
11 ግንቦት 2025, 08:31 EAT
ዶናልድ ትራምፕ የአገር ውስጥ ደህንነት መስርያ ቤት ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለማስወጣት የሚወስደውን እርምጃ ለማቀላጠፍ ቢያንስ ተጨማሪ 20,000 ፖሊሶችን እንዲመድብ ትዕዛዝ አስተላለፉ።
መመርያው የተላለፈው አርብ ዕለት ሲሆን አስተዳደሩ በፈቀዳቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉትን ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለማበረታታት የያዘው ዕቅድ አካል መሆኑ ተገልጿል።
ትራምፕ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት አሜሪካን ለቅቆ መውጣት “በተቻለ መጠን ቀላል” ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በፈቃዳቸው አሜሪካን ለቅቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ሰነድ አልባ ስደተኞችን የአውሮፕላን ትኬት ወጪን የአሜሪካ የፌደራል መንግሥት የሚሸፍን ሲሆን ተጨማሪ “ጉርሻ” ለመስጠት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መተላለፉ ተገልጿል።
ትዕዛዙ በአገር ውስጥ ደህንነት መስርያ ቤቱ ውስጥ የሠራተኞች ቁጥር መጨመር እንዴት በገንዘብ እንደሚደገፍ ያለው ነገር የለም።
ሕገወጥ ስደተኞችን በሚመለከት በቀጥታ እየሰራ የሚገኘው የኢሚግሬሽን እና ጉሙሩክ መስርያ ቤት በአሁኑ ሰዓት ከ 21,000 በላይ ሠራተኞች አሉት።
ከእነዚህም መካከል 6,100 ያህሉ ሕገወጥ ስደተኞችን ከአገር የሚያስወጡ ፖሊሶች ሲሆኑ ከ750 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ረዳቶቻቸው መሆናቸውን የኤጀንሲው ድረገጽ ያሳያል።
ትራምፕ ለረዥም ጊዜ የግዛቶች እና የአካባቢ ሕግ አስከባሪዎች እንዲሁም ብሔራዊ ዘብ ድንበር ጥሰው የሚገቡ ሕገወጥ ስደተኞችን በሚመለከት በመተባበር እንዲሰሩ ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።
ይህ የአሁኑ ትዕዛዝ የአገር ውስጥ ደህንነት መስርያ ቤቱ እያደረገ ያለውን ጥረት ” ለግዛቶች እና አካባቢ ሕግ አስከባሪዎች፣ የቀድሞ ፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ሌሎች የፌደራል ኤጀንሲ ባለሙያዎች ውክልና እና ኮንትራት የሚሰጥ ነው።”
- ፑቲን ከዩክሬን ጋር “በቀጥታ ለመነጋገር” ጥሪ አቀረቡ11 ግንቦት 2025
- በፈቃዳቸው ከአሜሪካ ለሚወጡ ሕገወጥ ስደተኞች ገንዘብ ሊሰጥ ነው6 ግንቦት 2025
- በየመን የስደኞች ማቆያ ላይ አሜሪካ በፈጸመችው ጥቃት የተገደሉት ሦስቱ ኢትዮጵያውያን የአንድ ቤተሰብ አባላት10 ግንቦት 2025
ዶናልድ ትራምፕ የሠራተኞች ቁጥር እንዲጨምር ጥሪ ያቀረቡት አስተዳደራቸው ሰነድ አልባ ስደተኞች ዩናይትድ ስቴትስን ለቅቀው እንዲወጡ የተለያዩ መንገዶችን እየተጠቀመ ባለበት ወቅት ነው።
ትራምፕ ሰነድ አልባ ስደተኞች በገዛ ፈቃዳቸው አሜሪካን ለቅቀው ለመውጣት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በዚህ ሳምንት የአገር ውስጥ ደህንነት መስርያ ቤት ዋና ጸኃፊ ክሪስቲ ኖኤም አሜሪካን በፈቃዳቸው ለቅቀው ለመውጣት ለሚወስኑ ሰነድ አልባ ስደተኞች የ1000 ዶላር ጉርሻ ለመስጠት እና የአየር ቲኬት ወጪያቸውን ለመሸፈን ቃል ገብተዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ጥር ወደ ሥልጣን ከተመለሱ ወዲህ አወዛጋቢውን በጦርነት ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውለውን ሕግ ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕገወጥ ስደተኞችን ማሰር እና ከአገራቸው ማስወጣት ጀምረዋል። ነገር ግን አንዳንዶቹ እርምጃዎቻቸው ሕጋዊ ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።
በዚህ ወር መጀመርያ ላይ በትራምፕ የተሾሙት የቴክሳስ ግዛት ዳኛ ፈርናንዶ ሮድሪጌዝ፣ አስተዳደሩ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ለማስወጣት እየተጠቀመበት ያለውን ሕግ “ሕገ ወጥ” ነው ብለዋል።
ሌላ በኒውዮርክ የሚገኙ የፌደራል ዳኛ እንዲሁ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
ትራምፕ ግን በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከአገር የሚያስወጡ ስደተኞችን በሚመለከት ሲናገሩ “ወደ አገር መመለስ” በማለት ነው።
“በአሜሪካ ለመቆየት የሚወስኑ ሕገ ወጥ ስደተኞች፣ ረዥም እስርን ጨምሮ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት፣ ያፈሩት ንብረት መወረስ እና ከአገር መባረር ይጠብቃቸዋል” ብለዋል።