ከብቶች

11 ግንቦት 2025, 07:56 EAT

በጃፓኗ ሆኪያኮ መንደር የቀንድ ከብቶች ሲጸዳዱ ለኃይል ማመንጫነት እንዲውል የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል።

20 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል በወተት ተዋጽኦ ሥራ ይታወቃል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ላሞች ይገኙበታል።

በእርግጥ ላሞች ሲጸዳዱ አፍንጫ የሚያውክ ሽታ ያስከትላል። የጃፓኗ ከተማ ግን ይህንን ወደ ጠቃሚ ኃይልነት በመለወጥ የሃይድሮጂን ነዳጅ በማመንጨት ትታወቃለች።

ሃይድሮጂን ሲቃጠል በካይ ካርበን አይለቅም። ስለዚህ አካባቢን ከሚበክሉ ጋዞች የተሻለ አማራጭ ነው።

ቤት ለማሞቅ፣ ለመኪና ወይም ለአውሮፕላን እንዲሁም ለመርከብ የኃይል ምንጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘላቂነት ያለው እና የማይበክል የኃይል አማራጭ ነው።

አሁን ባለው አሠራር ሃይድሮጂን ሲመረት ሜቴን ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃል። ሜቴን ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን ከሚያባብሱ በካይ ጋዞች መካከል ይመደባል።

ሺካዎይ የሃይድሮጂን ማምረቻ ነው። በጃፓን የሚገኘው ፋብሪካው ከብቶች ሲጸዳዱ ኃይል ያመነጫል።

ይህ በጥንቃቄ ካልተያዘ የቀንድ ከብቶች የሚለቁት ሜቴን ውሃ እና ከባቢን ይበክላል።

ሌላው ሃይድሮጂን የሚያመርተው ድርጅት ኤር ወተር ውስጥ የሚሠራው ማይኮ አቤ “ይህ ሃይድሮጂን ማመንጫ መንገድ በጃፓን ነው የተጀመረው” ይላል።

ከከተማው 30 በመቶ የሚሆነውን የከብቶች ተረፈ ምርት ወደ ታዳሽ ኃይል ይለውጣሉ።

በአውሮፓውያኑ 2015 የጃፓን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ነው አሠራሩን የዘረጋው።

ከአካባቢው ባሻገር የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ይደግፋል ተብሎ ይታመናል።

ተረፈ ምርት

ፋብሪካው 70 ኪውቢክ ሜትር ሃይድሮጂን ምርት አለው። ይህም ማለት በቀን 28 መኪኖች ሊያንቀሳቅስ የሚችል ኃይል ነው።

እስካሁን በግብርና አካባቢ ትራክተር ለማንቀሳቀስ ሃይድሮጂኑን እየተጠቀሙ ነው።

ትራክተሮቹ ግዙፍ ስለሆኑ በባትሪ እንዲሠሩ ለማድረግ ቀላል አይደለም። ስለዚህም በአካባቢው በሃይድሮጂን የሚሠሩ ትራክተሮች አርሶ አደሮች ሲጠቀሙ ይስተዋላል።

በአካባቢው የሚገኝ የዓሣ ማቀነባበሪያ ፋብሪካም የሚሠራው በሃይድሮጂን ነው።

ነገር ግን ሃይድሮጂን ከእንከን ነጻ ነው ማለት አይደለም። በኃይል ታምቆ መቆየት አለበት። በቀላሉ ሾልኮ ሊወጣም ይችላል።

ከነዳጅ ጋር ሲነጻጸር ሃይድሮጂን ሦስት እጥፍ አቅም አለው። በዓለም በጣም ቀላሉ ጋዝ ሃይድሮጂን ነው።

ሃይድሮጂን ለማምረት፣ ለማከማቸት እና ለማጓጓዝ መሠረተ ልማት መሟላት አለበት።

የጃፓኗ ከተማ በዚህ ረገድ ፈተና ገጥሟት ነበር።

በጣም ቀዝቃዛ ወቅት ሲሆን ሃይድሮጂን ለማምረት አዳዲስ መንገድ ይጠቀማሉ።

ከተፈጥሮ ጋዝ ሃይድሮጂን የሚመረትበት መንገድ እና ከብቶች ሲጸዳዱ ሃይድሮጂን የሚመረትበት መንገድ ተመሳሳይ ናቸው።

ከብቶች ከተጸዳዱ በኋላ ሃይድሮጂን ተመርቶ የሚቀረው ተረፈ ምርት ለማዳበሪያነት ይውላል።

አሁን ላይ ሃይድሮጂን ለማምረት እና ለማቆየት የጃፓን ብሔራዊ የኤሌክትሪክ መስመር ጥቅም ላይ ቢውልም በቀጣይ ዘላቂነት ወዳለው እና አካባቢን ወደማይጎዳ ማቆያ እንደሚሸጋገሩ የፋብሪካው ሠራተኛ ይናገራል።

