
ከ 9 ሰአት በፊት
የጆሮ ኩክ በመባል የሚታወቀው ጆሮ ውስጥ ያለው ፈሳሻማ ቅባት ለጆሮ ጤና ጠቃሚ ከመሆኑ ባሻገር እንደ አልዛይመር እና ካንሰር ያሉ ህመሞችን ይጠቁማል።
ስለ አንድ ሰው ጤና ለማወቅ የጆሮ ኩክ (earwax) ትልቅ ዋጋ አለው። ሳይንቲስቶች ይህን በመጠቀም ህመሞችን ለማግኘት እየሞከሩ ነው።
የልብ ህመም እና ዓይነት 2 የስኳር ህመም ከጆሮ ኩክ ጋር ይገናኛሉ።
የጆሮ ኩክ በጆሮ የላይኛው ክፍል ላይ የሚፈጠር ሲሆን፣ ከሲርሚነስ ግላንድ እና ሰባሲየስ ግላንድ ይመነጫል። የሞተ የቆዳ ክፍል እና ፀጉርም ይቀላቀልበታል።
የጆሮ ትቦ ቅባታማ ሆኖ እንዲቆይ እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ነፍሳት፣ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ በጆሮ በኩል ወደ ሰውነት እንዳይገቡም ይከላከለላል።
የጆሮ ኩክ ስለ ሰዎች የጤና ሁኔታ ብዙ መረጃ እንደሚሰጥ ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል።
በአውሮፓውያን እና በአፍሪካውያን ዘንድ በአብዛኛው ቀለሙ ቢጫ እና ብርቱካናማ ነው። የምሥራቅ እስያውያን የጆሮ ኩክ ደረቅ እና ግራጫ መሆኑን ሳይንስ ይጠቁማል።
ይህንን የጆሮ ኩክ የሚያመርተው በሰው ልጅ ውስጥ የሚገኝ የተለየ ዘረ መል ነው ። ይህ ዘረ መል ከብብት ሥር ከሚፈጠር ጠረን ጋርም ይገናኛል።
ደረቅ የጆሮ ኩክ ያላቸው ሰዎች የብብት ሥር ጠረን እንደሌላቸው ጥናቶች ያሳያሉ።

