሪ የመጡበት ቅንጡ መኪና
የምስሉ መግለጫ,የቤተክርስቲያኑ መሪ ሊዮናርድ ፍሬዴሪክ ወደ ሥን ሥርዓቱ ሲያቀኑ በቅንጡ መኪናዎች እና በማርሽ ባንድ ታጅበው ነበር።

ተጨማሪ ሚስት በማግባት ጋብቻን መፈፀመም የተለመደ አይደለም። አንድ ወንድ ከአንድ በላይ ሴት ማግባት በደቡብ አፍሪካ ይፈቀዳል። እንዲህ ዓይነት ግንኑነቶች በወሳኝ ሁነት የሚመዘገቡ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄዱ ሥነ ሥርዓቶች አይኖሩም።

ሆኖም የአፍሪካ ገለልተኛ የሆነ ቤተክርስቲያን የሚባለው አይፒኤችአይ ጋብቻው በአገሪቷ ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እስከተመዘገበ ድረስ ቤተክርስቲያኑ ይህንን በይፋ ይባርካል።

በአውሮፓውያኑ 2022 እንደወጣው የሕዝብ ቆጠራ መረጃ ከሆነ ከ85 በመቶ የሚበልጡ ደቡብ አፍሪካውያን ራሳቸውን ክርስቲያን እምነት ተከታይ እንደሆኑ የገለጹ ሲሆን፣ ስምንት በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካን ባህላዊ እምነት እንደሚያራምዱ ተናግረዋል።

እንደ አይፒኤችሲ ያሉ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ሁለቱንም ሥርዓቶች የሚያራምዱ ሰፊ ተከታዮች አሏቸው። ሆኖም ፕሮቴስታንት እና የካቶሊክ እምነት በአገሪቷ በርካታ ተከታይ ያላቸው እምነቶች ናቸው።

በአይኤኤችሲ ቤተክርስቲያን ተደራራቢ ጋብቻ ሲሰበክ እና ሲበረታታ ቆይቷል። “እንደ አውሮፓውያኑ በ1962 በሰዌቶ የተፀነሰ እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተወለደ ነው፤ አሁን ላይ ቤተክርስቲያኗ አባላት 3.1 ሚሊዮን ደርሷል” ብለዋል የቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ምፖ ማክዋና ለቢቢሲ ሲናገሩ።

ሞላላ የመጀመሪያ ሚስታቸውን ያገቡት ቤተክርስቲያኗን ከተቀላቀሉ ከስድስት ዓመት በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ በ1991 ነበር። እርሷም የቤተክርስትያኗ አባል ነበረች። ቤተክርስቲያኗ አባል ካልሆኑ ሰዎች ጋር የሚፈፀም ጋብቻን በግልጽ ትከለክላላች።

ከዘጠን ዓመታት በኋላ ሞላላ እና ባለቤታቸው ቤተሰባቸውን እንዴት እንደሚያሰፉ ቁጭ ብለው መነጋገር ጀመሩ። ከዚያም በቤተክርስቲያኗ ተከታዮች መካከል በተደረገ ሰፊ ፍለጋ ያኔ 23 ዓመት ወጣት በሆነችው ሽርሊይ ላይ ዓይናቸው አረፈ።

“በቤትክርስቲያኗ አባል ከሆኑት በርካታ ሴቶች መካከል መመረጤ በጣም ወሳኝ አንደሆንኩ ተሰማኝ” ትላለች ሽሪሊይ።

ኤቭሊንም የተመረጠችው እንዲሁ በቤተክርስቲያኗ አነሳሽነት የካቲት ወር ላይ ጀምሮ በተደረገ ሒደት ነው። እርሷ እንደምትለው ሃሳቡን ለመቀበል ጊዜ ፈጅቶባታል። ሆኖም አዳዲስ ሃሳቦችን የመቀበል አመለካከቷ ሁኔታውን ቀላል አድርጎልኛል ትላለች።

የ44 ዓመቷ ኤቭሊን በቤተክርስቲያኗ ነው ያደገችው። ወደ ቤተክርስቲያኗ ድጋሚ ከመመለሷ በፊት ከአባልነት ወጥታ ሦስት ልጆችን ወልዳለች።

ሞላላ ከኤቭሊን ጋር ባላቸው ጋብቻ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ልጆቿን በማደጎ ወስዷቸዋል። በዚህም የሚያሳድጋቸው ልጆች ቁጥር 13 ደርሰዋል።

እያንዳንዳቸው ሚስቶች ለየብቻ የሚኖሩ ሲሆን፣ ኤቭሊን ግን አዲስ ሙሽራ በመሆኗ ሞላላ ቤት ውስጥ ነው የምትኖረው።

አንድ ወንድ ተጨማሪ ሚስት ማግባት በደቡብ አፍሪካ ባህል የሚፈፀም ልማዳዊ ድርጊት ሲሆን፣ በአገሪቷ ያሉትን ዜጎች በሃሳብ ከፋፍሏቸዋል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በርካታ በእውነት ላይ የተመሠረቱ የቴሌቪዝን ፕሮግራሞች በርካታ ቤተሰቦችን በተመለከተ የሆነ ሃሳብ ያጫሩ ሲሆን፣ ጠቃሚ ነው አይደለም የሚል ክርክር አስነስቷል።

ኤቭሊን [ቬሎ የለበሰችው] ከመጀመሪያ የሞላላ ሚስት ጋር
የምስሉ መግለጫ,ኤቭሊን [ቬሎ የለበሰችው] ከመጀመሪያ የሞላላ ሚስት ጋር