ሃይድሮጂን ከሌሎች ኃይል ምንጮች አንጻር ዋጋው ውድ ነው።

ማይኮ አቤ “በሃይድሮጂን የሚንቀሳቀስ መኪና ገና አልተለመደም። ስለዚህ ሃይድሮጂኑን በማቆያ ውስጥ ይዘነዋል” ይላል።

የሃይድሮጂን እና የሌሎች ነዳጆች ዋጋ ተቀራራቢ እንዲሆን ለማድረግ ጥረቶች አሉ። ሃይድሮጂን በነዳጅ ማደያ እንዲቀርብ ለማስቻልም ታቅዷል።

ኃይል ማመንጫ
የምስሉ መግለጫ,የሃይድሮጂን ኃይል ማመንጫ

በሌሎች አገራት ከአሳማ እንዲሁም ከሌሎች እንስሳት ከሚገኝ ተረፈ ምርት ኃይል የማመንጨት ሙከራዎች ተስተውለዋል። ያን ያህል ጉልህ ናቸው ማለት ግን አይቻልም።

ጃፓን በሃይድሮጂን መኪና ከዓለም ቀዳሚ ናት። በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ከፍተኛ ገንዘብም እያፈሰሰች ነው።

አሁን ላይ ከሃይድሮጂን ይልቅ የኤሌክትሪክ መኪና ርካሽ ነው።

የሃይድሮጂን አቅርቦት አሁን ባለው መጠን የመላው ጃፓንን ፍላጎት ላያዳርስ ይችላል።

ሆኖም ግን ለወደፊቱ የጃፓን ምጣኔ ሃብት አካል የማድረግ ጅማሮ አለ።

በአሜሪካ የኤሊኖይ ዩኒቨርስቲ ሃይድሮጂንን ለማምረት ተመሳሳይ ሙከራ እየተደረገ ነው።

የሸንኮራ አገዳ እና የበቆሎ ተረፈ ምርት ጥቅም ላይ ከዋሉት መካከል ይጠቀሳሉ።

ሃይድሮጂን ለመፍጠር የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ለመቀነስ ሙከራ እየተደረገ ነው።

በዩኒቨርስቲው ኬሚካል ኢንጂነር ሜንሽ ሲንግ “ከተረፈ ምርት ሃይድሮጂን በመፍጠር ግንባር ቀደም ነን” ይላል።

በጃፓን በፉካዎካ ከተማም መሰል ሙከራ ተከናውኗል።

ከአስርታት በላይ በከተማው የቆሻሻ ማስወገጃ ሃይድሮጂን ለማምረት ምርምር ተደርጓል።

የበካይ ጋዝ ልቀታቸው ዜሮ የሆነ የቆሻሻ መሰብሰቢያ መኪኖችን ለማሽከርከር ሃይድሮጂን ጥቅም ላይ ውሏል።

ኃይል ማመንጫ

በከተማው የሃይድሮጂን ምርት ኃላፊ አሪካ ሚያካ እንደምትለው፣ በእነዚህ ተሽከርካሪዎች የተተኩት መኪኖች የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት በማስከተል ቀዳሚ ነበሩ።

“አሁን ይሄንን ልቀት ለመቀነስ ነው እየሠራን ያለነው” ትላለች ኃላፊዋ።

ካይሹ ዩኒቨርስቲ እና ፉካዮካ ዩኒቨርስቲ በጥምረት ይሄንን ምርምር ይመራሉ።

“ቆሻሻ በየቀኑ ከከተማዋ ይለቀቃል። ይሄን ቆሻሻ ጥቅም እንዲሰጥ ነው የምናደርገው። በአግባቡ ቆሻሻው እንዲወገድ አድርገን ለሃይድሮጂን ምርት እናውለዋለን። ለአካባቢው የኃይል ምንጭም ይሆናል” ስትል ኃላፊዋ ታስረዳለች።

በ2024 ቶዮታ በጃፓን የመጀመሪያው የሃይድሮጂን መኪና እንዲተዋወቅ አግዟል።

አምቡላንስ፣ የቆሻሻ ማንሻ መኪና እና እቃ አመላላሽ ከባድ ተሽከርካሪዎች በሃይድሮጂን እንዲሠሩ ማድረግ ተችሏል።

በ300 ኪሎ ግራም ሃይድሮጂን 30 ተሽከርካሪዎች ለ12 ሰዓት እንዲጓዙ ተደርጓል።

ኮንኮርድ ብሉ በጀርመን፣ ሕንድ፣ ጃፓንና አሜሪካ ከተረፈ ምርት ኃይል የሚያመነጭ ፋብሪካ አለው።

በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከፍሳሽ ውሃ ሃይድሮጅን የማምረት ሙከራ ተደርጓል።

የዩኬው ዋቭሪክ ማኒፋክቸረር በዚህ ረገድ ታዋቂ ነው። በአምስት ዓመታት ቴክኖሎጂው እውን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የበረራው ዘርፍ ከካርበን ልቀት 2 በመቶ ይይዛል።

በዩኬ ቤተ ሙከራ ከሰው ዓይነ ምድር ኃይል በማመንጨት ለጄት በማብረር እንዲውል ሙከራ ተደርጓል።

ለአሁኑ ጃፓን በሃይድሮጂን ምርት የብዙዎችን ትኩረት ስባለች።

የሃይድሮጂን ተሽከርካሪዎች በሕዝቡ ዘንድም እየታወቁ መጥተዋል።