Skip podcast promotion and continue reading

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በቀጥታ በዋትስአፕ ለማግኘት
ይህን በመጫን የቻናላችን አባል ይሁኑ!
End of podcast promotion
በአውሮፓውያኑ 1971 ኒኮላስ ኤል ፔትራኪስ የተባለ ባለሙያ ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ በሠራው ጥናት ጥቁር አሜሪካውያን እና የጀርመን ሴቶች ፈሳሻማ የጆሮ ኩክ ሲኖራቸው በጡት ካንሰር የመሞት ዕድላቸው እንደሚጨምር ገልጿል።
ጃፓናውያን እና ታይዋናውያን ሴቶች ደረቅ የጆሮ ኩክ ስላላቸው ተጋላጭነታቸው እንደሚቀንስም ተናግሯል።
በ2020 በቶክዮ በተሠራ ጥናት ከ270 ካንሰር የያዛቸው ሴቶች የጆሮ ኩክ ናሙና ተወስዷል። ይህም ከ273 ካንሰር የሌለባቸው ሴቶች ናሙና ጋር ተነጻጽሯል።
77 በመቶ ጃፓናውያን ካንሰር ያለባቸው ሴቶች ፈሳሻማ የጆሮ ኩክ እንዳላቸው ጥናቱ ጠቁሟል። ሆኖም ግን የጥናቱ ግኝት አወዛጋቢ ነው።
በጀርመን፣ በአውስትራሊያ እና በጣሊያን የተሠሩ ጥናቶች ፈሳሻማ እና ደረቅ የጆሮ ኩክ ባላቸው ሰዎች መካከል የተለያየ የካንሰር ተጋላጭነት አላገኙም።
በእርግጥ በእነዚህ አገራት እምብዛም ደረቅ የጆሮ ኩክ ያላቸው ሰዎች አይገኙም።
ሜፕል ሲረፕ ዩሪን ዲዚዝ የሚባለው ህመም ምግብ ውስጥ የሚገኝ አንዳንድ አሚኖ አሲድ እንዳይብላላ የሚያደርግ ነው።
በደም እና በሽንት ውስጥ ይከማችና የሚያውክ ጠረን ይፈጥራል።
ሽንት የማይረብሽ ጠረን እንዲኖረው የሚያደርገው ሶቶሎን የሚባለው ንጥረ ነገር በጆሮ ኩክ ውስጥም ይገኛል።
ስለዚህ ህመሙ ያለበትን ሰው ለመለየት የጆሮ ኩክ ናሙና መውሰድ ይቻላል። ይህም የዘ መል ምርመራ በማድረግ ብዙም ወጪ ላለማውጣት ይረዳል።
በሉዊዝያና ስቴት ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ራቢ አን ሙሳ “የጆሮ ኩክ ጠረን አለው። ልጆች በተወለዱ በ12 ሰዓት ውስጥ ይህ ጠረን ካለ በሰውነታቸው ውስጥ ህመሙ መኖሩን እናውቃለን” ይላሉ።
አንዳንዴ የኮሮናቫይረስን ለማወቅ የጆሮ ኩክ ናሙና ይወሰዳል። ዓይነት 1 እና 2 የስኳር ህመሞችም በጆሮ ኩክ ይለያሉ።
የልብ ድካምን ለማወቅ የደም ምርመራ ቀላል ቢሆንም የጆሮ ኩክ ናሙና መውሰድም እንደሚረዳ ማወቅ ተችሏል።
- በፊንጢጣ አካባቢ የሚከሰት እብጠት ሁሉ ኪንታሮት ነው? ኪንታሮት ካልታከመ ምን ያስከትላል?28 ሚያዚያ 2025
- በቀን ምን ያህል ጊዜ መጸዳጃ ቤት ይሄዳሉ? ዓይነ ምድራችን ስለጤናችን ምን ያመለክታል?21 ሚያዚያ 2025
- የእርግዝና መከላከያ ክኒን በእርግጥ ሴቶችን የበለጠ እንዲጨነቁ ሊያደርግ ይችላል?22 ሚያዚያ 2025
የጆሮን የማድመጥ ችሎታ የሚጎዳውና ሰዎች እንዲያዞራቸው የሚያደርገው ማሪኒስ የተባለው ህመም ከጆሮ ኩክ ጋር ይገናኛል።
“ምልክቱን ለማወቅ ከባድ ነው። ሆኖም ግን ጆሮ መስማት ሊያቆም ይችላል” በማለት ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
“በሌላ ምርመራ ሊታወቁ ያልቻሉ ህመሞችን ለማወቅ የጆሮ ኩክ እንጠቀማለን። በደም ወይም በሽንት ምርመራ ለማወቅ ቢሞከርም የሚወስደው ጊዜ ረዥም ነው” ሲሉም ያክላሉ።
የጆሮ ኩክ ሰውነት ውስጥ ያለውን ኬሚካል መጠን እና ባህሪ እንዲሁም ምግብ የማብላላት አቅም ለማወቅ ይረዳል።
በብራዚል የኬሚስትሪ መምህር ሮቤርቶ አንቶኒሲ ፊልሆ አብዛኛው ህመም ምግብን ከማብላላት አቅም ማጣት ጋር የተገናኘ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የስኳር ህመም፣ ካንሰር፣ ፓርኪንሰንስ እና አልዛይመርስ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ።
“ሕዋሳት ሊፒድ፣ ካርቦሃይሬት እና ፕሮቲንን ወደ ኃይል ሲለውጡ ጤናማ የሰውነት እንቅስቃሴ ይኖራል” ይላሉ ባለሙያው።
ደም፣ ሽንት፣ ላብ እና እምባ ካላቸው የኬሚካል መጠን ይልቅ የጆሮ ኩክ እንደሚበልጥ በጥናት ደርሰውበታል።
ኬሚካል ኢኮሎጂስቱ ብሩስ ኪምባል እንደሚሉት፣ የጆሮ ኩክ አንድ ቦታ ላይ ስለሚከማች ናሙና ወስዶ ለመመራመር ምቹ ነው።
ከሰው ጆሮ ናሙና በመውሰድ የተወሰኑ የካንሰር ዓይነቶች መኖራቸውን ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ ሴረሜኖግራም (cerumenogram) ይባላል።
በ2019 በብራዚል የኬሚስትሪ መምህር ሮቤርቶ አንቶኒሲ ፊልሆ ከ52 የካንሰር ህሙማን ላይ የጆሮ ኩክ ናሙና ወስደዋል።
ሊምፎሚያ፣ ካሪሲኖሚያ እና ሉኬሚያ ያለባቸው ህሙማን ናቸው ናሙና የሰጡት።
50 ካንሰር የሌለባቸው ሰዎች ለማነጻጸሪያ ናሙና ሰጥተዋል።
ጥናቱ 27 ዓይነት የጆሮ ኩክ የካንሰር ምልክት ማሳያ እንደሚሆኑ ይጠቁማል። መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን ሦስቱን የካንሰር ዓይነቶች በሰውነት ውስጥ መኖራቸውን ለማረጋገጥም ተችሏል።

ካንሰር ከመፈጠሩ አስቀድሞ ሰውነት ምግብን ወደ ኃይል የመለወጥ አቅሙ ሲዳከም ምልክቶችን ለማየት ጥናታቸውን ተጠቅመውበታል።
“የመጀመሪያው ደረጃ ላይ ሳሉ የሚታወቁ ካንሰሮችን 90 በመቶውን ማከም ተችሏል። ወደ ካንሰርነት ሳይለወጥ ማወቅ ከተቻለ ውጤቱ ከዚህም በላይ ይሆናል” ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ፓርኪንሰንስ እና አልዛይመርስ በቀዳሚ ደረጃ ላይ ሳሉ መታወቅ ይችሉ እንደሆነ ለማወቅ ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።
“ምርመራው የየትኛውም ሕክምና አካል እንዲሆን ማድረግ ነው የወደፊት ዕቅዳችን። ስኳር፣ ካንሰር፣ ፓርኪንሰንስ እና አልዛይመርስን በጆሮ ኩክ ማወቅ መቻል ቀላል ነገር አይደለም” ሲሉ ያስረዳሉ።
የሮቤርቶ አንቶኒሲ ፊልሆ ጥናት በብራዚል ሆስፒታል ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
በሉዊዝያና ስቴት ዩኒቨርስቲ የሚሠሩት ራቢ አን ሙሳም ተስፋ ሰጪ ውጤት ለማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል።
“ፋርማሲ ሄዶ መግዛት የሚቻል የምርመራ መሣሪያ ቢኖር እና ልክ ለኮቪድ-19 እንደተደረገው መመርመር ቢቻል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ይላሉ ባለሙያዋ።
በሰው አካል ውስጥ ካለው የኬሚካል መጠን ያነሰ መጠን በጆሮ ኩክ ናሙና ሲገኝ አንድ ህመም እንዴት እንደተከሰተ እና እንዴት ማከም እንደሚቻል ለማወቅ እንደሚረዳ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ።
ጥናቱ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ እንዲሆንም ተጨማሪ ምርምሮች ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።