በደቡብ አፍሪካ የባህል፣ የሃይማኖት እና የቋንቋ መብቶች ኮሚሽን ውስጥ የሃይማኖት ባለሙያ ሆኑት ፕሮፌሰር ሙሳ ዙሉ እንደሚሉት በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰቦች ውስጥ የኤችአይቪ ሥርጭት መስፋፋት የተለመደ ነበር።

ምንም እንኳን አሁን ላይ ችግሩ ቢቀንስም አሁንም ትልቅ ችግር አንደሆነ ባለሙያው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ማክዋና በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ ቀደም ብሎ ይህንን ለተጋቢዎች ታስገነዝባለች ያሉ ሲሆን፣ ጥንዶች እና ተደራራቢ ጋብቻ ያላቸው ቤተሰቦች ከኤችአይቪ ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን እንዴት እንደሚጠብቁ ታስተምራለች ብለዋል።

ጋብቻ ለመፈፀም የፈለጉ ሰዎች መጀመሪያ የኤችአይቪ ምርመራ ማድረግ አለባቸው።

“ይህንን ሳያደርግ ማንም ሰው ጋብቻውን መፈፀም አይችልም፤ ስለዚህ ወደፊት ሊከሰት የሚችል እንግዳ ነገር አይኖርም” ብለዋል።

ጥንዶቹም የምርመራ ውጤታቸውን አንዳቸው ለአንዳቸው መናገር የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗም ይህንን ትመዘገብላች።

ይህ ግልጽነት በማታለል ወይም በማጭበርበር በኋላ ላይ የሚከሰት ፍቺንም ይቀንሳል ብለዋል።

ፕሮፌሰር ዙሉ እንደ አይፒኤችሲ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት “ግማሽ ክርስትና፣ ግማሽ አፍሪካዊ” የሆነ ለክርስትና ልዩ አቀራረብ ቢኖራቸውም፣ በባህላቸው አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችሉ መመሪያዎች አሏቸው ይላሉ። በችግር ላይ ያሉ ቤተሰቦችንም ይረዳሉ ብለዋል።

ሃሳቡ ከቀረበ በኋላ በሒደቱ በንቃት ይሳተፋሉ። ይህም በርካታ ወራትን ይወስዳል። ከጋብቻ በፊት በሚካሄዱ ሦስት ሥነ ሥርዓቶች ይለያሉ ብበልዋል።

“በዚህ ጊዜያ ጥንዶች በመንፈሳዊ ፕሮግራም ኃላፊነት የሚወስዱበትን ጉዳይ ምን ያህል እንደሚያውቁ እርግጠኛ መሆናቸውን በሚያረጋግጥ መንፈሳዊ ሥርዓት ውስጥ ያልፋሉ ብለዋል” ማክዋና።

ይፋዊው ሥነ ሥርዓት ከመካሄዱ በፊት በርካታ ጥንዶች እንግዳ ናቸው። ይህ የ35 ዓመቱን ፍሬድ ሌሶዋላ እና የ31 ዓመቷን ሬንዳኒ ሚያውን የገጠማችውም ይኸው ነበር።

ጥንዶቹ ቃል ኪዳን ያሰሩት በፋሲካ ዕለት ነበር። ሁለቱም ጋብቻ የፈፀሙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሌሶዋላ ሚስቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ያያት ከአስር ዓመት ገደማ በፊት በጓደኛው ሰርግ ላይ ነበር – በጋራ ጋብቻ በሚፈፀምበት ዕለት ።

ሆኖም ከትውውቃቸው በኋላ በወቅቱ አላወሩም፤ ምን ያደረጉት ነገርም አልነበረም ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በዕይታ ብቻ ነበር የወደድኳት፣ ግን አስታውሳታለሁ። ሁለታችንም የቤተክርስቲያናችንን አስተምህሮ እናውቃለን።”

በኋላ ላይ ሁለቱም የፌስቡክ ጓደኛ ከሆኑ በኋላ ግንኙነታቸው ለልደት መልካም ምኞት ከመለዋወጥ ያለፈ አልነበረም። ይህ ግን የዘለቀው እስከ ታኅሣሥ 2024 ወደ መጋባቱ ሃሳብ ሲሄዱ ቤተሰቦቹን አሳወቀ፤ ከዚያም ለቤተክርስቲያኑ አስተዳዳር አሳውቋል።

“ለእኔ ፍላጎት እንዳለው አላውቅም ነበር። ሳውቅ በጣም ነበር ደስ ያለኝ። ስለ ሰርጌ ቀን ሁልጊዜም አስብ ነበር” በቤተ ክርስቲያኑ ያደገችው መሆኗን ትናገራለች።

ህልሟ ተሳክቶ ከዘጠኙ ሙሽሮች ጋር በጌጥ በተንቆጠቆጠ ቬሎ እና ቲያራ፣ እንዲሁም ብዙ ሜትሮች ርዝመት ያለውን የሙሽራ ልብስ ለብሳ በመንጣፉ ላይ ስትራመድ ተውባ ነበር።

ጥንዶቹ አሁን ላይ ትኩረታቸው ስለ አዲሱ ሕይወታቸው ቢሆንም ባልየው ሌላ ሚስት ለማግባት የሚያስችለው ጋብቻ ቢፈጽም ሁለቱም ፈቃደኞች ናቸው።

“ባለቤቴ ሌላ ሚስት የማግባት ዕድል አንዳለው አውቃለሁ” የምትለው አዲሷ ሙሽራ ሌትሶአሎ፤ ባለቤቷ ሌላ ሚስት ደርቦ እንዲያገባ በሚፈቅደው “በድርብ ጋብቻ አምናለሁ” ብላለች።

ሆኖም ይህ አመለካከት በበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ አወዛጋቢ ነው።