የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን

11 ግንቦት 2025, 08:04 EAT

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር “ከግንቦት 7 በፊት. . .ቀጥተኛ ንግግር” ለማድረግ ጥሪ አቀረቡ።

ቅዳሜ ዕለት ከክሬምሊን በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ “የግጭቱን መሰረታዊ ምክንያት ለማስወገድ እንዲሁም ዘላቂ እና ጠንካራ ሠላም ለማምጣት የሚያስችል. . . ኮስተር ያለ ንግግር ማድረግ እንፈልጋለን” ብለዋል።

ይህ የቭላድሚር ፑቲን ንግግር የተሰማው የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪየር ስታርመር፣ የፈረንሳዩ ኢማኑዔል ማክሮንን ጨምሮ የአውሮፓ መሪዎች ዩክሬንን ከጎበኙ እና ሩሲያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ለ30 ቀናት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም እንድታደርግ ከጠየቁ በኋላ ነው።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለአውሮፓ መሪዎች ጥያቄ “በሚገባ ማሰብ ይኖርብናል” ሲሉ የሞስኮን ምላሽ አሳውቀው፣ ነገር ግን “እኛ ላይ ጫና ለማድረስ መሞከር ፈጽሞ ረብ የለሽ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፑቲን በመግለጫቸው በቱርክ ትልቋ ከተማ ኢስታንቡል እንዲካሄድ የጠየቁት የሁለቱ አገራት ንግግር “አዲስ የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነት” ላይ መድረስ ያስችላል የሚለው ላይ “ተስፋ እንዳላቸው” ተናግረዋል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት እሁድ ዕለት ለቱርኩ ፕሬዝዳንት ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶዋን ጋር በውይይቱ ዝርዝር ጉዳዮችን በሚመለከት እንደሚያነጋግሯቸው አስታውቀዋል።

የአውሮፓ መሪዎች ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ተጉዘው ሞስኮ ለአንድ ወር የሚቆይ የተኩስ አቁም እንድታደርግ በጠየቁበት ዕለት በቀረበው የሩሲያ የእንነጋገር ግብዣ ላይ እስካሁን ኪየቭ ምላሽ ሰጥታለች።

ቮሎድሞር ዜሌንስኪ ዩክሬን ስለ ተኩስ አቁም ለመነጋገር ከፑቲን ጋር ለመገናኛት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

አክለውም ሩሲያ ጦርነቱ እንዲያበቃ ፍላጎት ማሳየቷ “በጎ ምልክት ነው” ብለዋል።

ዜለንስኪ “ሩሲያ የተሟላ፣ ዘላቂ እና አስተማማኝ የሆነ የተኩስ አቁም ከነገ ጀምሮ እንደሚኖር ማረጋገጫ ትሰጣለች ብዬ እጠብቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

የአውሮፓ መሪዎች “የፈቃደኞች ጥምረት” ሲሉ የመሰረቱት አባል አገር የሆኑት ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ዩኬ እና ፖላንድ ወደ ኪየቭ በተጓዙበት ወቅት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር በአንድነት መግለጫ ሰጥተው ነበር።

መሪዎቹ ፑቲን ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለማድረግ የማይስማሙ ከሆነ “አዲስ እና ግዙፍ” ማዕቀብ “በአየር፣ በባሕር እና በየብስ” በሩሲያ ኤነርጂ እና ባንክ ዘርፎች ላይ ሊጥሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

እነዚህ መሪዎች ይህንን ምክረ ሃሳብ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

ሰር ኪየር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ያቀረቡት የተኩስ አቁም ሃሳብ ” በፍጥነት ተቀባይነት ማግኘት ያለበት” እንደሆነ “ጥርት ያለ አቋም” ነው ያላቸው ብለዋል።

