
ከ 5 ሰአት በፊት
የማሊ ጦር ሠራዊት ሥልጣን ከያዘ በኋላ በተቃዋሚዎች ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ ወታደራዊው አስተዳደር በአገሪቱ ያሉ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አገደ።
“በመላው አገሪቱ ያሉ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ስብስብ እና ፖለቲካዊ ባሕሪ ያላቸው ድርጅቶች በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ” እንዲሆኑ ከወታደራዊው ቡድን (ሁንታ) ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ወጥቶ በአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን የተነበበረው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው በ2020 እና 2021 በማሊ በተደረገው መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን በጨበጡት ወታደራዊው መሪ አሲሚ ጎይታ የተፈረመ ሲሆን፣ ወታደራዊ መሪው ምርጫ ተካሂዶ ሥልጣን እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ቢያንስ ለቀጣይ አምስት ዓመታት በመንበራቸው ላይ ይቆያሉ እየተባለ ነው።
ይህ የወታደራዊው ቡድን ውሳኔ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገባ ሲጠይቁ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞን እንደሚቀሰቀስ ይጠበቃል።
ካለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ወዲህ የወታደራዊው መንግሥት ባለሥልጣናት በአገሪቱ በሚካሄዱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው።
ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው የዴሞክራሲ ጥያቄ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በኋላ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ፖሊስ መሆናቸውን በገለጹ በታጣቁ ግለሰቦች ታፍነው ተወስደዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ የማሊ ባለሥልጣናት ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።
ወታደራዊው መንግሥት ባዘጋጀው ባለፈው ወር በተጠራው እና ዋነኛ የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባልሆኑበት ጉባኤ ላይ የወታደራዊው ቡድን መሪ ጄኔራል አሲሚ ጎይታ አስከ 2030 ድረስ በፕሬዝዳንትነት እንዲቀጥሉ ሃሳብ ቀርቧል።
በ2022 በአገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ እንደሚካሂድ ቃል ገብቶ ከነበረው ወታደራዊ መንግሥት በኩል የቀረበው ይህ ሃሳብ ከተቃዋሚ መሪዎች እና ከሰብአዊ መብት ቡድኖች በኩል ውዝግዘት ገጥሞታል።
አሁን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ለማገድ የወጣውን አዋጅ የማሊ ዜጎች ችላ ሳይሉ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ይህንን ውሳኔ በጣሱ ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወሰድ ግን የተባለ ነገር የለም።
አዋጁ ጨምሮም በፖለቲካዊ ወይም አስተዳዳራዊ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ያሉ የአገሪቱ ዜጎች “ከለፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ሥራቸው ማከናወን መቀጠል” እንሚችሉ ገልጿል።
ይህ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማገድ ውሳኔ የመጣው በመንግሥት አዘጋጅነት ከተካሄደው አገራዊ ጉባኤ በኋላ የቀረበውን የመሪውን የሥልጣን ዘመን የማራዘም ሃሳብ ከቀረበ በኋላ ነው።
በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው ቡድን ባለፈው ሳምንት የአገሪቱን የሽግግር አስተዳደር በመቃወም ተቃውሞ ለማሰማት ጥሪ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣለውን ዕገዳ ተከትሎ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፎ ነበር።
የተቃዋሚ ቡድን መሪዎች ፖለቲካ ፓርቲዎችን ከእንቅስቃሴ ውጪ የማድረጉን የወታደራዊ መሪዎቹን ውሳኔ አውግዘውታል።
ሙሳ ማራ የተባሉት የቀድሞው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር በወታደራዊው መንግሥት የተላለፈው ዕገዳ “ባለፈው ዓመት በተጀመረው የእርቅ ጥረት ላይ የተፈጸመ ትልቅ ጥቃት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
አንድ የማሊ ጉዳይ ተንታኝ እንዳሉት ወታደራዊ መሪዎቹ ይህንን እርምጃ የወሰዱት “ከአገሪቱ ነጻነት አንስቶ በአመራር ላይ ያሉትን እና አሁን ድረስ ከቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው የሚባሉትን ቀደምት ልሂቃንን ከመንግሥት ውስጥ ለማስወጣትት ነው።”
የወታደራዊ መንግሥቱ መሪ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙት ከቡርኪናፋሶ እና ከኒጀር ወታደሮች ጋር የትብብር ኅብረት በመመሥረት ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሳይ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመቀነስ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል።
የማሊ ወታደራዊ መሪዎች በመፈንቅለ መንግሥት የያዙትን ሥልጣን ምርጫ በማካሄድ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመለሱ በመጠየቁ ምክንያት ጄነራል ጎይታ ማሊን ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ማኅበር ኤኮዋስ አስወጥተዋታል። በተመሳሳይ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀርም ከማኅበሩ እራሳቸውን አግልለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ሦስቱ ተጎራባች የምዕራበን አፍሪካ አገራት የጋራ ትብብር መሥርተው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ነው።