ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)
የምስሉ መግለጫ,ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

7 ግንቦት 2025

ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የትጥቅ ግጭት ውስጥ የገባው የአማራ ክልልን አብዛኛውን አካባቢ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ‘ኤንቢሲ’ ከተባለ የአገር ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ ስለ አማራ ክልል የፀጥታ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ክልሉ “የኅልውና አደጋ” ውስጥ ገብቶ ነበር ያሉት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ጊዜ 90 በመቶ የክልሉ አካባቢዎችን መንግሥት መቆጣጠሩን ተናግረዋል።

የፋኖ ኃይሎች በበኩላቸው ከ80 በመቶ በላይ የክልሉ አካባቢው በእጃቸው እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት አሁንም ድረስ መቀጠሉን ከሁቱም ወገኖች የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት “የክልሉ መንግሥት ተጠናክሯል፤ አደረጃጀቱን እስከ ቀበሌ አጠናክሯል። በአብዛኛው 90 በመቶ በሚሆነው አካባቢ ክልሉ በራሱ ታጣቂ፣ አስተዳደር፣ የፀጥታ ሁኔታውን የሚቆጣጠርበት ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከቁጥጥሩ ውጪ የሆኑትን አካባቢዎችን በተመለከተ ደግሞ፤ “የቀሩትን የክልሉ የፀጥታ ኃይል እና የፌደራል ኃይል በጋራ ሆነው ችግሩን የሚፈቱበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው” ብለዋል።

“በድርድር እና ሕግ በማስከበር እንቅስቃሴ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሰላማዊ ሁኔታ ተፈጥሯል” ቢሉም ሚኒስትሩ፤ የክልሉ ነዋሪዎች ግን ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ የእለት ከዕለት ሕይወታቸው በግጭቱ መስተጓጎሉን ይናገራሉ።

ሚኒስትሩ ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቆይታ አጠቃላይ የአገሪቱን የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ያነሱ ሲሆን፤ “ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የሰላም ሁኔታ መጥታለች” ሲሉ ሁለት የተቃርኖ ሀሳቦች መኖራቸውን ገልፀዋል።

“መሬት ላይ ያለው እውነታ እና የሰዎች አረዳድ የተለያዩ ናቸው” ሲሉ እገታ፣ ዝርፊያ እና የንብረት ውድመት የመሰሉ ክስተቶችን በማንሳት ይህ ሁኔታ “በየትኛውም አገር ይኖራል” ሲሉ ዶ/ር ለገሰ ተናግረዋል።

አገሪቱ ከነበረችበትን “የታፈነ የፖለቲካ” ምኅዳር በማስፋት እና ወደ ነፃነት በሚደረገው ሽግግር ችግሮችን በኃይል መፍታት የወለዳቸው ክስተቶች እንደሆኑም አስምረዋል።

“የፀጥታ አካላት በሳሱበት አካባቢ፤ የፀጥታ አካላት በሌላ ነገር በሚጠመዱበት አካባቢ ይህን አጥንተው ረብሻ የሚፈጥሩ ሽፍቶች አሉ። ቀድሞም የነበረ ነው፤ በሂደትም ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።

“አልፎ አልፎ የማገት ሁኔታዎች አሉ፤ የመዝረፍ ሁኔታዎች አሉ፤ [ንብረት] ማቃጠል ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ እየቀነሱ ቢመጡም አሁንም አሉ” ብለዋል።

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ባሉ አካባቢዎች ሳይቀር በተደጋጋሚ ስለሚፈፀሙ እገታዎች ባሕሪም ሲናገሩ “አብዛኛው እገታዎች የሚደረጉት ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው” ሲሉ “በአቋራጭ ለመበልፀግ” የሚደረግ እንደሆነ ገልፀዋል።

አልፎ አልፎ እገታዎች የፖለቲካ መልክ እንደሚሰጣቸው ያብራሩት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ማሳያ አድርገው የአማራ ክልልን ያቀረቡ ሲሆን፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች “ኃይላቸውን ለማሳየት” ሲሉ እገታዎችን ይፈፅማሉ ብለዋል።

ሚኒስትሩ እገታዎችን ለመከላከል የማኅበረሰቡን “የነቃ ተሳትፎ” ደጋግመው ያነሱ ሲሆን፤ “ውስጣዊ ሁኔታውን በአብዛኛው የሚመለከተው ኅብረተሰቡን ነው። ኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ፤ አካባቢውን የሚጠብቅ ካልሆነ በወታደራዊ ኃይል ሁሉንም አካባቢ መጠበቅ አይቻልም ብለዋል።