ከስብሰባው በኋላ ዜለንስኪ መሪዎቹ ከዩክሬን “ጎን በመቆማቸው” አመስግነዋል።

“ዛሬ ዘላቂ ደህንነት እንዴት መገንባት እና ማረጋገጥ እንዳለብን የሚለው ላይ እናተኩራለን” ብለዋል።

በአውሮፓ መሪዎች የቀረበው ምክረ ሃሳብን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት የክሬምሊን ቃል አቀባይ “አዲስ እርምጃ ነው። ነገር ግን እኛ ላይ ጫና ለማድረግ መሞከር ረብ የለሽ ነው” ብለዋል።

የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የክሬምሊን ቃል አቀባይ የአውሮፓ መሪዎች “ግንኙነታችን ዳግም እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ በባህሪያቸው ጠብ አጫሪ ናቸው” ማለታቸውን ጠቅሰው ዘግበዋል።

ከዚህ ቀደም ሞስኮ የተኩስ አቁምን በተመለከተ እንደምታስብበት ገልጻ የነበረ ሲሆን በቅድሚያ ግን ለዩክሬን የሚቀርበው ወታደራዊ እርዳታ መቆም አለበት ብላ ነበር።

ፑቲን በክሬምሊን ለተሰበሰቡ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የዩክሬን ጦር አዲስ የጦር መሳርያ እና የሰው ኃይል ካገኘ በኋላ፣ በጥድፊያ ምሽግ ከቆፈረ በኋላ እና አዲስ ኮማንድ ፖስቶችን ካቋቋመ በኋላ የተራዘመ ውግያ ከማካሄድ ይልቅ፣ ይህ የረዥም ጊዜ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የመጀመሪያው እርምጃ ይሆናል” ብለዋል።

አክለውም “ማን እንደዚያ ዓይነት ሠላም ይፈልጋል?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

ፑቲን በንግግራቸው ዩክሬንን ለ30 ቀናት በሩሲያ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ በመጣስ እንዲሁም ባለፈው ወር በፋሲካ በዓል ዕለት ከሩሲያ የቀረበላትን የተኩስ አቁም ጥሪ ውድቅ በማድረግ ከስሰዋል።

ሞስኮ የዩክሬንያንን የኢነርጂ መሠረተ ልማቶች ላለመምታት ስምምነት በተደረሰ ማግስት “ምንም ነገር ሳይለወጥ” ሞስኮ ጥቃቷን ቀጥላበታለች ሲሉ ዜሌንስኪ ለአውሮፓ መሪዎች ተናግረዋል።

ፑቲን በንግግራቸው የጠቀሱት ሌላኛው የተኩስ አቁም የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ድል መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ነው።

ኪየቭ በተናጠል የሚደረግን የሦስት ቀን የተኩስ ቁም ጥሪ “ለታይታ ነው’ በማለት ውድቅ አድርገዋለች።

ዜሌንስኪ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር።

የአውሮፓ መሪዎች በኪየቭ በተገኙበት ወቅት ከፕሬዝደነት ዜሌንስኪ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

የሦስት ቀኑ የተኩስ አቁም ይጀመራል ተብሎ በሚታሰብበት ሐሙስ ዩክሬን ሩሲያ 730 ጥሰቶችን ፈጽማለች በሚል “ተመጣጣኝ” እርምጃ መውሰዷን አስታውቃ ነበር።

ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬንን 480 ጥሰቶችን ፈጽማለች በማለት ከመወንጀሏ በፊት የተኩስ አቁሙ እየተጤነ ነው ብላ ነበር።

ፑቲን ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ ላይ “ሁሉም ነገር እየሆነም ቢሆን፣ ለኪየቭ ባለሰልጣናት ድርድሩን እንዲቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን. . . አጽንኦት መስጠት የምፈልገው ቀጥተኛ ንግግሩን እንዲቀጥሉ እንዲሁም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መሆን እንዳለበት ነው” ብለዋል።

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ለመጨረሻ ጊዜ ቀጥተኛ ንግግር የተካሄደው ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ አስቀድሞ ከሦስት ዓመት በፊት ነው።